‘አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው’ የተባለው ሸገር ከተማ ምን ይዟል?

የፎቶው ባለመብት, obn
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የሸገር ከተማ መመስረት በኦሮሚያ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ እሁድ የካቲት 19/2015 ዓ.ም. የከተማው ምሥረታ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የሸገር ከተማ መመስረት ሁለት ዋነኛ ተልዕኮዎች አሉት ብለዋል።
የመጀመሪያው የሸገር ከተማ ተልዕኮ “አዲስ አበባን መጠበቅ ነው” ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ ‘አዲስ አበባን የመጠበቅ’ ተልዕኮ ዝርዝር ምን እንደሆነ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ሁለተኛው የሸገር ከተማ ተልዕኮ፤ ‘ለኦሮሞ ሕዝብ የምጣኔ ሃብት፣ የማኅበራዊ እና ፖለቲካ ምሶሶ ሆኖ ማገልገል ነው’ ብለዋል።
ሸገር ከተማ በኦሮሚያ ክልል ስር በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ አምስት ከተሞች በመያዝ በ12 ክፍለ ከተሞች የተመሰረተ ነው።
ፕሬዝዳንት ሽመልስ በንግግራቸው ያለፉት ሥርዓቶች በኦሮሞ ሕዝብ ላይ “ከሰማይ በታች ያለደረጉት ነገር የለም፤ ሕዝቡ ግን ችግሩን ተቋቁሞ በድል እዚህ ደርሷል” ካሉ በኋላ፤ የሸገር ከተማ ምሥረታ “ዘመድን አስደስቷል፤ የኦሮሞን ሕዝብ የበታችነት ለሚፈልጉ ደግሞ አስደንግጧል” ብለዋል።
የክልሉ ፕሬዝዳንት፤ የከተማውን መመስረት ተከትሎ ተቃውሞ ቢነሳም፤ “የኦሮሞን ሕዝብ ድል ለአንድ ሴኮንድም ወደ ኋላ መመለስ የሚችል ኃይል የለም” ብለዋል።
አዲስ የተመሰረተው ከተማ ከላይ የተጠቀሱትን ኃላፊነቶች ዓላማ እንዲወጣ የኦሮሚያ ክልል በትኩረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንሚያደርግ የገለጹት ሽመልስ አብዲሳ፤ ለከተማው መመስረት ስኬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አመስግነዋል።
“አገሪቷ በታሪኳ አይታ የማታውቀው ምሳሌ የሚሆን አመራር በመስጠት ለዚህ ከፍተኛ ድል እና ውጤት ያደረሱንን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕምድን ማመስገን እፈልጋለሁ” ብለዋል።
በከተማ ምሥረታ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የመጀመሪያው የሸገር ከተማ ከንቲባ ሆነው የተሾሙት ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው የመሬት አስተዳደርን ማዘመን እና አዋጭነቱን ማሳደግ ነው ብለዋል።
በከተማው ምሥረታ ሥነ ሥርዓት ላይ ከተገኙት የቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንቶች መካከል አንዱ የሆኑት አባዱላ ገመዳ፣ የከተማው መመስረት ከአካባቢው ነዋሪ አልፎ ለሌሎችም ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
“በዚህ በተገኘው ዕድል በመጠቀም ከድህነት መውጣት አለብን። ይህም የወጣቶቻችንን ሥር ፍለጋ መውጣትን ከማስቀረትም በላይ ከሌሎች አካባቢዎች ለሚመጡም ዕድል ይፈጥራል” ብለዋል አባዱላ።
ሸገር ከተማ ምንድነው?
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት የሸገር ከተማ ምሥረታን በማስመልከት ደንብ ቁጥር 233/2015 በማርቀቅ ተግባራዊ አድርጓል።
በዚህ መሠረት በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች፣ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች በአንድ ላይ በመሆን ከተማዋን መሠረተዋል።
ቡራዩ፣ ኮሎቦ፣ ሱሉልታ፣ ለገ ጣፎ-ለገ ዳዲ፣ ገላን እና ሰበታ ከተሞች እንዲሁም በወልመራ፣ ሱሉልታ፣ በረክ፣ አቃቂ እና ሰበታ ሃዋስ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ቀበሌዎች የከተማዋ አካል ሆነዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) ባጸደቀው ደንብ መሠረት ሸገር ከተማ 160 ሺህ ሄክታር የሚሆን የመሬት ይዞታ ያለው ሲሆን፣ እንደ አስፈላጊነቱ ሊሰፋ ወይም ሊጠብ ይችላል።
መቀመጫውን አዲስ አበባ የሚያደርገው ሸገር ከተማ፤ ተጠሪነቱ ለክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ይሆናል።
ድንበሩን በተመለከተ ጨፌው ያጸደቀው ደንብ፤ የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሐምሌ 22/2014 ዓ.ም. በደረሱት ስምምነት ላይ የተመሠረት ይሆናል ይላል።
ሸገር በከተማ፣ በክፍለ ከተማ እና በወረዳ የሚዋቀር ሲሆን፤ ከተማው የከተማ አስተዳደር፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ጨምሮ አስፈላጊ የሆኑ መሥሪያ ቤቶች ይኖሩታል።
ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሠራተኞች አዲስ በተመሰረተው የሸገር ከተማ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች ውስጥ መመደባቸውን አንዳንድ ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የከተማ መመሥረት ይፋ ባደረገው የጨፌው ደንብ ላይ ሸገር ከተማን መመሥረት ያስፈለገው፤ ከተማዋን ለማዘመን፣ ለልማት ሳቢ ለማድረግ እንዲሁም የምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ማዕከል ለማድረግ ያለመ መሆኑን ያትታል።
የሸገር ከተማ መመሥረት ከዚህ ቀደም የነበረውን ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚተካ ይሆናል።












