በምሥራቅ ወለጋ በተፈናቃዮች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 50 ሰዎች ተገደሉ - ኢሰመኮ

ተፈናቃዮች የተጠለሉበት ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, ehrc

የምስሉ መግለጫ, ተፈናቃዮች የተጠለሉበት ስፍራ

በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ አኖ ከተማ በአካባቢው ባለ ግጭት ሳቢያ ተፈናቅለው በነበሩ ተፈናቃዮች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያነስ 50 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ጥቃቱን በአኖ ከተማ የፈጸሙት ከሁለት ሳምንት በፊት በጥር 25/2015 ዓ.ም. ሲሆን፣ በዋናነት ኢላማ ያደረጉትም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን መሆኑን ገልጿል።

በጥቃቱ ዕለት ከንጋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው የወታደር ልብስ የለበሱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነግ-ሸኔ) አባላት መሆናቸው በነዋሪዎች የተገለጹ ታጣቂዎች በሦስት አቅጣጫ ወደ አኖ ከተማ በመግባት ጥቃት እንደከፈቱ እና “የሲቪል ሰዎች ግድያ እና የአካል ጉዳት፣ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት መድረሱ” ከነዋሪዎች መረዳቱን አመልክቷል።

ኢሰመኮ የዐይን ምስክሮችን፣ የመንግሥት አካላትን እና የጥቃቱ ተጎጂ ቤተሰቦችን በማነጋገር ባደረገው ምርመራ፣ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና የታጣቂዎቹ ዋነኛ ኢላማ የነበሩት ከጎቡ ሰዮ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ተፈናቅለው በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዮች መሆናቸውን ለመረዳት ችሏል።

በጥቃቱም አንድ የክልል የሥራ ኃላፊ ከነሾፌሩ፣ የከተማ ፖሊስ እና የቀበሌ ሚሊሻ አባላትን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሰዎች ተገድለዋል።

ከእነዚም መካከል 42ቱ የጥቃቱ ሰለባዎች በተፈናቃዮች የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እና ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩ ተፈናቃዮች እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ የተባሉ ነዋሪዎች ሲሆኑ፣ ከሟቾች መካከልም አራት ሴቶች እና ሦስት ሕፃናት ይገኙባቸዋል።

በተለይ ታጣቂዎቹ በከተማዋ ‘ሰኞ ገበያ’ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ተፈናቃዮችን “ቤት ለቤት እየዞሩ በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ለይተው ገድለዋል” ሲል የኢሰመኮ መግለጫ ጠቅሷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ የሚገኝ እና ቀደም ሲል የቀበሌ አስተዳደር ንብረት የነበረና ወደ አረጋውያን፣ ሴቶች እና ሕፃናት ተፈናቃዮች መጠለያነት በተቀየረ ግቢ ውስጥ በመግባት በፈጸሙት ጥቃት፤ “ማምለጥ ያልቻሉ ወንድ ተፈናቃዮችን መርጠው የገደሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከተገደሉ በኋላ ሬሳቸው በእሳት የተቃጠለ ሰዎች” መኖራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

በጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪም ስምንት ሰዎች ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው እና በከተማዋ የሚገኙ የግለሰቦች የንግድ መደብሮች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አኖ ቅርንጫፍ እና ሌሎች ተቋማት መጠነ ሰፊ ዘረፋ እና ውድመት ተፈጽሞባቸዋል።

ታጣቂዎቹ ቀደም ባለ አለመረጋጋት ምክንያት ተፈናቅለው በከተማዋ የነበሩ ተፈናቃዮችን ኢላማ በማድረጋቸው ምክንያት የቀሩት ተፈናቃዮች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መበተናቸውን እና መጠለያውም በጊዜያዊነት ተዘግቶ እንደነበር ኢሰመኮ ገልጿል።

ኮሚሽኑ ይህንን ጥቃት በተመለከተ እንዳለው ይህ “ተፈናቃዮችን ኢላማ በማድረግ የተፈጸመው ጥቃት፣ በክልሉ በቀጠለው ግጭት ምክንያት የሲቪል ሰዎች ደኅንነት የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል” ብሏል።

ጨምሮም መንግሥት የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት ከማስጠበቅ በተጨማሪ ለግጭቱ ዘላቂ እና ሰላማዊ መፍትሔ ለማበጀት ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ አለበት በማለት አሳስቧል።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአካባቢው በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ከጎቡ ሰዮ ወረዳ 11 ቀበሌዎች እና ከሁለት የአዋሳኝ ወረዳ ቀበሌዎች በድምሩ ከ13 ቀበሌዎች ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ኢሰመኮ አስታውሷል።

ተፈናቃዮቹም በአኖ ከተማ በመጠለያ ውስጥ እንዲሁም ከመጠለያ ውጭ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ 10,800 የሚሆኑ ሰዎች የሚገኙ መረጃ እንዳለው አመልክቷል።

በምዕራብ እና በደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሰው መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የተባለው ቡድን በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጽማቸው ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ቡድኑ ግን ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ እንደማያደርግ ያስተባብላል።

በተለይ በምዕራብ የኦሮሚያ ክፍል ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀሰው ቡድን ሰላማዊ ነዋሪዎችን፣ የመንግሥት ኃላፊዎች እና ሠራተኞችን በማጥቃት እና በመግለደል እንዲሁም ባንኮችን ጨምሮ በተቋማት ላይ ዘረፋ እና እገታዎችን በመፈጸም ሲከሰስ ቆይቷል።

የመንግሥት ሸኔ የሚለው ኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር ቡድንነት የተፈረጀ መሆኑ ይታወቃል።