ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን የማተራመስ እርምጃን በዝምታ እንደማትመለከት አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Ministry Of foreign Affairs
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት አስታወቀች።
ኢትዮጵያ ተሳታፊ የሆነችበት እና በመጪው ዓመት ጥር ወር የሚጠናቀቀው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ ቀጣዩ ሁነት ጋር ተያይዞ ስጋት አንዣቧል ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የረቡዕ፣ ነሐሴ 22/ መግለጫ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እርምጃ የሚወስዱ ሌሎች ተዋናዮች አሉ ብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን መግለጫ ያወጣው ወታደሮችን እንዲሁም የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ሁለት የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች በትናንትናው ዕለት በሞቃዲሾ የአየር ማረፊያ ደርሰዋል መባላቸውን ተከትሎ ነው።
በተጨማሪ የሶማሊያ መንግሥት "ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ስትል ከሳለች።
ኢትዮጵያ በዚህ መግለጫ ላይ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ እርምጃ እየወሰዱ ነው ያለቻቸውን "ሌሎች ተዋናዮች"ም ሆነ የውጭ ኃይሎች ማንነት እንዲሁም በምን መንገድ እንደሆነ አልገለጸችም።
ሆኖም በቀጣናው የብሔራዊ ደህንነቷን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሁሉ በንቃት እየተከታተለች እንደሆነ አሳስባለች።
ግብጽ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተገባው የባህር በር መግባቢያ ስምምነት ውጥረት ውስጥ ለገባችው ሶማሊያ በሁለት የጦር አውሮፕላኖች የጦር መሳሪያዎች ልካለች።
የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች በሶማሊያ የታዩት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ካይሮ እና ሞቃዲሾ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ነው።
በተጨማሪም ግብጽ በሚቀጥለው ዓመት በሶማሊያ ለሚሰማራው አዲስ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ወታደሮች ለመዋጣት ያቀረበችው ሃሳብ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአፍሪካ ህብረት መግለጫ ላይ ይፋ ሆኗል።
የአፍሪካ ህብረት ሽግግር ተልዕኮን የሚተካው የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ላይ አዲስ ስጋት ይዞ መምጣቱን ይህም ለአገሪቱ አሳሳቢ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫው ጠቁሟል።
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ወታደሮቿን ያዋጣችበት የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በመጪው ዓመት ጥር ወር ተልዕኮውን አጠናቆ የጸጥታ ሁኔታውን የሶማሊያ መንግሥት እንዲረከብ እንደሚደረግ ተገልጿል።
ሆኖም በሶማሊያ የጸጥታ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ከአስር ሺህ የማይበልጡ ወታደሮች ያሉበት የሰላም አስከባሪዎች ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባለበት እንደሚሰማራ ተጠቅሷል።
በሶማሊያ በቀጣይነት የሚሰማሩትን የሰላም አስከባሪዎች በተመለከተ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እየተዘጋጁ መሆኑን ያስታወቀችው ኢትዮጵያ “ቀጣናው ሊተነበይ ወደማይቻል ፈተና ውስጥ እየገባ ይገኛል” ብላለች።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ወታደሮቻቸውን ያሰማሩ አገራት ተደጋጋሚ ጥሪዎችና አስተያየቶች ትኩረት አልተሰጣቸውም ስትል ወቅሳለች።
ኢትዮጵያ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወታደሮቿን እንድታስገባ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚገኘው የሰላም አስከባሪ ልዑክ አሰማርታ ትገኛለች።
ይህንንም ከግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ የመከላከያ ሰራዊት መልካም ስምና ዝናን እንዲሁም መስዋዕትነት የሚያጠለሹ መግለጫዎች ወጥተዋል ሲልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ተችቷል።
ይህንንም ኢትዮጵያ በዝምታ እንድታልፍ ከአንዳንድ ወገኖች በኩል ፍላጎት ታይቷል ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ።
ኢትየጵያ “ለሶማሊያና ለአካባቢው ሰላምና ፀጥታ መስፈን፣ ለጋራ ዕድገት እና በክልሉ ያሉ ህዝቦች መካከል ያለውን የጠበቀ የእርስ በርስ ትስስር ይበልጥ እንዲጎለብት ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን” አስታውሷል መግለጫው
አክሎም“ቀደም ሲል አህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ አሸባሪ ቡድኖች ላይ የተገኘውን አበረታች ውጤት አደጋ ላይ የሚጥሉና የሚቀለብሱ ድርጊቶች ኢትዮጵያ አትታገስም” ብሏል።
ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተፈረመ የባሕር በር መግባቢያ አወዛጋቢ ስምምነት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ቱርክ እያሸማገለች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የሁለቱን አገራት ውጥረት ለማርገብ በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች ላይ በንቃት ተሳትፎ ማድረጓን ገልጻ ተጨባጭ ውጤቶች መታየታቸውን አስታውሳለች።
የሶማሊያ መንግሥት “እነዚህን ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ስትል ከሳለች።
ቀጠናውን ለማተራመስ ይሻሉ የተባሉ የውጭ ኃይሎች በዚህ መግለጫ በስም አልተጠቀሱም።
ሆኖም “ለአጭር ጊዜ ፍላጎታቸው እና ከንቱ አላማቸው ሲሉ በክልሉ ውጥረትን ለማቀጣጠል የሚሞክሩ ኃይሎች ዕኩይ ተግባራቸው የሚያስከትሏቸዉን መዘዞች መሸከም ይኖርባቸዋል።” ሲል መግለጫው አስጠንቅቋል።
ራሷን በነጻ አገር ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተገባው የባህር በር መግባቢያ ስምምነት ምክንያት ሶማሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች የሰላም ተልዕኮው ጊዜው ሳይጠናቅቅ እንዲወጡ በመግለጫዎች ማስታወቋ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ስምምነት አዲሱ ተልዕኮ ከሚወሰንበት፣ ከሰኔ መጨረሻ በፊት ካልሰረዘች በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ስር እንዲሁም በሁለትዮሽ ስምምነት የሰፈሩት ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከአገሪቱ እንደሚወጡ እንደሚደረግ የአገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሑሴን አሊ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በአትሚስ ስር 3 ሺህ ያህል ወታደሮችን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አሰማርታለች።
ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ወታደሮችን ጨምሮ በሶማሊያ ተሰማርተው ከሚገኙት 18 ሺህ 500 ያህሉ 5 ሺዎቹ ከአገሪቱ እንዲወጡ ተደርገዋል።
ይህንን የሶማሊያ አቋም አስመልክቶ ከዚህ ቀደም በቢቢሲ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢዩ ተድላ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ያላት ተልዕኮ በሶማሊያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት የተቀበለው የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ኃላፊነት ያለው ነው ብለዋል። ጥያቄውም የሚመጣው ከሶማሊያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በእነዚህ አህጉራዊ እና አለም አቀፍ ተቋማት እንደሚሆንም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ወታደሯቿን እንድታስወጣ ከተፈለገ በይፋ ጥያቄው ሲቀርብ ተግባራዊ እንደሚሆን አምባሳደር ነብዩ ጠቁመው “ከሶማሊያ መንግሥት፣ ከአፍሪካ ኅብረትም ይሁን ከተባበሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ኢትዮጵያ በሶማሊያ ያለውን ኃይሏን ታስወጣ የሚል በይፋ የቀረበ ነገር የለም” ሲሉ ተናግረው ነበር።
ከአትሚስ በኋላ የሚሰማራው ኃይል እና ያለው ዝግጅት ገና እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ነቢዩ “ለእኛ ቀላል ነው ኃይላችንን ስበን ‘በፈር ዞን’ [የጦር መጠባበቂያ ሰፈር] እንፈጥራለን” ብለው ነበር።
ነገር ግን ለኢትዮጵያ የሚያሰጋ ነገር ካለ አገሪቷ እጇን አጣጥፋ እንደማትቀመጥ ገልጸው “ለእኛ የብሔራዊ ደኅንነት የሚያሰጋ ከሆነ የማንንም ፍቃድ የምንጠብቅበት ነገር አይደለም እኛ የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ቃል አቀባዩ ከዚህ ቀደም ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ አጽንኦት መስጠታቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ከሶማሊያ በኩል ተደጋጋሚ ክሶች እና መግለጫዎች ከመቅረባቸው በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።












