የኦሮሚያ መስተዳደርን የሰላም ጥሪ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ‘በጥንቃቄ’ እንደሚቀበለው ገለጸ

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ

የፎቶው ባለመብት, obn

የምስሉ መግለጫ, የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ

በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያቀረቡትን የሰላም እና የእርቅ ጥሪ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በአውንታዊ እርምጃነት ነገር ግን በጥንቃቄ እንደሚቀበለው ገለጸ።

በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርገው መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የእርቅ ጥሪው በክልሉ ሰላም ለማምጣት መልካም እርምጃ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የክልሉ መንግሥትን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ለምክር ቤቱ አርብ የካቲት 10/2015 ዓ.ም. ሪፖርት ባቀረቡት ወቅት ነው “ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ እንደ ሸኔ ያሉ ኃይሎችን በንግግር ወደ እርቅ እንዲመጡ” ጥሪ ያቀረቡት።

አቶ ሽመልስ በአዳማ ከተማ በተካሄደው የኦሮሚያ ምክር ቤት (ጨፌ) መደበኛ ጉባኤ ላይ በክልሉ ለሚካሄደው የልማት ሥራ ሰላም ወሳኝ መሆኑንና በክልሉ ውስጥ ሰላም ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ በመጥቀስ ለዚህም “ኦነግ ሸኔ በእርቅ ወደ ሰላማዊ መንገድ ተመልሶ እንዲገባ” እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

ይህንን ጥሪ ተከትሎ የቡድኑ ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ “ወደ ድርድር በመግባት ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ መፈለግ ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን ወደ ውይይቱ የምንገባበት መንገድ መታየት አለበት” ብለዋል።

ድርጅቱ ይህንን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ቡድኑ በኢትዮጵያ ላለው ውስብስብ የፖለቲካ ችግር በድርድር ላይ የተመሠረተ ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ሂደት እንደሚያስፈልግ ስለሚያምን፣ በኦሮሚያ ያለውን ችግር በሰላም ለመፍታት የቀረበውን ጥሪ እንደሚቀበለው ገልጿል።

ነገር ግን ከዚህ በፊት በመንግሥት እና በቡድኑ መካከል የተደረጉት ስምምነቶች የከሸፉት ሦስተኛ ወገን በሌለበት በመካሄዳቸው መሆኑን አመልክቶ፣ ገለልተኛ አሸማጋይ በሂደቱ ውስጥ እንደሚያስፈልግ ቃል አቀባዩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የቀረበውን የሰላም ጥሪ “ግልጽነት የሚጎድለው ነው” ቢልም ነገር ግን በቀጣይ ቀናት ዝርዝር ሁኔታዎች ይወጣሉ ብሎ እንደሚጠብቅ አመልክቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ድርጅቱ የሚያደረገው ንግግር የተሳካ እንዲሆን ገለልተኛ የሦስተኛ ወገን የውጭ አሸማጋዮች እንዲኖሩ እንደሚፈለግ ገልጾ፣ ይህ የማይሆን ከሆነ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር መካከል የተደረሰው ‘የአሥመራው ስምምነት’ አይነት እንቅፋት ያጋጥመዋል ሲል አሳስቧል።

በተጨማሪም በሰላም ሂደቱ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት መሳተፉ መልካም መሆኑን ቢቀበልም፣ ዋነኛው መሪ መሆን የለበት የፌደራል መንግሥቱ እንዲሆን እንደሚፈልግ ምክንያቶቹን ጠቅሶ ጠይቋል።

የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተለያዩ ጊዜያት በሰጡት መግለጫ የቡድኑ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ጥሪ ሲያርቡ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት ለምክር ቤት ባደረጉት ንግግር የሰላም ሃሳቡን አንስተዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም ለንግግር ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ ሊፈጸሙ ይገባሉ ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በቅርቡ ይፋ ባደረገው ማኒፌስቶው ላይ ማቅረቡ ይታወሳል።

በአማጺ ቡድኑ እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በሚደረጉ ግጭቶች እና በሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ ባለፉት አራት ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን መንግሥት ‘ሸኔ’ ሲል የሚጠራው ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት ገደማ በሽብርተኛነት በፌደራል መንግሥቱ ፓርላማ ተሰይሞ ሕገወጥ ቡድን ሆኗል።

በምዕራብ እና በደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሰው መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የተባለው ቡድን በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጽማቸው ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ቡድኑ ግን ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ እንደማያደርግ ያስተባብላል።

በተለይ በምዕራብ የኦሮሚያ ክፍል ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀሰው ቡድን ሰላማዊ ነዋሪዎችን፣ የመንግሥት ኃላፊዎች እና ሠራተኞችን በማጥቃት እና በመግደል እንዲሁም ባንኮችን ጨምሮ በተቋማት ላይ ዘረፋ እና እገታዎችን በመፈጸም ሲከሰስ ቆይቷል።