በአዲስ አበባ በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች ታስረው እንደነበር ኢሰመኮ ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, ACT OF SAMARITAN
በአዲስ አበባ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሰነድ የላችሁም በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
ኮሚሽኑ ቀረቡልኝ ያላቸውን አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ ባካሄደው ክትትል በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከታሰሩት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መካከል ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንደዋሉ አመልክቷል።
ጨምሮም ክስ ሳይመሠረትባቸው በእስር የቆዩ መኖራቸውን እና በተለያየ ጊዜ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በአብዛኛው መለቀቃቸውን ኮሚሽኑ ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ትግራይ ውስጥ በሚገኙ ካምፖች ውስጥ ተጠልለው ነበር።
ነገር ግን ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ከፍሎች፣ በተለይም በትካቶች ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ኢሰመኮ እንዳለው ኤርትራውያኑ በዋና ከተማዋ ውስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ምክንያት የሆነው ስደተኛ መሆናችሁን የሚገልጽ የሰነድ ማስረጃ የሌላቸው፣ ከካምፕ ለመውጣት ፈቃድ ሳይኖራቸው ከተማ ውስጥ በመገኘታቸው፣ የሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሥራ ላይ በመሰማራታቸው ነው።
ነገር ግን ስደተኝነታቸውን የሚያሳይ ያልታደሰ መታወቂያ እያላቸው በእስር ላይ የሚገኙ ስደተኞች መኖራቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ በርካታ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከዐሥር ቀናት በላይ በእስር ላይ ቆይተዋል ብሏል።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ከስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መካከል በወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ ሰዎች ካሉ በመደበኛው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ደንቦች መሠረት በጥንቃቄ መለየት አለባቸው ብለዋል።
ይህ በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ያለ ሕግ አግባብ የሚደረግ እስር በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸውን እንደሚገድብ እና ላሉባቸው ችግሮች ዘላቂ መፍትሔን ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ ይጥላል ሲል ኢሰመኮ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ ጉዳዩን በተመለከተ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር ኤርትራውያን ስደተኞችን በተመለከተ ያጋጠመውን ችግር ለማቃለል የሚያስፈልጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን እና በእስር ላይ ያሉትም የሚለቀቁበት አሠራር እንደተዘረጋ እንደተገለጸለት አመልክቷል።
የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች የመታወቂያ እድሳት ወይም የመታወቂያ አገልግሎትን ዘመናዊ ለማድረግ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቋርጦ የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡም አዲስ የምዝገባ ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።
ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት በርካታ ኤርትራውያን ከአገራቸው በመውጣት በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ ካምፖች ተጠልለው የቆዩ ሲሆን፣ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ካምፖቹ በመዘጋታቸው ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተበትነዋል።
እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላም ከወረደ በኋላ በርካታ ኤርትራውያን በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም ሕጋዊ የምዝገባ ሰነድ የሌላቸው እንዳሉ ይነገራል።












