የቱርክ ፓርላማ የአገሪቱ ባሕር ኃይል በሶማሊያ እንዲሰማራ ፈቀደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን የአገሪቱን ባሕር ኃይልን በሶማሊያ ለማሰማራት ያቀረቡትን ሞሽን የአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጸደቀ።
መንግሥታዊው አናዱሉ ኤጀንሲ የቱርክ ጦር “የጸረ-ሸብርና የደኅንነት ስራዎችን ለመደገፍ እና ሌሎች ስጋቶችን ለመቀልበስ” ለሁለት ዓመታት በሶማሊያ ይሰማራል ሲል ዘግቧል።
ፓርላማው የአገሪቱ ጦር ወደ ሶማሊያ እንዲሰማራ ፍቃድ ይስጥ እንጂ ምን ያክል ጦር እና መቼ ወደ ሶማሊያ እንደሚያቀና የተባለ ነገር የለም።
የቱርክ ባሕር ኃይል በሶማሊያ የሚሰማራው ሁለቱ አገራት ከጥቂት ወራት በፊት የደረሱትን ወታደራዊ ስምምነት ተከትሎ ነው።
የካቲት 1/2016 ዓ.ም. አንካራ እና ሞቃዲሾ የመከላከያ እና የምጣኔ ሃብት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
የዚህ ስምምነት ሙሉው ዝርዝር ይፋ ባይደረግም በተለይ በመከላከያ ዘርፍ፤ ቱርክ የሶማሊያን ባሕር ኃይልን ለማጠናከር እና የአገሪቱን የባሕር ጠረፍ በጋራ ለመጠበቅ ከስምምነት መደረሱ ተነግሯል።
ከዚህ በተጨማሪም ቱርክ የሶማሊያን የባሕር ኃይል በማሠልጠን ለማስታጠቅ መስማማቷ ተገልጾ ነበር።
በወቅቱ የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ ከቱርክ ጋር የተደረሰው ስምምነት “የትኛውንም የሽብር ስጋት እና በባሕር ላይ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ጨምሮ ከውጭ አገራት የሚፈጸምን ጥሰት እንዲሁም ስጋትን” ለመከላከል ይጠቅማል ብለው ነበር።
ይህ ስምምነት ከተፈረመ ከጥቂት ቀናት በኋላ የካቲት 13/2016 ዓ.ም. የሶማሊያ ፓርላማ ስምምነቱን አጽቆት ነበር። ይህን ተከትሎ የቱርክ ባሕር ኃይል የጦር መርከብ ሞቃዲሾ ወደብ መድረሷ ይታወሳል።
የቱርክ ፓርላማ በበኩሉ ከፕሬዝዳንት ኤርዶሃን የአገሪቱ ጦር ወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር እንዲሰማራ የሚጠይቀውን ሞሽን አርብ ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም. ከተቀበለ በኋላ፤ ምክር ቤቱ ሞሽኑን ትናንት ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም. አጽድቆታል።
ፕሬዝዳንቱ ያቀረቡት ሞሽን ከአስር ዓመታት በላይ ሶማሊያ ደኅንነቷን እና መረጋጋቷን እንድታረጋግጥ እንዲሁም ሽብርትኝነትን እንድትዋጋ ቱርክ ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች ይላል።
ሞሽኑ ከእአአ 2009 ጀምሮ የቱርክ ጦር በሶማሊያ የባሕር ላይ ውንብድና፣ ዘረፋ እና የባሕር ላይ ሽብር ለመከላከል የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረቶችን ሲደግፍ ቆይቷል ይላል።
በሌላ በኩል ቱርክ የባሕር ኃይሏን ወደ ሶማሊያ እንድትልክ የአገሪቱ ፓርላማ መፍቀዱ የተሰማው፤ የአንካራ ሰርጓጅ መርከብ የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ወደ ሶማሊያ እንደምትጓዝ ከተገለጸ በኋላ ነው።
የቱርክ ኢነርጂ ሚኒስቴር በሶማሊያ የውሃ አካል ላይ ነዳጅ እና ጋዝ የምትፈልግ ሰርጓጅ መርከብ በአውሮፓውያኑ 2024 ማብቂያ እንደሚልክ አስታውቋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአንካራ እና ሞቃዲሾ ወዳጅነት ተጠናክሯል።
ቱርክ እአአ 2017 ላይ ከአገር ውጪ ትልቁን የራሷን ወታደራዊ ጦር ሰፈር በሶማሊያ ገንብታለች።
ከዚህ በተጨማሪ ቱርክ በአሁኑ ወቅት የሶማሊያን ሠራዊት እና ፖሊስ አባላት ታሰለጥናለች።
ቱርክ በሶማሊያ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን እና የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ከመገንባቷ ባሻገር፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሶማሊያ ተማሪዎች በቱርክ የትምህርት ዕድል እያገኙ ይገኛሉ።












