‘አወዛጋቢው’ አንድሪው ቴት በመድፈር እና በሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር ተከሰሰ

አንድሪው [በስተቀኝ] እና ወንድሙ ትሪታን ቴት

የፎቶው ባለመብት, EPA

በሮማኒያ በቁም እሥር የሚገኘው አወዛጋቢው ተፅዕኖ ፈጣሪ አንድሪው ቴት ክስ ተመሰረተበት።

የክስ መዝገቡ ግለሰቡ፤ በመድፈር ወንጀል፣ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሴቶች ላይ ወሲባዊ ብዝበዛ የሚያደርስ ቡድን በመመሥረት እንደተከሰሰ ያሳያል።

ወንድሙ ትሪስታን ቴትና ሌሎች ሁለት ግብረ አበሮቻቸውም እንዲሁም ክስ ቀርቦባቸዋል።

ሁሉም ከደሙ ንፅሕ ነን ይላሉ።

ሁለቱ ወንድማማቾች ባለፈው ታኅሣሥ ቡካሬስት ከሚገኘው ቤታቸው ታፍሰው መወሰዳቸው ይታወሳል።

ወርሃ መጋቢት ሮማኒያዊው ዳኛ የቤት ውስጥ እሥር እንዲሆንላቸው ወስነው ነበር።

የቡካሬስት ፍርድ ቤት የክስ መዝገብ እንደሚያሳየው አራቱ ተከሳሾች የወንጀል ቡድን አቋቁመው ሮማኒያ ውስጥ ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር ሲከውኑ ነበር።

ቡድኑ ከሮማኒያ አልፎ በዩናይትድ ስቴትስና በዩናይትድ ኪንግደምም ይንቀሳቀሳል ይላል የክስ መዝገቡ።

ሰነዱ እንደሚገልጠው 7 ስማቸው የተጠቀሰ ሴቶች በወንድማማቾቹ ሐሰተኛ የፍቅርና ትዳር ቃል ተማለው ቡድኑን ተቀላቅለዋል።

የወንድማማቾቹ የወንጀል ቡድን ሰለባ ናቸው የተባሉት ሰዎች ሮማኒያ ውስጥ ወደ ሚገኝ አንድ ሥፍራ ተወስደው ያለፈቃዳቸው ቆይተዋል ይላል።

የገቡ የወጡበት ክትትል እየተደረገበት አልፎም በግድ ዕዳ ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸው ሰነዱ ይገልጣል።

ተከሳሾቹ ሴቶቹን በግድ በወሲብ ፊልም እንዲሳተፉ አድርገዋቸው ቆይቶ ይህ ፊልም በማሕበራዊ ሚድያ እንዲሰራጭ ሆኗልም ይላል ክሱ።

ከተከሳሾቹ መካከል አንዱ አንዲት ሴትን በፈረንጆቹ መጋቢት 2022 ሁለት ጊዜ ደፍሯታል ሲል ክሱ ያሳያል።

የፍርድ ሂደቱ ወዲያው ይጀምራል ተብሎ አይጠበቅም። እንዲያውም ዓመታት ሊፈጅ ይችላል የሚል ግምት አለ።

የቴት ወንድማማቾች የሚድያ ቡድን ይህንን ክስ ተከትሎ መግለጫ ለቋል።

“ይህ ዜና እንደሚሰማ ምንም ባያጠራጥርም፤ ወንድማማቾቹ ንፁሕ መሆናቸውን ማሳያ በመሆኑ በፀጋ እንቀበለዋለን” ይላል።

አክሎ “ክሱ ያለንን እጅጉን የተደራጀ ማስረጃ ተጠቅመን የወንድማማቾቹን ንፅሕና እናስጠብቃለን” ብሏል።

ከዚህ ክስ በተጨማሪ በሕገ-ወጥ ገንዘብ ማስተላለፍና ሕፃናትን በማዘዋወር ወንጀል የተከሰሱበት መዝገብ አለ።

በኪክቦክስ ስፖርት እውቅናን ያተረፈው ብሪታኒያዊ አሜሪካዊው አንድሪው ቴት ከቢግ ብራዘር የቴሌቪዥን ፕሮግራም አንዲት ሴትን ሲያጠቃ በመታየቱ መባረሩ ይታወሳል።

ከዚህ ቀጥሎ ወደ በይነ መረብ በማቅናት ለወጣት ወንዶች ‘ምክር የሚለግስ’ ንግግር ማሰማት ያዘ።

ነገር ግን ሴቶች ለሚደርስባቸው ወሲባዊ ጥቃት ‘የተወሰነ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል’ ማለቱን ተከትሎ ከትዊተር ተባሮ ነበር።

ምንም እንኳ ከበርካታ ማሕበራዊ ሚድያ አውታሮች ቢባረርም እውቅናው ግን ይልቁን እየናኘ መጥቷል።

አንድሪው ቴት ማነው?

ሙሉ የመዝገብ ስሙ ኢሞሪይ አንድሩ ቴት ነው። ቴት ከአሜሪካዊ አባት እና ከብሪታኒያዊት እናቱ በአሜሪካ ቺካጎ ግዛት ነው የተወለደው። ኮከብ የቼዝ ተጫዋች የሆኑት አባቱ ከእናቱ ጋር የተዋወቁት ለአሜሪካ አየር ኃይል በብሪታኒያ ውስጥ ሲያገለግሉ ነበር።

አባት እና እናት እስከተፋቱበት ጊዜ ድረስ ቴት ያደገው አሜሪካ ውስጥ ነበር። ከፍቺው በኋላ ከወላጅ እናቱ ጋር ወደ ብረታኒያ ተመለሰ።

ከአምስት ዓመት በፊት ደግሞ ጠቅልሎ ወደ አውሮፓዊቷ ሩማኒያ ገብቷል። ቴት ኑሮውን ወደ ሮማኒያ እንዲያዞር ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ በአገሪቱ ከአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ማምለጥ ቀላል ነው ብሎ ስለሚያምን መሆኑን በራሱ አንደበት ተናግሯል።

የቴት የልጅነት ሕይወት በፈተና የተሞላ ነበር። እርሱም ሆነ ታናሽ ወንድሙ በተለያዩ አጋጣሚዎች የድህነት ሕይወት መግፋታቸውን ተናግረዋል።

እንዳንድ ጊዜ የተጠበሰ የዶሮ ሥጋ መሸጫ ወደሆነው ኬኤፍሲ ሄደው የሰዎች ትራፊን ለቃቅመው ፍሪጅ ውስጥ እያስቀመጡ የሚመገቡበት ወቅት እንደነበረ በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግረዋል።

አንድሩ ቴት አሁን ላይ በተለይ በወጣቶች ዘንድ ተዋቂ ነው።

ቲክቶክ ላይ ከአንድሩ ቴት ጋር የተያያዙ ቪዲዮች ከ12.7 ቢሊዮን ጊዜ በላይ ታይተዋል።