በአዲስ አበባ የጁመዓ ጸሎትን ተከትሎ በተከሰተ “ረብሻ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ” ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, social media
በታላቁ አንዋር መስጂድ የጁመዓ ሶላት ከተጠናቀቀ በኋላ ተነሳ ባለው “ረብሻ የሦስት ሰዎች ሕይወት” ማለፉን የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አርብ ምሽት ባወጣው መግለጫ አሳወቀ።
ግብረ ኃይሉ ረብሻው “ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ” ያላቸው በስም ያልተጠቀሱ ቡድኖች የፀጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የፈጠሩት ነው ሲል ከሷል።
በዚህም ሳቢያ የሦስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ 63 የፖሊስ አባላት ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንዳጋጠማቸው እንዲሁም በንብረት ላይም ግምቱ ያልተወቀ ጉዳት መከሰቱን መግለጫው አመልክቷል።
በታላቁ አንዋር መስጂድና አካባቢው በሙስሊም ምዕመናን እና በፀጥታ ኃይሎችም መካከል በተከሰተው ችግር ጉዳት መድረሱን በአካባቢው የነበሩ ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት እንዳጋጠመው ሁሉ ዛሬም ዐርብ ግንቦት 25/2015 ዓ.ም. ከተካሄደው የጁመዓ ጸሎት በኋላ በአንዋር መስጂድ አካባቢ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን እና የሞቱ እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለታላቁ አንዋር መስጂድ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው የበኒን መስጂድ የጁመዓ ጸሎትን ታድመው የነበሩ ምዕመን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ከጸሎት በኋላ ከአንዋር መስጂድ አካባቢ የተኩስ ድምጽ ሰምተው ወደዚያው ማምራታቸውን ገልጸዋል።
በመንገድ ላይ ሰዎችን ለመበትን የፀጥታ ኃይሎች “ቀጥታ መተኮሳቸውን” ገልጸው፣ በጥይት ተመትተው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
በተተኮሰ ጥይት ሰዎች ከተጎዱ በኋላ በፖሊስ ላይ ድንጋይ መወርወሩን እና ፖሊስም በመንገድ ላይ እና በአቅራቢው ባሉ ሰፈሮች ውስጥ ቤት ለቤት በመግባት ድብደባ መፈጸሙን እኚሁ የዐይን እማኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ክስተቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ “በሸገር ከተማ ስለፈረሱ መስጂዶች ተቃውሞ ለማሰማት የተደረገውን ሙከራ ተከትሎ በተፈጠረ ግጭት እና በተወሰደ የኃይል እርምጃ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ...” ገልጿል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላ በአካባቢው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ እና አንድ በዕለቱ ጁምዓ ጸሎት ላይ የተሳተፉ ግለሰብ የፀጥታ ኃይሎች መተኮሳቸውን እና ድብደባ መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
ሁለቱ ግለሰቦች ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ሰዎችን እንዳዩ እና የሞተ ሰው መኖሩን መስማታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።
ታዋቂው የእስልምና መምህር ኡስታዝ አቡበር አህመድ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ “በንፁሃን ሰጋጆች ላይ በተወሰደው የኃይል እርምጃ በርካታ ሙስሊሞች ላይ ጉዳት ደርሷል” በማለት የሕክምና እርዳታ ማግኘት አለመቻላቸውን አስፍረዋል።
ቢቢሲ በሰው ላይ ስለደረሰ ጉዳት ከፖሊስ እና ከሆስፒታል ምንጮች መረጃ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ነው።
በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኘው የሸገር ከተማ ውስጥ መስጂዶችን ሕገወጥ ተብለው እንዲፈርሱ መደረጋቸውን በመቃወም ተመሳሳይ ተቃውሞ ባሰሙ ምዕመናን ላይ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ባለፈው ሳምንት ሁለት ሰዎች መሞታቸውን እና በርካቶች ላይ ጉዳት መድረሱ መገለጹ ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው የመስጂድ ፈረሳ እንዲቆም፣ የፈረሱትም ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ምክር ቤቱ ሐሙስ ዕለት ባስተላለፈው መልዕክትም በከተማዋ የሚገኙ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች የጁመዓ ጸሎት በሰላም እንዲከናወን ጥሪ አቅርቦ ነበር።
በዚህም የተነሳ በአንዋር መስጂድ ዙሪያ እና በአብዛኛው የመርካቶ አካባቢዎች የሚገኙ የንግድ ተቋማት ችግር ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት ዝግ በመሆናቸው ስፍራው ጭር ብሎ ነበር ያረፈደው።
ከረፋድ ጀምሮም መስጂዶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች በተለይም መሃል መርካቶ በሚገኘው የታላቁ አንዋር መስጂድ አካባቢ እና በዙሪያው ከወትሮው በተለየ በርካታ የፀጥታ ኃይሎች ተሰማርተው ነበር።
ዘወትር ዐርብ የሚደረገው የጁምዓ ጸሎት ከተካሄደ በኋላ ግጭት መከሰቱን እና የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውን ለጸሎት ከስፍራው የነበሩ ምንጭ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ተመሳሳይ ተቃውሞ ከአዲስ አበባ ውጪ በአንዳንድ አካባቢዎች መከሰቱ የተነገረ ሲሆን፣ ከእስልምና ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ወይም ከፖሊስ ስለተከሰተው ችግር እና ስለደረሰ ጉዳት አስካሁን ያሉት ነገር የለም።
ባለፈው ሳምንት ዐርብ እና ዛሬ ለተከሰተው ችግር መነሻ ምክንያቱ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ዙሪያ አዲስ ባቋቋመው የሸገር ከተማ ውስጥ የሚገኙ በርካታ መስጂዶች መፍረሳቸው ነው።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንዳለው በሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ 19 መስጂዶች ሕገወጥ ተብለው የፈረሱ ሲሆን፣ ይህንንም እርምጃ ምክር ቤቱ አውግዟል።












