በቲክቶክ ላይ ቪዲዮዎቹ ከ12 ቢሊዮን ጊዜ በላይ የታዩለት የአንድሩ ቴት መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል?

አንድሪው ቴት

የፎቶው ባለመብት, Channel 5

የምስሉ መግለጫ, አወዛጋቢው አንድሪው ቴት

አወዛጋቢው የብሪታኒያ እና የአሜሪካ ዜግነት ያለው አንድሩ ቴት በሰዎች የሕገ-ወጥ ዝውውር እና ከአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ከሳምንታት በፊት ሩሜኒያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ይህ ራሱን “ለሴቶች ጥልቅ ጥላቻ ያለው ሰው” አድርጎ የሚገልጸው ግለሰብ በሶሻል ሚዲያዎች ላይ በሚያጸባርቃቸው አመለካከቶች ተጽእኖ ፈጣሪነቱ ባለፉት ዓመታት እጅጉን ጨምሯል።

አንድሩ ቴት በቀደመ የስፖርት ሕይወቱ ከአንዴም አራት ግዜ የኪክቦክስ ውድድር የዓለም ሻምፒዮና ሆኗል።

አሁን ላይ ታዋቂ ያደረገው ግን በስፖርት ሕይወቱ ያገኘው ስኬት ሳይሆን ሴቶችን በተመለከተ የሚሰጣቸው “አጸያፊ እና አስነዋሪ” የተባሉት አስተያየቶቹ ናቸው።

አንድሩ ቴት ሴቶችን በተመለከተ በሚሰጣቸው አስተያየት ከፌስቡክ፣ ከኢንስታግራም እና ከዩቲዩብ ታግዷል። ከትዊተርም እንዲሁ ታግዶ የነበረ ቢሆንም፣ ማኅበራዊ ሚዲያ በኤሎን መስክ ስር መግባቱን ተከትሎ ዳግም ወደ ማኅበራዊ ትስስር መድረኩ ተመልሷል።

እንደ አውሮፓውያኔ አቆጣጠር 2016 ያጋጠመ አንድ ክስተት ቴትን ከብዙዎች ጋር አስተዋውቆታል። በወቅቱ ግለሰቡ አንዲ ሴት ላይ ጥቃት ሲሰነዘር የሚያሳይ ምስል መውጣቱን ተከትሎ ብዙ ተመልካች ካለው “ቢግ ብራዘር” ከተሰኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም እንዲታገድ ተደረገ።

ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ከወጣ በኋላ ቴት “እኔን መጥፎ ሰው አስመስሎ ለማቅረብ በፈለጉ ሰዎች ምስሉ ተቀናብሮ የቀረበ እንጂ እኔ አልተማታሁም” ብሎ አስተባብሎ ነበር።

የቀድሞ ኪክቦክሰር አንድሩ ቴት አሁን ላይ በትዊተር ላይ 3.6 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት።

ሙሉ የመዝገብ ስሙ ኢሞሪይ አንድሩ ቴት ነው። ቴት ከአሜሪካዊ አባት እና ከብሪታኒያዊት እናቱ በአሜሪካ ቺካጎ ግዛት ነው የተወለደው። ኮከብ የቼዝ ተጫዋች የሆኑት አባቱ ከእናቱ ጋር የተዋወቁት ለአሜሪካ አየር ኃይል በብሪታኒያ ውስጥ ሲያገለግሉ ነበር።

አባት እና እናት እስከተፋቱበት ጊዜ ድረስ ቴት ያደገው አሜሪካ ውስጥ ነበር። ከፍቺው በኋላ ከወላጅ እናቱ ጋር ወደ ብረታኒያ ተመለሰ።

ከአምስት ዓመት በፊት ደግሞ ጠቅልሎ ወደ አውሮፓዊቷ ሩሜኒያ ገብቷል። ቴት ኑሮውን ወደ ሩሜኒያ እንዲያዞር ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ በአገሪቱ ከአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ማምለጥ ቀላል ነው ብሎ ስለሚያምን መሆኑን በራሱ አንደበት ተናግሯል።

የቴት የልጅነት ሕይወት በፈተና የተሞላ ነበር። እርሱም ሆነ ታናሽ ወንድሙ በተለያዩ አጋጣሚዎች የድህነት ሕይወት መግፋታቸውን ተናግረዋል።

እንዳንድ ጊዜ የተጠበሰ የዶሮ ሥጋ መሸጫ ወደሆነው ኬኤፍሲ ሄደው የሰዎች ትራፊን ለቃቅመው ፍሪጅ ውስጥ እያስቀመጡ የሚመገቡበት ወቅት እንደነበረ በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግረዋል።

አንድሩ ቴት አሁን ላይ በተለይ በወጣቶች ዘንድ ተዋቂ ነው።

ቲክቶክ ላይ ከአንድሩ ቴት ጋር የተያያዙ ቪዲዮች ከ12.7 ቢሊዮን ጊዜ በላይ ታይተዋል።

ቴት ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሮማኒያ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ቴት ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሮማኒያ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአንድ የዩቲቭ ቪዲዮ ላይ ቴት እራሱን “የለየለት በሴቶች ጥላቻ ያበደ ሰው” አድርጎ እንደሚመለከት ገልጾ ነበር። “እኔ እውነተኛ ነኝ። እውነተኛ ስትሆነ ለጾታዊ ጉዳዮች ደንታ አይኖርህም” ሲል ይታያል።

አንድሩ ቴት በዚሁ ቪዲዮ ላይ ሴቶችን “የለየላቸው ሰነፎች” ሲል ከገለጸ በኋላ “እራሷን የቻለች ሴት” ብሎ ነገር የለም ይላል።

ቴት በአንድ ወቅት “ሴቶች የወንዶች ንብረት ናቸው” ብሎ ነበር። በሌላ ቪዲዮው ደግሞ “18 እና 19 ዓመት የሆነችው ሴቶች ከ25 ዓመት ሴቶች የበለጡ ሳቢ ናቸው ምክንያቱም አነስተኛ ቁጥር ካላቸው ሰዎች ጋር የተኙ ስለሆኑ” ብሏል።

ቴት በተደጋጋሚ በሚሰነዝራቸው የጥላቻ እና አዋራጅ አዋራጅ ንግግሮቹ ዩቲዩብ፣ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ቲክቶክ አግደውታል። ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ “ሴት ጠል ርዮተ ዓለም እንታገስም” በሚልም ከመድረካቸው አግደውታል።

ቴት ዳግም ከመመለሱ በፊት ከትዊተርም ታግዶ ነበር። ከትዊተር ያሳገደው ደግሞ ሴቶች ለሚፈጸሙባቸው ጾታዊ ጥቃቶች ኃላፊነቱን እራሳቸው መውሰድ አለባቸው ማለቱን ተከትሎ ነው።

የቴት ዝነኝነት ወላጆችን እና መምህራንን ያሳሰበም ነው። በዌልስ በሚገኝ አንድ ትምህር ቤት ተማሪዎች “አርአያችሁ” ስለሆነ ግለሰብ ጽሑፍ ጻፉ ቢባል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወንድ ልጆች ስለ አንድሩ ቴት ለመጻፍ መነሳታቸው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል።

ቴት “ቤቴ ሆኜ በቪዲዮ ካሜራ አማካይነት እራሴን ሚሊየነር ማድረግ የቻልኩ ሰው ነኝ” ይላል።

“በአራት ቦታዎች ላይ ያሉ 75 ሴቶች ለእኔ እየሰሩ በየወሩ 600 ሺህ ዶላር አገኛለሁ” ሲል ቃለ መጠይቅ ሰጥቶ ነበር።

አሁን ላይ በተሰረዘ ድረ-ገጹ ላይ ደግሞ “ጾታዊ ግንኙነቶች እንደመዝናኛ ሆነው ወደሚቀርቡበት ኢንዱስትሪ ሴቶች አስገብቻለሁ” ይላል።

ቴት ሴቶችን ከኮምፒዩተር ፊትለፊት አስቀምጦ በኢንተርኔት አማካይነት ወንዶችን እንዲያማልሉ በማድረግ ከወንዶች በሚቀበለው ገንዘብ ሃብት እንዳፈራ ይነገራል።

“ሥራዬ ከሴት ጋር መተዋወቅ ነው። ለትንሽ ጊዜ የፍቅር ቀጠሮዎች ይኖሩኛል። አብሪያት በመተኛት ጥራት እንዳላት እፈትሻለሁ፤ ያዘዝኳትን ሁሉ እንድትፈጽም እና እንድታፈቅረኝ አደርጋለሁ። ከዚያ ካሜራ ፊት ቁጭ ብላ በመስራት (የኢንትርኔት ካሜራ ፊት በመሆን ወንዶችን ማማለል) ሁለታችንም ሃብታም እንሆናል” ሲል ተናግሮ ነበር።

ቴት ይህን የሚሰራው ከታናሽ ወንድሙ ትሪስታን ጋር በመሆን ነው። ትሪስታን በአንድ ወቅት ለዴይሊ ሚረር ጋዜጣ ሲናገር ሥራቸው ማጭበርበር እንደሆነ በግልጽ አምኖ ነበር። ይህም ወንዶች በኢንተርኔት ለሚያነጋግሯቸው ሴቶች ክፍያ እንዲፈጽሙ ማድረግን ያካትታል።

“ቤታቸውን፣ መኪናቸውን፣ ቴሌቪዥናቸውን . . . የሚሸጡ ወንዶች አጋጥመውኛል። አንዱ አያቱ ከሞቱ በኋላ የውርስ ቤት ለመሸጥ እየተጠባበቀ ነው። ቤቱ ከተሸጠ በኋላ 20 ሺህ ፓዎንድ እንደሚደርሰው እና በውሽት የገንዝብ ችግር ውስጥ ለገባች (ሞዴል) ክፍያ እንደሚፈጽም ቃል ገብቶላት ነበር” ሲል የቴት ወንድም ለዴይሊ ሚረር ተናግሯል።

ትሪስታን በሩሜኒያ መዲና ቡካሬስት ከወንድሙ ጋር አብሮ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ቴት በበርካታ ቪዲዮች ላይ ውድ መኪኖቹን ሲያሸከረክር፣ በግል ጄት ሲበር፣ ውድ ጀልባ ውስጥ ሆኖ . . . ቅንጡ ሕይወቱን አሳይቷል።

ቴት በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት ከአየር ንብረት ተቆርቋሪዋ ግሬታ ተንበርግ ጋር የቃላት ምልልስ ውስጥ ገብቶም ነበር።

ቴት 33 መኪኖች እንዳሉት እና እያንዳንዱ መኪና የሚያወጣውን ከፍተኛ የሆነ አየር የሚበክል ጭስ መጠን እልክልሻለሁ ሲል ጽፎ ነበር።