አሜሪካና ዩኬ በኤርትራ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ አሳስቦናል አሉ

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት 53ኛው ጉባኤ በጄኔብ በተጀመረ ወቅት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት 53ኛው ጉባኤ በጄኔብ በተጀመረ ወቅት።

ዩናይትድ ስቴትስና ዩናይትድ ኪንግደም በኤርትራ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ አሳስቦናል አሉ።

አገራቱ የኤርትራ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው የገለጡት በተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት 53ኛው ጉባኤ በጄኔብ በተካሄደ ወቅት ነው።

የአሜሪካ ተወካይ የሆኑት ኬሊ ቢሊንግስሊ “የአሜሪካ መንግሥት ዜጎቹን እየበደሉ መሆኑን አሜሪካ አጥብቃ ታወግዛለች” ብለዋል።

ተወካይዋ እንዳሉት “የኤርትራ መንግሥት ሕዝቡን እየበደለ ነው፣ አልፎም ሐሳባቸውንና እምነታቸውን በነፃ የሚያራምዱ ዜጎችን እየጨቆ ነው።”

ቢሊንግስሊ አክለው አሜሪካ የኤርትራን ብሔራዊ አገልግሎት ሥርዓት እንደምትቃወም ገልጠዋል።

በቅርቡ የኤርትራ መንግሥት የሱዳን ግጭትን ተከትሎ ከአገር ወጥተው የነበሩ ኤርትራዊያንን በግዴታ ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉ ተዘግቧል።

ይህ ጉዳይ “እጅግ አሳሳቢ” ነው ያለው የአሜሪካ መንግሥት የፕሬዝደንት ኢሳይያስ አስተዳደር ይህን “ሕጋዊነት የሌለው” ተግባር እንዲገታ ጥሪ አቅርቧል።

ተወካይዋ በመልዕክታቸው የኤርትራ ወታደሮች ሰሜን ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ማድረስ እንዲያቆሙ ተናግረዋል።

“የኤርትራ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያ ያደረሱት ጥፋት እጅግ ያሳስበናል። ወታደሮቹ የጦር ወንጀልና ሰብዓዊነት ላይ ወንጀል ፈፅመዋል። ይህን ጥፋት የፈፀሙ ለሕግ እንዲቀርቡ ግድ ይላል።”

በተመሳሳይ የዩናይትድ ኪንግደም በኤርትራ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ እንዳሳሰባት በተወካይዋ አማካይነት ገልጣለች።

የዩኬ ሰብዓዊ መብት አምበሳደር ሪታ ፍሬንች የኤርትራ ብሔራዊ አገልግሎት “ለውጥ ያሻዋል” ብለዋል።

ብሔራዊ አገልግሎቱ “የበርካታ ኤርትራዊያንን በተለይ ደግሞ የወጣቶችን ሕይወት እያቃወሰ ነው። በርካቶች ሃገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል” ይላሉ ተወካይዋ።

አምባሳደር ፍሬንች አክለው የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንዲወጡ ሃገራቸው ጫና ማሳደሯን እንደምትቀጥል ገልጠዋል።

የኤርትራ መንግሥት ኃይሎች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በፈፀሟቸው ጥሰቶች ተጠያቂ እንዲሆኑም ዩኬ መወትወቷን ትቀጥላለች ይላሉ ተወካይዋ።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባል የሆነችው ዩኬ፤ ኤርትራ ከሰብዓዊ መብት እንድትቆጠብ አጥብቃ እንደምትጠይቅ አምባሳደር ፍሬንች ተናግረዋል።

በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የምትመራው ኤርትራ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥስት ስትወቀስ ቆይታለች።

በሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርትነት ተሳታፊ የነበረችው ኤርትራ ጦሯን ወደ ትግራይ በማዝመት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከባድ ጥሰት ስለመፈጸሙ ሪፖርት ሲደረግ ቆይቷል።

ጦርነቱን ለማስቆም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና ህወሓት በፈረሙት የሰላም ስምምነት የውጭ ኃይሎች ከትግራይ እንደሚወጡ የተደነገገ ቢሆንም አሁንም የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል እንደሚገኙ ሪፖርት እየተደረገ ነው።