ወደ ሌላ አገር ለመጓዝ ኢትዮጵያ ውስጥ አስፈላጊ ሰነድ ለማግኘት የተቸገሩ ኤርትራውያን ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, SUPPLIED
በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች በቤተሰብ መቀላቀል መርሃ ግብር አማካይነት በኢትዮጵያ የሚገኙት ልጆቻቸውን እና የትዳር ጓደኞቻቸውን ለመውሰድ ትልቅ ፈተና እየገጠማቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ስደተኞቹ እየገጠማቸው ያለው መዘግየት በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ግልጽ ካልሆኑ ፖሊሲዎች የመነጨ ነው ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
በተለይ በጀርመን የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች መንግሥት ባወጣው ጥብቅ በሆነው ቤተሰብ የመውሰድ መስፈርት ዋነኛ እንቅፋት ሆኖባቸው ቆይቷል።
ይህም ተሰሚነት እንዲያገኝ እና እንዲፈታ ሕጋዊ ቅሬታ በማቅበረ እንዲሁም አደባባይ በመውጣት ተቃውሞን በማደራጀት ጠይቁ ቆይተዋል።
ጥቂቶች ከረዥም ሂደት በኋላ ቪዛ ማግኘት ቢችሉም፣ በሂደቱ ውስጥ በነበሩት ጊዜያት መካከል የተወለዱ ልጆቻቸው ግን ጉዟቸው ተስተጓጉሏል።
አሁን ያሉበት ችግር ከኢትዮጵያ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ከተሰኘው ተቋም ጋር የተያያዘ መሆኑን ይናገራሉ።
በዚህም ሳቢያ ይህ በአገሪቱ ያለውን የስደተኞች ጉዳይ ከሚመለከተው ተቋም የልጆች የልደት መረጃ ማግኘት አለመቻላቸው በዋናነት ይነሳል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ከተሰደዱ የትዳር አጋሮቻቸው እና ልጆቻቸው ጋር ለመቀላቀል ረጅም ሂደት በወሰደው አሰራር ቢሳካላቸውም፣ አስፈላጊው ሰነድ ባለመሟላቱ ምክንያት ግን ጉዳያቸው መደናቀፉን ገልጸዋል።
ይህንንም በተመለከተ ቢቢሲ ትግርኛ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ኃላፊ ከሆኑት አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ምላሽ አላገኘም።
ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀል የሚፈልጉ ኤርትራውያን ስደተኞች “የሚያዳምጠን በማጣታችን ምክንያት ምን ማድረግ እንደምንችል ግራ ገብቶናል” ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።
‘ልጆቼ ከአባታቸው እና ከእናታቸው ተለያዩ’
በጀርመን አገር የሚኖረው ለደኅንነቱ ሲባል ‘ዮናስ’ በሚል ስም የምንጠራው ስደተኛ ሚስቱ እና ልጁ አስፈላጊውን ሰነድ ማግኘት ባለመቻላቸው አዲስ አበባ ውስጥ እየተጉላሉ እንደሆነ ይናገራል።
ከረዥም እና ውስብስብ ሂደት በኋላ ሚስቱ እና ልጆቹ የጀርምን ቪዛ አግኝተዋል፤ ይህም ከቤተሰቡ ጋር ለመቀላቀል የጠበቀውን ረጅም ጊዜ ያሳጥርልኛል ብሎ ተስፋ ሰንቆ ነበር።
ዮናስ ኤርትራ ውስጥ ባለው የብሔራዊ አገልግሎት ምክንያት ከ20 ዓመታት በፊት ካገባት ሚስቱ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ አልቻለም። ከበኩር ልጁ ጋርም ከ10 ዓመታት በኋላ ነበር የተገናኘው።
በስደት ጉዞው ሁሉንም የኤርትራ ጎረቤት አገራት ያዳረሰው ዮናስ፣ በመጨረሻ እንደ በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች የሰሃራ በረሃ በሊቢያ በኩል በማቋረጥ የሜዲትራኒያን ባሕርን ተሻግሮ ወደ አውሮፓ ለመግባት ችሏል።
ምንም እንኳን አደገኛውን ጉዞ ተሻግሮ ደኅንነት ሊሰጠው የሚችል አገር መግባት ቢችልም የቤተሰቡ ሁኔታ እረፍት ሊሰጠው አልቻለም።
ከቤተሰቦቼ የሚገናኝባት ቀን ሲናፍቅ ኖሯል። ዮናስ ከአምስት ዓመት በፊት ያቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል።
“በአውሮፓውያኑ 2018 በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ድንበር ሲከፈት ባለቤቴ ልጆቻችንን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ ገባች” ይላል ዮናስ።
በዚህ ምክንያት ከቤተሰቦቹ ጋር እንደተገኛኘ የሚገልጸው ዮናስ፣ ወደ ጀርመን አገር ተመልሶ ቤተሰቡ የሚወስድበትን ጥያቄ ማቅረቡን ይናገራል።
አራት ዓመታት ከፈጀው ውስብስብ ሂደት በኋላ ሚስቱ እና ልጆቹ ወደ ጀርምን ለመግባት የሚያስችላቸው ቪዛ ተፈቀደላቸው።
ይሁን እንጂ በሂደቱ ውስጥ የተፀነሰው ሕፃን በመሃል ላይ ተወለደ፤ ሕፃኑ ከሌሎች ወንድሞቹ እና እህቶቹ ጋር ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ቪዛ ማግኘት አለበት። ነገር ግን ለቪዛ ከማመልከቱ በፊት የልደት ሰነድ ሊኖረው ይገባል።
ይህ ደግሞ ዋናው ችግር ነው።
የጀርመን ኤምባሲ የስደተኞች ኤጀንሲ ከሚሰጠው የልደት የምስክር ወረቀት ውጪ የሚመጣ የምስክር ወረቀት አይቀበልም።
በ2021 በትግራይ ጦርነት ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቁሞ የነበረው የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ተመላሾች አግልግሎት እንደገና ሥራው ሲጀምር የልደት የምስክር ወረቀት መስጠት አቁሟል። ይህ የሆነበት ምክንያት እስካሁን አልታወቀም።
ስደተኞቹ ግን “ሰነዱን እንዳናወጣ በባለሥልጣናት ተከልክለናል” ይላሉ።
በዚህ ምክንያት ቪዛ የወሰዱ ልጆቹ ወደ ጀርመን ቢመጡም ሚስቱ እና አዲስ የተወለደው ሕፃን ግን አዲስ አበባ ውስጥ ቀርተዋል።
ዮናስ “ልጆቼ ከአባታቸው ጋር ለዓመታት ተለያይተዋል፣ አሁን ደግሞ ከእናታቸው ተለያይተዋል” ይላል።
ተመሳሳይ ፈተና የገጠመው ኤርሚያስ በበኩሉ ኤጀንሲው ጀርመን ኤምባሲ የሚጠይቀውን ሰነድ እንዲሰጠው ከአንድ ዓመት በላይ መጠበቁን ተናግሯል።
“እኔ እና ቤተሰቤ ለ14 ወራት ያህል በማይጨበጥ ተስፋ እና ምኞች ውስጥ እየኖርን ነው። አሁንም ቀጠሮ ከያዙ አንድ ዓመት አልፏል” ይላል።
‘ልጆቻችሁን ትታችሁ መሄድ ትችላላቹ’
ሌላ ሄኖክ የተባለ ስደተኛ በበኩሉ ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገረው ከባለቤቱ ጋር በተመሳሳይ ምክንያት መለያየቱን ይናገራል።
ሊቢያ ሳለ በተለያዩ ሕገወጥ የስደተኛ አሸጋጋሪዎች ታግቶ በሺህ የሚቆጠር ዶላር ከፍሎ ሕይወቱን ያተረፈው ሄኖክ፣ አሁን በጀርመን አገር ከአንድ ልጁ ጋር ይኖራል። ባለቤቱ እና ሌላ ልጁ ግን አዲስ አበባ ሆነው የሚገናኙበትን ቀን እየጠበቁ ነው።
ሚስቱ ነፍሰ ጡር እያለች ቪዛ ብታገኝም የመውለጃ ቀኗ ደርሶ ከኢትዮጵያ ሳትወጣ ቀረች።
ልጁ ከእርሷ ጋር የሚሄድ ከሆነ ቪዛ እና የልደት የምስክር ወረቀት ከኢትዮጵያ የስደተኞች ቢሮ ማግኘት አለበት።
ሆኖም በጀርመን ኤምባሲ የተጠየቁትን ሰነዶች ለማግኘት ብዙ ጊዜ ስለ ወሰደ ባለቤቱ የተሰጣት ቪዛ “በስድስት ወራት ውስጥ ጊዜ አለፈበት” ሲል ይናገራል።
ኤርሚያስ “ዓለም አቀፍ” የልደት ሰርተፍኬት ከሚሰጥበት ተቋም ቢያወጣም በጀርመን ኤምባሲ ተቀባይነት አላገኘም።
የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት የሚገኘው ሰነድ የግድ አስፈላጊ መሆኑ የተገለጸላቸው ቢሆንም ያንን ማግኘት ግን አዳጋች እንደሆነባቸው ይናገራሉ።
“አለዚያ ግን የትዳር አጋሬ በስደት ላይ ሆና የወደለችውን ሕጻን ልጃችንን አዲስ አበባ ትታ ወደ ጀርመን መሄድ እንደምትችል ተነግሮናል” ሲል በተሰበረ ልብ ኤርሚያስ አማራጭ ማጣታቸውን ገልጿል።
ይህ ደግሞ ከእናታቸው እና ከአባታቸው የተነጠሉ ወላጆች እና ልጆች ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫናን እየፈጠረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት መፍትሄ እንዲፈልጉ ይማጸናሉ።
ኤርትራውያን ስደተኞች
በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሕጻናትን ጨምሮ ወደ 200 የሚጠጉት ኤርትራውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በኃይል ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ ከተደረጉ በኋላ ደኅንነታቸው አሳሳቢ ነው ማለቱ ይታወሳል።
ኮሚሽኑ ቅዳሜ ሰኔ 17/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ‘ያለመመለስ መርኅ’ ማንኛውም ሰው ስቃይ፣ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ፣ ኢሰብዓዊ ወይም አዋራጅ አያያዝ አልያም ቅጣት እና ሌላ ጉዳት ሊጠብቀው ወደሚችለው አገር መመለሰን ይከለክላል ብሏል።
ኮሚሽኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ኤርትራውያኑ ኢትዮጵያ ያሉት ‘ሕጋዊ ሳይሆኑ ነው’ በሚል ምክንያት በኃይል ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ያደረጋቸውን ኤርትራውያንን በተመለከተ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ማጣራቱን እንደሚቀጥል አመለክቷል።
ይህን የኢሰመኮ መግለጫ ተከትሎ የኢኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት በሰጠው ምላሽ፣ ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉት ኤርትራውያን በሙሉ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አይደሉም ብሏል።
አገልግሎቱ እሁድ ሰኔ 18/2015 ዓ.ም. ባወጠው መግለጫ የኢሰመኮ መግለጫ “የስደተኞችን እና የጥገኝነት ጠያቂዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚወሰደውን ጥብቅ እርምጃዎች የዘነጋ ነው” ብሎታል።
በ2020 መጨረሻ አካባቢ ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች በኢትዮጵያ ይኖሩ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኤርትራውያን በዋናነት በአገሪቱ ያለውን ገደብ የሌለውን የብሔራዊ አገልግሎት በመሸሽ ወደ ተለያዩ አገራት በስደት ተጉዘዋል።
በዚህም ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ለመሻገር የቻሉ እና ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያገኙ ኤርትራውያን የትዳር አጋሮቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ወዳሉበት አገር ለመውሰድ ጥረት ያደርጋሉ።












