በደቡብ ኮሪያ ይፋ የሆነው የዕድሜ አቆጣጠር ሥርዓት የዜጎችን ዕድሜ በአንድ ዓመት ዝቅ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደቡብ ኮሪያውያን ባሕላዊ የዕድሜ አቆጣጠር ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተለመደው ሥርዓት ጋር ለማስማማት ሕግ መተላለፉን ተከትሎ የአገሪቱ ዜጎች ዕድሜ በአንድ ወይም በሁለት ዓመት ዝቅ አለ።
ይህ አዲሱ ሕግ ደቡብ ኮሪያውያን በባሕላዊ የዕድሜ አቆጣጠር ሥርዓታቸው ጽንስ በማሕጸን ውስጥ የቆየበትን ግዜ ከግምት በማስገባት ልጅ ሲወለድ አንድ ዓመት ብሎ መቁጠርን ሰርዟል።
ከዚህ በተጨማሪም ኮሪያውያን በተወለዱበት ቀን ሳይሆን የፈረንጆቹ የመጀመሪያው ወር ‘ጄነዋሪ’ በገባ ቁጥር ዕድሜ ይጨምራሉ።
ይህ ማለት በዓመቱ የመጨረሻ ቀን (ዴሴምበር 31) የተወደለ ጨቅላ በቀጣዩ ቀን (ጄነዋሪ 1) የሁለት ዓመት ልጅ ይሆናል።
ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ-ዬኦል እነዚህ ሁለት የኮሪያውያን የዕድሜ አቆጣጠር ሥርዓቶችን ለመቀየር አጥብቀው ሲወተውቱ ነበር።ፕሬዝዳንቱ ባሕላዊ የዕድሜ አቆጣጠሮቹ “አለስፈላጊ የሆነ ማሕበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ወጪዎችን አስከትሏል” ይላሉ።
ለምሳሌ የመድህን ክፍያን በተመለከተ እንዲሁም መንግሥት ለሚሰጠው ጥቅማ ጥቅም ከእድሜ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ አለመግባባቶች ይፈጠራሉ።
በኮሪያ በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው የእድሜ አቆጣጠር ልጅ ሲወለድ ዕድሜው ‘ዜሮ’ ካለ በኋላ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን አንድ ዓመት ተብሎ መቁጠር ይጀመራል።
አንድ በፈረንጆቹ ጁን 29፣ 2003 የተወለደ ሰው ዛሬ (ጁን 29 2023) በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለመደው የዕድሜ አቆጣጠር 19 ዓመት ይሞላዋል። በሁለቱ የኮሪያ የዕድሜ አቆጣጠር ሥርዓት ግን ዕድሜው 20 እና 21 ነው።
ሃንኩክ የተባለ ጥናት አድርጊ ተቋም ከአጠቃላይ ኮሪያውያን በ75 በመቶ የሚሆኑት እነዚህ ሁለት የዕድሜ አቆጣጠር ሥርዓቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደተለመደው የዕድሜ አቆጣጠር ሥርዓት እንዲቀየር ይደግፋሉ ብሏል።
የአገሪቱ ፓርላማም ባሕላዊ የዕድሜ አቆጣጠር ሥርዓት በኮሪያ ጥቅም ላይ እንዳይውል ከወራት በፊት የሰረዘ ሲሆን ሕጉ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።
ይህ ባሕላዊ የዕድሜ አቆጣጠር በሌሎች የእስያ አገራት ጥቅም ላይ ይውል ነበር።ጃፓን በ1950ዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደተለመደው አቆጣጠር የተመለሰች ሲሆን ሰሜን ኮሪያ ደግሞ ባሕላዊ የዕድሜ አቆጣጠሩን በ1980ዎቹ መጠቀም አቁማለች።












