በሕንድ በደረሰ የባቡር አደጋ ከ260 በላይ ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሕንድ ምሥራቃዊ ኦዲሻ ግዛት፣ ባላሶሬ በሚባል አውራጃ ሁለት በተለያየ መስመር የሚዘወሩ ባቡሮች ተላትመው 260 በላይ ተሳፋሪዎች ሲሞቱ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደረሰባቸው።
አደጋውን ተከትሎ 200 አምቡላንሶች ወደ ስፍራው የተንቀሳቀሱ ሲሆን ከአደጋው የተረፉ ተሳፋሪዎች የከፋ ጉዳት የደረሰባቸውን ሌሎችን ለማዳን ሲረባረቡ ታይተዋል።
አደጋው የደረሰው ትናንት ዐርብ ሲሆን፣ አንድ የመንገደኞች ባቡር መስመሩን ስቶ ከወጣ በኋላ በሌላ ከተቃራኒ አቅጣጫ እየከነፈ ይመጣ በነበረ ባቡር መገጨቱን ተከትሎ ነው በርካታ ሰዎች ሊጎዱ የቻሉት።
ይህ አደጋ በሕንድ በዚህ 21ኛው ክፍለ ዘመን ከደረሱ የባቡር አደጋዎች የከፋው ነው ተብሏል።
የአካባቢው ባለሥልጣናት የሟቾች ቁጥር አሁን ካለበት በብዙ ሊያሻቅብ እንደሚችል ሰግተዋል።
የሕንድ የባቡር አስተዳደር እንዳለው በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ኮሮማንዴል ኤክስፕረስ እና ሆውራሽ ሱፐርፋስት ኤክስፕረስ ባቡሮች ናቸው።
የሕንድ አገር ውስጥ ሚኒስትር አሚት ሻህ አደጋው ልብ የሚሰብር ብለውታል።
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንዳ ሞዲ በአደጋው ማዘናቸውን ለሟች ቤተሰብ መጽናናትን ተመኝተዋል።
አንድ ከአደጋው የተረፈ ግለሰብ ለሚዲያ ሲናገር ግጭቱን ተከትሎ ‘ከ10-15 ሰዎች ላዬ ላይ ተጭነውኝ ነበር’ ሲል የተፈጠረውን ትርምስ አስረድቷል።
“እጄ መሰበሩን ተረዳሁ፤ አንገቴም አካባቢ ሕመም ይሰማኝ ነበር። ዞር ስል እግሩ የተቆረጠ፤ እጁ የተቆረጠ ብዙ ሰው አየሁ፤ ዘግናኝ ነበር” ብሏል።
ረዥም የባቡር ፉርጎዎች ያሏቸው ከሻሊማር ወደ ቼናይ ይጓዙ የነበሩ የኮሮማንዴል ኤክስፕረስ ባቡሮች ከሌላ አቅጣጫ ከሚመጣ ባቡር ጋር የተላተሙት በአገሬው አቆጣጠር ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ ነው።
በተቀራኒ አቅጣጫ የሚጓዙት ባቡሮችና ፉርጎዎቻቸው ከተላተሙ በኋላ በአካባቢው የነበሩ የቆሙ ባቡሮች ሳይቀር የአደጋው ዳፋ ለእነርሱም ተርፏል።
በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችና የግል አውቶቡስ ባለንብረቶች ተጎጂዎችን ወደ ሆስፒታል በማመላለስ እገዛ ሲሰጡ ታይተዋል።
ሕንድ በዓለም ላይ ሰፊ፣ ረዥም እና ጥልፍልፍ የባቡር መስመሮች ያሏት አገር ስትሆን የባቡር መስመሮች ከፍተኛ ወጪ ወጥቶ በተደጋጋሚ ዕድሳት ቢደረግላቸውም እንዲህ ዓይነት አደጋዎች የተለመዱ ናቸው።
በሕንድ የከፋ የተባለው የባቡር አደጋ የደረሰው በነርሱ አቆጣጠር በ1981 ዓ/ም ሲሆን በወቅቱ አንድ ባቡር በአውሎ ንፋስ ከሃዲዱ ተሽቀንጥሮ ፉርጎዎቹም ወደ ወንዝ መወርወራቸውን ተከትሎ 800 ተሳፋሪዎች አልቀው ነበር።












