ናይጄሪያዊው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ በአሜሪካ እስር እና ካሳ እንዲከፍል ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, INSTAGRAM/HUSHPUPPI
ናይጄሪያዊው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለፈጸማቸው የማጭበርበር ወንጀሎች የ11 ዓመት እስር ተፈረደበት።
ሀሽፓፒ በሚለው መጠሪያው በስፋት የሚታወቀው ራሞን አባስ ከእስሩ በተጨማሪ ካጭበረበራቸው ግለሰቦች መካከል ለሁለቱ 1 ሚሊዮን 732 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ተፈርዶበታል።
ሀሽፓፒ 2.8 ሚሊዮን ተከታዮች ባሉት የኢንስታግራም ገጹ ላይ የሚመራውን ቅንጡ ሕይወት በማሳየት ይታወቃል።
ሀሽፓፒ ኢንስታግራም ገጹ ላይ የሚያጋራቸው ይዘቶች ቤተ-መንግሥት በመሰለ ቤቱ ሲኖር፣ እጅግ ውድ መኪና ሲያሽከረክር እና በግል አውሮፕላን ሲበር የሚያሳዩ ነበሩ።
ይሁን እንጂ ናይጄሪያዊው ተጽእኖ ፈጣሪ እአአ 2021 ላይ ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ የማጭበርበር ድርጊቶች ተጠርጥሮ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ዱባይ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውሎ አሜሪካ ወዳለ እስር ቤት ሲወረወር ስሙም አብሮ ጠፍቷል።
የሎስ አንጀለስ የኤፍቢአይ ኃላፊ እንዳሉት ራሞን አባስ በዓለማችን ካሉ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብን ሕጋዊ ከሚያስመስሉ አደገኛ አጭበርባሪዎች መካከል አንዱ ነው ብሏል።
ሀሽፓፒ የኢንስታግራም ገጹን በመጠቀም በንግድ ሥራው ሃብት እንዳካበት በማስመሰል የንግድ ሥራ የኢሜይል መልዕክቶችን በመላክ ማጭበርበር፣ የኦላይን ባንክ ማጭበርበር፣ በርካታ ሰዎችን ለጉዳት የዳረገ የገንዘብ ማጭበርበር እና የሰሜን ኮሪያ መንግሥትን መርዳት የሚሉ ክሶች ቀርበውበት ነበር።
ሀሽፓፒ ከአንድ ዓመት በፊት በኳታር ትምህር ቤት መገንባት ከሚፈልግ ግለሰብ 1.1 ሚሊዮን ዶላር ማጭበርበሩን አምኖ ነበር።
ለዚህ የማጭበርበር ተግባሩ ሀሽፓፒ ተበዳዩን ለማታለል በኒው ዮርክ ያለ የባንክ ባለሙያ መስሎ ቀርቧል። ከዚህ በተጨማሪም ለዚሁ የማተልል ድርጊቱ እንዲረዳው ሐሰተኛ ድረ-ገጽ ከፍቶም ነበር።
ሀሽፓፒ በሦስት ወራት ውስጥ ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና አሜሪካ ካሉ አጋሮቹ ጋር በመሆን ከተበዳዩ ከአንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወስዷል።

የፎቶው ባለመብት, HUSHPUPPI/ INSTAGRAM
ከዚህ በተጨማሪም ሀሽፓፒ በጠቅላላው 24 ሚሊዮን ዶላር ጉዳት ያስከተለ በኢሜይል መልዕክት የማጭበርበር ተግባር መፈጸሙን ማመኑን የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ አስታውቋል።
እአአ 2019 መጀመሪያ ላይ ሀሽፓፒ በሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች ማልታ ውስጥ ከሚገኝ ባንክ የተሰረቀን 15 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሕጋዊ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ለማስመሰል ሙከራ አድርጎም የነበር። ይህ ድርጊትም የማጭበርበር ወንጀሎቹን ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነበር።
በናይጄሪዋ ሌጎስ የተወለደው ራሞስ አባስን በቅርብ የሚያውቁት ግን የሀሽፓፒ የማጭበርበር ሥራዎች እኚህ ብቻ አይደሉም ይላሉ።
በቅርብ የሚያውቁት ሀሽፓፒ የማጭበርበር ተግባሩን የጀመረው ‘ያሁ ቦይ’ በመሆን ነው ይላሉ። “ያሁ ቦይስ” አታላዮች ናቸው። በኢ-ሜይል የሚያገኟቸውን ‘ፍቅር ይዞኛል’ እያሉ በመጻፍ የሚያታልሉ። መጠሪያቸውንም ያገኙት በወቅቱ በርካታ ተጠቃሚዎች ከነበሩት ያሁ ሜይል ነው።
እንደ በርካታ የናይጄሪያ ‘ያሁ ቦይስ’ አባስም የወንጀል አድማሱን በማስፋት ወደ ሩቅ ምሥራቋ ማሌዢያ አቅንቷል። እአአ 2017 ላይ ደግሞ ዱባይ ከተሞ ነበር።
ሀሽፓፒ በበርካታ የማጭበርበር ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብሎ ብይን ይተላለፍበት እንጂ ራሞን አባስ “የተለወጠ ሰው” በማለት ክሱ ውድቅ እንዲሆንለት የጠየቁ አልጠፉም።
ፕሪሚየም ታይምስ የተኘው የናይጄሪያ ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ ሁለት ኢማሞች ምህረት እንዲደረግለት በሎስ አንጀለስ ጉዳዩን ለያዙ ዳኛ ደብዳቤ ጽፈዋል።
እነዚህ ሁለት የሃይማኖት መሪዎች ሀሽፓፒ ባሎቻቸውን በሞት የተነጠቀሱ ሴቶች እና ወላጅ አልባ ልጆችን እንደሚረዳ እና ለምገባ ፕሮግራሞች ገንዘብ እንደሚለግስ በመጥቀስ ምህረት እንዲደረግለት ጠይቀዋል።
ይህ በአንዲህ እንዳለ የሀሽፓፒ ሚስት የባለቤቷ እስር ሕይወት ከባድ እንዳደረገበት ገልጻ ለልጃቸው የትምህርት ቤት ክፍያ ለመፈጸም ትርፍ ሰዓት ለመስራት ተገድጃለሁ ብላለች።
አባስ በእጅ ጽሑፉ ለዳኛው በጻፈው ደብዳቤ በተግባሩ መጸጸቱን፣ ከተከሰሰበት ወንጀል 300ሺህ ዶላር ብቻ ማግኘቱን እና ተበዳዮቹን በራሱ ገንዘብ እንደሚክሳቸው ገልጾ ነበር።
ይሁን እንጂ የአባስም ሆነ የሌሎች ተማጽእኖ ከ135 ወራት የእስር ቤት ቆይታ ፍርድ አልታደጉትም።












