የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሸገር ከተማ ቢያንስ ሰባት መስጊዶች መፍረሳቸውን ገለጸ

ሼኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ

የፎቶው ባለመብት, ena

የምስሉ መግለጫ, ሼኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በኦሮሚያ ክልል፣ ሸገር ከተማ ቢያንስ ሰባት መስጊዶች መፍረሳቸውን ለቢቢሲ ገለጸ።

ምክር ቤቱ ባለፉት ሳምንታት አዲስ በተቋቋመው በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሚገኘው የሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ ፈረሱ ስላላቸው መስጊዶች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ጽፏል።

ሸገር ከተማ ተብሎ በኦሮሚያ ክልል እንደ አዲስ በተዋቀረው አካባቢ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ከመስጊዶች በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መኖሪያ ቤቶች እየፈረሱ መሆኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ እስካሁን በሸገር ከተማ ውስጥ ቢያንስ ሰባት መስጊዶች መፍረሳቸውን ተናግረዋል።

“እስካሁን በሸገር ከተማ ውስጥ የፈረሱት ቢያንስ ሰባት መስጊዶች ናቸው። እነዚህም በሰበታ አምስት፣ በቡራዩ ሁለት መስጊዶች መፍረሳቸውን ነው ሪፖርት የደረሰኝ” ሲሉ ገልጸዋል።

“ለምን እንደፈረሰ አፍራሹን ክፍል ነው መጠየቅ፣ እኛ ፈረሰብን እንጂ አፍራሽ ክፍልን አግኝተን በምን ምክንያት ፈረሰ ብልን አልጠየቅንም” ሲሉ መስጊዶቹ ለምን እንደፈረሱ ማወቅ እንዳልተቻለ ሼኽ ሐጂ ኢብራሒም አስረድተዋል።

ከፈረሱት መስጊዶች መካከል ቅድመ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው እና በድንገት የፈረሱ እንዳሉ መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ የሸገር ከተማ ባለሥልጣናትን ለማነጋጋር ቢቢሲ በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካም።

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ. ም. በጻፈው ደብዳቤ ላይ በሸገር ከተማ እየፈረሱ ላሉ መስጊዶች አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቋል።

“በቅርቡ በአዲስ መልኩ 'ሸገር ከተማ' ተብሎ በተመሠረተው ከተማ ሕገ ወጥ በሚል በርካታ መስጊዶች በከተማ አስተዳደሩ እየፈረሱብን ይገኛል” ሲል ምክር ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል።

አክሎም “በመስጊዶች ፈረሳ ጉዳይ ላይ ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጋር በስልክ በመነጋገር መፍትሔ ላይ እንደደረስን ብናምንም የከተማ አስተዳደሩ ግን በረመዳን ወር ለጊዜው የመስጊዶች ፈረሳውን እንዲቆም በማድረግ ከረመዳን በኋላ የመስጊዶች ፈረሳ በብዛት ቀጥሏል” በማለት ችግሩን ደብዳቤው ያስረዳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመስጊዶች ፈረሳ ጉዳይ በከተማ አስተዳደሩ “ሕገ ወጥ” ስለተባለ ብቻ በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን “የሕዝበ ሙስሊሙ የሃይማኖት ዋነኛ ኅልውና በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም” በማለት ለኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ደብዳቤ ምክር ቤቱ ቢጽፍም ምላሽ እንዳላገኘም ጠቁሟል።

“ለክልሉ ፕሬዝዳንት ደብዳቤ ከጻፍን እና በጉዳዩ ላይ በአካል በመገናኘት ለመነጋገር ቀጠሮ እየጠየቅን ባለንበት ወቅት መስጊዶች እየፈረሱ መሆኑ የጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮችን እንዲሁም ሕዝበ ሙስሊሙን በእጅጉ አሳዝኗል” ብሏል ደብዳቤው።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ በደብዳቤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመስጊዶች ፈረሳ ጉዳይ “አስቸኳይ መፍትሄ የመስጠት ሙሉ ሥልጣኑ እንዳላቸው” በማመን ለችግሩ “የማያዳግም መፍትሔ” እንዲሰጡ ጠይቋል።

የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ሼኽ ሐጂ ኢብራሒም ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ረመዳን ውስጥ ከሸገር ከንቲባ ጋር በስልክ የመስጊዶች ፈረሳን በተመለከተ ተነጋግረው “መግባባት ላይ” ደርሰው እንደነበር ገልጸዋል።

“በረመዳን ሰው እየጾመ ሰው ታስሮ ነበር። ሰው መታሰር የለበትም። ሰዎችን ያሰራችት መስጊድ ለማፍረስ ነው። መስጊድ ማፍረስም ተገቢ አይደለም” በሚልም መናገራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አያይዘውም “መስጊዳችን ካርታ ላይኖረው ይችላል። እኛ ሙስሊሞች ብዙውን ጊዜ በተጽዕኖ ሥር ነው ያሳለፍነው። . . .የአገራችን ሁለተኛ ዜጋ ተብለን ተፈርጀን የነበርን ነን። አሁን ግን በለውጡ ባገኘነው መብት እና እኩልነት የፈረሰ መስጊድ እንዲተካ” ሲሉ ጥያቄያቸውን ለከንቲባው መግለጻቸውን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ባለድርሻ አካላትን ሳያወያዩ እና ሳይተማመኑ መስጊዶች እንዳይፈርሱ እንዲሁም መስጊዶች የሚፈርሱ ከሆነም ተገቢው አካሄድ መስጊዱ ከመፍረሱ በፊት ምትክ ቦታ ሰጥቶ ሕዝበ ሙስሊሙ መስጊዱን እንዲያዛውር በማድረግ መሆኑን ለከንቲባው ገልጸዋል።

በስልክ ንግግራቸው ወቅት ከንቲባው አወንታዊ ምላሽ እንደሰጡ እና በረመዳን ፈረሳው ቆሞ እንደነበር፣ ረመዳን ከወጣ በኋላ ግን የመስጊዶች ፈረሳው በድጋሚ መጀመሩን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ባለፉት ቀናት በሸገር ከተማ የመስጊዶች መፍረስ በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። ምሥሎች እና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ያጋሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም አሉ።

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሼኽ ሐጂ ኢብራሒም ለኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች ሲያስረዱ “የፈረሱት መስጊዶች በመንግሥት ወጪ ይገንቡልን። መፍረስ ይቁምልን። ሳያማክሩ መስጊድ በማፍረሳቸው ሙስሊሙም ይቅርታ ይጠይቁ” ብለዋል።

በሸገር ከተማ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ያደረጓቸው ሙከራዎች ውጤት ባያስገኙም፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፉት ደብዳቤ መፍትሔ እንደሚሰጣቸው ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

“መስጊድ መጠበቅና ማስጠበቅ ትልቁ ኃላፊነታችን ነው” ያሉት ሼኽ ሐጂ ኢብራጂም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፉት ደብዳቤ መፍትሔ ካልሰጣቸው “ቀጣዩ እርምጃችን በአገሪቷ ሕግ መሠረት መብታችንን ማስከበር ነው” ሲሉም አክለዋል።