ኮሪያውያን ወላጆች እስረኛ ሳይሆኑ ለምን ‘መታሰርን’ ፈለጉ?

ባዶ ክፍል ውስጥ የተቀመጠች ሴት
የምስሉ መግለጫ, ደቡብ ኮሪያውያን ወላጆች በፈቃደኝነት በባዶ ክፍል ውስጥ ብቻቸውን እያሳለፉ ነው።

በደቡብ ኮሪያ በሚገኘው የደስታ ፋብሪካ (ሃፒነስ ፋክተሪ) ያሉ ክፍሎች ከውጭው ዓለም ጋር የሚገናኙት በበራቸው ላይ ባሉ የምግብ ማቅረቢያ ቀዳዳዎች ብቻ ነው።

አምስት ካሬ ሜትር በሚሆኑት በእነዚህ ጠባብ ክፍሎች ስልክ ወይም ላፕቶፕ ይዞ መግባት አይፈቀድም።

ወላጆች ከክፍሎቹ ባዶ ግድግዳ ጋር ተፋጠው ነው የሚያሳልፉት።

በደስታ ፋብሪካው ነዋሪዎች ሰማያዊ ቀለም ያለው የእስረኞች የደንብ ልብስ ይለብሳሉ፤ ነገር ግን እስረኞች አይደሉም። ወደ ማዕከሉ የገቡት መገለል ስለሚፈጥረው ስሜት የሕይወት ልምድ ለማግኘት ነው።

አብዛኞቹ ወላጆች የሚጋሩት ነገር አላቸው። ሁሉም ከማኅበረሰቡ ራሳቸውን የነጠሉ ልጆች ወላጆች ናቸው።

በእነዚህ ክፍሎች ከሌላው ማኅበረሰብ ራሳቸውን አግልለው የሚኖሩ ወላጆች ‘ሂኪኮሞሪ’ ይባላሉ። ሂኪኮሞሪ በጃፓን በ1990ዎቹ በታየው እና ታዳጊዎች እና ወጣቶች በአስከፊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ከማኅበረሰቡ መነጠላቸውን ተከትሎ የተፈጠረ ቃል ነው። ትርጉሙም ራስን መነጠል ወይም ማግለል እንደማለት ነው።

በእነዚህ ራስን የማግለያ ቦታዎች ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ወላጆች ለ13 ሳምንታት የሚቆይ የወላጆች የትምህርት ፕሮግራም ላይ እየተሳተፉ ነው።

ፕሮግራሙ መንግሥታዊ ባልሆኑት የኮሪያ ወጣቶች ፋውንዴሽን እና ብሉ ዌል የማገገሚያ ማዕከል ይደገፋል።

የፕሮግራሙ ዓላማም ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በተሻለ መልኩ እንዴት መነጋገር እንደሚችሉ ማስተማር ነው።

የጂን ያንግ ሄ ልጅ ላለፉት ሦስት ዓመታት በመኝታ ክፍሉ ራሱን አግልሎ ነው የተቀመጠው።

ጂን [ስሟ የተለወጠ] በማግለያ ክፍሉ ጊዜ ማሳለፍ ከጀመረች ወዲህ የስሜት እስረኛ የሆነውን የ24 ዓመት ልጇን በተወሰነ መልኩም ቢሆን መረዳት ችላለች።

“ልጄ እንዲህ እንዲሆን ምን ስህተት እንደፈፀምኩ አስብ ነበር። ስለ እርሱ ማሰቡም ይረብሸኛል” ስትል የ50 ዓመቷ ጂን ተናግራለች።

ሆኖም “ይህንን ሃሳቤን መግለጽ ከጀመርኩ ወዲህ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ግልጽ እየሆነልኝ መጥቷል” ብላለች።

ጂን እንደምትለው ልጇ ልዩ ተሰጥኦ ነበረው። እርሷ እና የልጇ አባት ከእርሱ ብዙ ይጠብቁ ነበር።

ሆኖም ብዙ ጊዜ ይታመም ነበር። ጓደኝነት ለመመሥረት ይቸገር የነበረ ሲሆን፣ ቀስ በቀስም የምግብ ፍላጎቱን እያጣ መጣ። ይህም ትምህርቱን እንዳይከታተል እንቅፋት ሆነበት።

ልጇ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ ለሦስት ወር ያህል ደኅና ይመስል ነበር። አንድ ቀን ግን ሙሉ በሙሉ ከትምህር ቤት በመቅረት ራሱን አገለለ።

በክፍሉ ውስጥ ተዘግቶ፣ ቆሽሾ፣ ምግብ በሥርዓት መመገብ አቁሞ ማየቷ ልቧን ሰበረው።

ጭንቀት፣ ከቤተሰብ እና ከጓደኞቹ ጋር ግንኙነት ለመመሥረት መቸገሩ እንዲሁም በአንድ ከፍተኛ ዩኒቨርሲቲ ተቀባይነት አለማግኘቱ በልጇ ጤና ላይ እክል ፈጥሮበት ሊሆን እንደሚችል ብትገምትም፣ ምን እንዳጋጠመው ግን ሊነግራት አልፈለገም ነበር።

በክፍል ውስጥ ብቻውን አንገቱን ደፍቶ የተቀመጠ ወጣት
የምስሉ መግለጫ, 'ሂኪኮሞሪ' ጃፓንኛ ቃል ሲሆን ራስን መነጠል ወይም ማግለል እንደማለት ነው። (ከክምችት የተገኘ ምስል)

ጂን ወደ ደስታ ማዕከሉ (ሃፒነስ ፋክተሪ) ከገባች በኋላ በሌሎች ራሳቸውን ባገለሉ ወጣቶች የተጻፉ ማስታወሻዎችን አንብባለች።

“ልጄ ብዙ ስለማያወራ ምን እንደሚያስብ እና በአዕምሮው ውስጥ ምን እንዳለ አላውቅም ነበር” ብላለች።

ካነበበቻቸው ማስታወሻዎችም ልጇ ማንም ሊረዳው እንማይችል በማሰብ በዝምታ ውስጥ ራሱን እየጠበቀ እንደነበር መረዳት እንደቻለች ትናገራለች።

ፓርክ ሃን ሲልም [ስሟ ተለወጠ] ወደ ማዕከሉ የገባችው ለ26 ዓመት ልጇ ስትል ነው። ልጇ ከውጪው ዓለም ጋር ግንኙነት ያቋረጠው እና ራሱን የነጠለው ከሰባት ዓመታት በፊት ነበር።

ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከቤት እያመለጠ ይወጣ ነበር፤ አሁን ግን ከክፍሉ የሚወጣው አንዳንዴ ነው።

ፓርክ ልጇን የሥነ ልቦና አማካሪዎች እና ሐኪሞች ጋር ወስዳው ነበር። ሆኖም የታዘዘለትን የአዕምሮ ጤና መድሃኒቶችን አልወስድም ብሎ በቪዲዮ ጌሞች ላይ ጥገኛ ሆነ።

ፓርክ አሁንም ልጇን ለማግኘት ብትቸገርም፣ ፕሮግራሙን መከታተል ከጀመረች ወዲህ ስሜቱን በተሻለ መልኩ መረዳት ችላለች።

“እኔ በምፈልገው መልኩ እንዲሆን ሳላስገድደው የልጄን ሕይወት መቀበል ወሳኝ መሆኑን ተረድቻለሁ” ብላለች።

የጤና እና ደኅንነት ጥበቃ ሚኒስቴር በ2023 በሠራው የዳሰሳ ጥናት ዕድሜያቸው ከ19 እስከ 34 ከሆኑ 15 ሺህ ወጣቶች መካከል ከአምስት በመቶ በላይ የሚሆኑት ራሳቸውን ነጥለው ክፍላቸው ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ይህ ጥናት አጠቃላይ የደቡብ ኮሪያን ሕዝብ የሚወክል ከሆነ 540 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ማለት ነው።

ጥናቱ እንዳመለከተው ለዚህ ለመዳረጋቸው የተጠቀሱት አብዛኞቹ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦

  • ሥራ ማጣት (24.1 በመቶ)፣
  • ከሰዎች ጋር ባለ ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት (23.5 በመቶ)፣
  • የቤተሰብ ችግር ( 12.4 በመቶ) እና
  • የጤና ችግር (12.4) በመቶ ናቸው።
የማብሳያ ክፍል ውስጥ ፊታቸውን አዙረው የተቀመጡ አዛውንት
የምስሉ መግለጫ, ጃፓን የተራዘመ የሂኪኮሞሪ ችግር እያጋጠማት ሲሆን አረጋውያን አዋቂ ልጆቻቸውን ለመርዳት ተገደዋል።(ምስል ከክምችት)

በጃፓን በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ የተከሰተው ራስን የማግለል ማዕበል አዋቂዎች በአረጋውያን ቤተሰቦቻቸው ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ አድርጓል።

አረጋውያኑ በጡረታ ገንዘባቸው እነዚህን አዋቂ ልጆቻቸውን ለመርዳት በሚያደርጉት ጥረትም ለድህነት እና ለድብርት ተጋልጠዋል።

በኪዩንግ ሂ ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ ጥናት (ሶሲዮሎጂ) ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር የሆኑት ጆንግ ጎ ውን እንደሚሉት በተለይ የሥራ ማጣት እና የኢኮኖሚ ችግር ባለበት ወቅት ኮሪያውያን ወላጆች ከልጆቻቸው የተሻለ ሕይወት የመጠበቅ ልማድ በወጣቶች ላይ ጭንቀት እንዲፈጠር አድርጓል።

የልጆች ጥሩ ደረጃ መድረስ የቤተሰብ ስኬት ተደርጎ መቆጠሩም መላ ቤተሰቡን ለቀውስ ዳርጓል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚጠብቁት ቦታ ላይ አለማግኘታቸውን እንደ የአስተዳደግ ውድቀት መቁጠራቸው የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓል።

“በኮሪያ ብዙውን ጊዜ ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር እና ስሜት የሚገልጹት ከቃል ይልቅ በተግባር እና አርአያ በመሆን ነው” ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

ለዚህም ወላጆች ጠንክረው በመሥራት በሚያገኙት ገንዘብ የልጆቻቸውን የትምህርት ክፍያ በመክፈል ኃላፊነታቸውን የመወጣት ባህላቸውን እንደሚያሳዩ በምሳሌነት ያጣቅሳሉ።

አንገቷን ደፍታ የተቀመጠች ወጣት
የምስሉ መግለጫ, አንዳንድ ወላጆች በፕሮግራሙ ላይ መሳተፍ ከጀመሩ ወዲህ ራሳቸውን ያገለሉ ልጆቻቸውን በተሻለ መልኩ መረዳት እንደጀመሩ ተናግረዋል።

የብሉ ዌል የማገገሚያ ማዕከል ዳይሬክተር ኪም ኦክ ራን እንደሚሉትም ወጣቶች ራሳቸውን ያገለሉት በቤተሰብ የአስተዳዳግ ችግር ምክንያት እንደሆነ ከታሰበ፣ በርካታ ወላጆች በዙሪያቸው ካሉ ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ያደርጋቸዋል።

አንዳንዶችም ፍረጃን በመፍራት ስላሉበት ሁኔታ ለቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸው እንኳን ለማውራት ይከብዳቸዋል።

“ጉዳዩን በግልጽ ወደ አደባባይ ማውጣት አለመቻላቸው ደግሞ ወላጆች ራሳቸው እንዲገለሉ ያደርጋቸዋል” ይላሉ ኪም።

“ብዙውን ጊዜ ቤተሰብ ተሰባስቦ በሚያሳልፏቸው የበዓላት ወቅትም መሳተፍ ያቆማሉ” ይላሉ።

እርዳታ ለማግኘት ወደ የደስታ ፋብሪካው (ሃፒነስ ፋክተሪ) የገቡ ወላጆች ልጆቻቸው እንደገና ወደ ጤናማ ሕይወታቸው የሚመለሱበትን ቀን በጉጉት ይጠባበቃሉ።

ልጇ ራሱን ከነጠለበት ክፍል ቢወጣ ምን እንደምትለው የተጠየቀችው ጂን፣ ዐይኖቿ በእንባ ተሞልተው “በጣም ብዙ አሳልፈሃል” እንደምትለው ሳግ እየተናነቃት ተናግራለች።

“በጣም ከባድ ነበር፣ አልነበረም እንዴ? እጠብቅሃለሁ” ብላለች።