95 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ ክፈል የተባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 180 ሚሊዮን ዶላር ተይዞብኛል አለ

የፎቶው ባለመብት, @flyethiopian
ለተለያዩ አየር መንገዶች 95 ሚሊዮን ዶላር የተከማቸ ገንዘብ እንዲፈል የተጠየቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተለያዩ አገራት ያልሰበሰበው 180 ሚሊዮን ዶላር እንዳለው ገለጸ።
ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የኢትዮጵያ መንግሥት የያዘውን የሌሎች አየር መንገዶች 95 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በፍጥነት እንዲለቅ ጠይቋል።
የነገር ግን ኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ በሌሎች አገራት ውስጥ ተወዝፎ የሚገኝ ከ180 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያልተለቀቀለት ገንዘብ እንዳለው ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው “እስከ ዛሬ ድረስ በሌሎች አገራት ማንቀሳቀስ ያልቻልነው 180 ሚሊዮን ዶላር ውዝፍ ገንዘብ አለን። ውዝፉን ገንዘብ ማንቀሳቀስ ለአየር መንገዱ ከባድ ፈተና መሆኑ ቀጥሏል” ማለታቸውን መግለጫው ጠቅሷል።
ባለፉት ቀናት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሌሎች አገራት ያለውን ገንዘብ ማስለቀቅ አልቻለም የሚሉ ዘገባዎች በስፋት ሲወጡ ቆይቷል።
በእነዚህ ዘገባዎች አየር መንገዱ ውዝፍ ገንዘቡ ተከማችቶ የሚገኘው እንደ ናይጄሪያ እና ኤርትራ ባሉ አገራት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ አየር መንገዱ ግን የየትኛዎቹን አየር መንገዶች ገንዘብ ይዞ እንዳለ ግልጽ አልሆነም።
ወደ 300 የሚጠጉ አየር መንገዶችን የሚያቅፈው ማኅበር ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የአየር ትራንስፖርት ግንኙነቷ የመቋረጥ ስጋት ላይ እንዳይወድቅ አገሪቱ በፍጥነት ውዝፉን 95 ሚሊዮን ዶላር መክፈል አለባት ብሏል።
ማኅበሩ የሌሎች አየር መንገዶች ገንዘብን መልቀቅ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተረጋገጠ ነው ያለ ሲሆን፤ ዓለማችንን በአየር ትራንስፖርት ለማገናኘት ይህ ስምምነት መከበር አለበት ብሏል።
የማኅበሩ ዳይሬክተር ጄኔራል ዊሊ ዋልሽ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ማዕከላዊ ባንኩ ለአቪየሽን ኢንዱስትሪው አነስተኛ ዶላር መመደባቸው 95 ሚሊዮን ዶላሩ ከአገር እንዳይወጣ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
“ይህ ትክክለኛ ያልሆነ መልዕክት ያስተላልፋል” ያሉት ዊል ዋልሽ፤ የኢትዮጵያን እድገት እየደገፈ የሚገኘው አየር መንገድ የሚያመጣው የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጥቅሞች አደጋ ላይ ይጥላል ብለዋል።
ስለዚህም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመከተል ችግሩን በፍጥነት የምትፈታበት ሰዓት ነው ብለዋል ዳይሬክተር ጄኔራሉ።
ማኅበሩ ኢትዮጵያ ያለባትን እዳ እንድትከፍል ከመጠየቁ ውጪ፣ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በሌሎች አገራት ውስጥ አለኝ የምትለውን ውዝፍ ገንዘብ በተመለከተ ያለው ነገር የለም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕድገት
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው የሚመሩት ተቋም ባለፉት 12 ወራት ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
“የአሁኑ አፈጻጸማችን፤ በሁሉም መለኪያዎች፤ ስኬታችን ተጠንክሮ እንደሚቀጥል ያመላክታሉ። ከወረርሽኙ ተጽእኖ በጥሩ ሁኔታ አገግመናል። በዚህ የበጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ 1.6 ቢሊዮን ዶላር እናስገባለን ብለን እንጠብቃለን፤ ይህ ካለፈው ዓመት አፈጻጸማችን ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ዕድገት ነው” ብለዋል።
አየር መንገዱ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ55 በመቶ ዕድገት በማምጣት በዚህ ዓመት መጨረሻ 13.7 ሚሊዮን መንገደኞችን እንደሚያጓጉዝ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱን እየፈተኑ ካሉ ነገሮች መካከል በሌሎች አገራት ተከማችቶ የሚገኝ ገንዘብ አለመለቀቁ አንዱ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀዳሚው እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ የአየር ትራንስፖርት አገለግሎት ሰጪ ግዙፍ ተቋም ሲሆን፣ አየር መንገዱ 133 የመንገደኞች እና የጭነት መዳረሻዎች አሉት።












