የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡመድ እና ምክትላቸው ከሥልጣን ተነስተው አዲስ አመራሮች ሊሾሙ ነው

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡመድ ኡጁሉ (በግራ)፣ ነገ ይሾማሉ ተብለው የሚጠበቁት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ (መሀል) እና ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ (ቀኝ)
የምስሉ መግለጫ, የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡመድ ኡጁሉ (በግራ)፣ ነገ ይሾማሉ ተብለው የሚጠበቁት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ (መሀል) እና ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ (ቀኝ)

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ሐሙስ በሚያደርገው አስቸኳይ ስብሰባ፤ ከስድስት ዓመት በላይ ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ በቆዩት አቶ ኡመድ ኡጁሉ እና በምክትላቸው አቶ ቴንኩዌይ ጆክ ቦታ አዲስ አመራሮችን ሊሾም ነው።

ነገ በሚደረገው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው እየሠሩ ያሉት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ፤ “በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ” ክልሉን ለመምራር በዕጩነት እንደሚቀርቡ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ሐሙስ ነሐሴ 9/2016 ዓ.ም. አንድ ቀን የሚቆይ አስቸኳይ ጉባኤ የጠራው “በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎች ለማሳለፍ” እንደሆነ የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ምክር ቤቱ በጠራው በዚህ ስብሰባ ላይ አዳዲስ አመራሮች እንደሚሾሙ የክልሉ ከፍተኛ አመራር የሆኑ ሁለት ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል አዲስ አመራሮች እንዲሾሙ የሚደረገው፤ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በክልሉ ላይ ባደረገው “ግምገማ እና ምዘና” ነባሮቹ አመራሮች “እንዲቀየሩ” ውሳኔ በማሳለፉ እንደሆነ አንድ ከፍተኛ አመራር ተናግረዋል። ፓርቲው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው “የተለያዩ የመንግሥት የልማት አፈጻጸም ግምገማዎች እና ሱፐር ቪዥኖችን” ካደረገ በኋላ መሆኑን ምንጩ አስረድተዋል።

ገዢው ፓርቲ፤ በክልሉ “የልማት አፈጻጸም፣ የፀጥታ እና ሰላም ሁኔታ እንዲሁም በዚህ ላይ ያለ መሻሻልን” በተመለከተ ያደረገው ግምገማ፤ በእነዚህ መስኮች ያለው የመንግሥት አፈጻጸም “እየወደቀ እንደመጣ” እንደደረሰበትም አክለዋል።

ምንጩ፤ “ክልሉ ላይ ያለው አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የልማት እድገት፣ የክልሉ መልካም አስተዳደር፣ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳይ እዚህ ላይ ያለው አፈጻጸም እየወደቀ ስለመጣ፤ በሥልጣን ላይ የነበሩትን [የክልሉ] አመራሮች መቀየር እንደሚያስፈልግ ፓርቲው ስለደረሰበት፤ ውሳኔ አድርጎ አዳዲስ የክልል ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ተመርጦ፤ ነገ ጠዋት ክልሉ በጠራው አስቸኳይ ጉባኤ እነዚህ አመራሮች የሚሾሙ ይሆናል” ሲሉ የፓርቲውን ውሳኔ አስረድዋል።

የጋምቤላ ከተማ አደባባይ

የፎቶው ባለመብት, Gambella Community Development of Canada

የምስሉ መግለጫ, ጋምቤላ ክልል ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ በተከሰቱ ግጭቶች እና ጥቃቶች ምክንያት የጸጥታ ሁኔታው ሲፈተን ቆይቷል

ገዢው ፓርቲ፤ የክልሉን አመራር ለመለወጥ ያሳለፈው ውሳኔ “አሁኑኑ እንዲሁ ሳይታሰብ፣ በደንብ ሳይገመገም የተወሰነ” እንዳልሆነ የሚናገሩት ምንጩ፤ የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ኡመድ እና ምክትላቸው አቶ ቴንኩዌይ ጭምር “አውቀውት እና ተቀብለውት” የተላለፈ ውሳኔ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ጋምቤላ ክልል፤ በገዢው ፓርቲ የሚደረግ ግምገማን ተከትሎ የክልሉን አመራር ሲቀይር ይህ የመጀመሪያው አይደለም። የቀድሞው ክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እንዲሁም ብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የተዋሃደው የቀድሞው የክልሉ ገዢ ፓርቲ “የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ” (ጋህአዴን) ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ጋትሉዋክ ቱት፤ በጥቅምት 2011 ዓ.ም. ከኃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት ከፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ግምገማ በኋላ ነበር።

የወቅቱ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሰናይ አኩዌርም በተመሳሳይ መልኩ ጥያቄ አቅርበው ከሥልጣን ለቅቀዋል። ከሥልጣን የለቀቁትን እነዚህን ሁለት አመራሮች ተክተው የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ሥልጣን የተረከቡት እስካሁን ድረስ ክልሉን ሲመሩ የነበሩት አቶ ኡመድ እና አቶ ቴንኩዌይ ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን በመጣ በስድስት ወራት ውስጥ ጋምቤላ ክልልን የመምራት ኃላፊነትን የተረከቡት አቶ ኡመድ፤ የሥልጣን ዘመናቸው ክልሉ በሰላም እና ፀጥታ ጉዳይ የተፈተነበት ነው። ባለፉት ዓመታት ክልሉ ተደጋጋሚ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እና ጥቃቶችን አጋጥመዋል።

የቀድሞው የጋምቤላ ርዕስ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት እና አሁን የተነሱት አቶ ኡመድ ኡጁሉ ስልጣን ሲረካከቡ

የፎቶው ባለመብት, Fana/screenshot

የምስሉ መግለጫ, የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ ኡጁሉ ወደ ሥልጣን የመጡት መስከረም 2011 ዓ.ም. ነበር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ የካቲት ወር ላይ በወጣው ሪፖርት፤ ካለፈው ዓመት ግንቦት እስከ ጥር 2016 ዓ.ም. በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የ138 ሰዎች ሕይወት ማለፉን እንዳረጋገጠ አስታውቆ ነበር።

ከሁለት ዓመት በፊትም በክልሉ ሲንቀሳቀስ የነበረው የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በጋራ በክልሉ መዲና ጋምቤላ ከተማ ጥቃት በመክፈት የተወሰነውን የከተማዋን ክፍል ለሰዓታት ተቆጣጥረው እንደነበር ይታወሳል።

በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ክልሉን ሲመሩ የቆዩት አቶ ኡመድ እና ምክትላቸው አቶ ቴንኩዌይ፤ በፌደራል መንግሥት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ እያገለገሉ ባሉ ሁለት አመራሮች እንዲተኩ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ እንደወሰነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጭ አስረድተዋል።

ነገ በሚደረገው የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ አማካኝነት የርዕሰ መስተዳድርነት ኃላፊነት ይረከባሉ ተብለው የሚጠበቁት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ እንደሆኑ ሁለት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስለ አዲሱ ሹመት ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው ወ/ሮ አለሚቱ፤ ጉዳዩን “መስማታቸውን” በመግለጽ ማረጋገጫ የሚገኘው በነገው ዕለት እንደሆነ ተናግረዋል። በነገው ዕለት በሚደረገው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ በደረሳቸው ግብዣ መሠረትም ወደ ጋምቤላ እንደሚጓዙ አረጋግጠዋል።

ለመምራት ይሾማሉ ተብለው የሚጠበቁት ወ/ሮ አለሚቱ፤ የክልሉ ምክር ቤት አባል ባለመሆናቸው ሥልጣኑን የሚረከቡት “በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ” እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጭ ገልጸዋል። በ1995 ዓ.ም. የወጣው የጋምቤላ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚሾመው “ከክልሉ ምክር ቤት አባላት መካከል” እንደሆነ ይደነግጋል።

ወ/ሮ አለሚቱ በአንጻሩ የምክር ቤት አባልነታቸው በፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።

ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Women and Social Affairs

የምስሉ መግለጫ, በነገው ዕለት ይሾማሉ ተብለው የሚጠበቁት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ናቸው

ከመስከረም 2014 ዓ.ም. በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ሲሰሩ የነበሩት ወ/ሮ አለሚቱ፤ በጋምቤላ ክልል ውስጥም ተመሳሳይ ሥራ የሚያከናውነውን የክልሉን ሴቶች እና ሕጻናት ቢሮ በኃላፊነት መርተዋል።በነገው ስብሰባ አዲሱ ኃላፊነታቸውን ያጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የጋምቤላ ክልል ምክር ቤትንም በምክትል አፈ ጉባኤነት አገልግለዋል።

በምክትል ርዕስ መስተዳድርነት እንዲሾሙ የሚቀርቡት ደግሞ በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ እና የውጭ ግንኙነት ኦፊሰር ሆነው በመስራት ላይ ያሉት ዶ/ር ጋልዋክ ሮን ናቸው። ከሰባት ወር ገደማ በፊት ወደ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተሾሙት ዶ/ር ጋልዋክ፤ በመንግሥት ኃላፊነት እና በአካዳሚክስ ውስጥ የቆዩ ናቸው።

ዶ/ር ጋልዋክ፤ ከዚህ ቀደም በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲሁም በጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲንነት እንዳገለገሉ ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል። ወደ አዲስ አበባ በመምጣትም በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ሰርተዋል።

በመንግሥት የኃላፊነት ዘመናቸው ደግሞ የክልሉን የትምህርት እንዲሁም የአቅም ግንባታ ቢሮዎች በኃላፊነት መምራታቸውን ምንጮች ገልጸዋል።

በእነዚህ ሁለት አመራሮች የሚተኩት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ፤ በገዢው ብልጽግና ፓርቲ “ሌላ ተልዕኮ” ይሰጣቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጭ ገልጸዋል።

ሁለቱ አመራሮች የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል መሆናቸውን ያስታወሱት ምንጩ፤ ፓርቲው አዲስ ሹመት የሚሰጣቸው “በሚመጥናቸው መንገድ” እንደሆነ አክለዋል።