ሻኪራ ጄራርድ ፒኬን በተመለከተ ያወጣችው የሙዚቃ ቪዲዮ ክብረ ወሰን ሰበረ

ሻኪራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሻኪራ

ታዋቂዋ ዘፍኝ ሻኪራ የቀድሞ የትዳር አጋሯ ጄራርድ ፒኬ በእሷ ላይ ስለመወስለቱ የለቀቀችው የሙዚቃ ቪዲዮ በዩቲዩብ ላይ በመታየት ክብረ ወሰንን ሰበረ።

ይህ የሻኪራ ሙዚቃ ቪዲዮ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ63 ሚሊዮን ጊዜ በላይ በመታየት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በብዛት የታየ ቀዳሚው የላቲን የሙዚቃ ቪዲዮ ሆኗል።

የ45 ዓመቷ ሻኪራ ከቀድሞው የባርሴሎና እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች የ35 ዓመቱ ጄራርድ ፒኬ ጋር ከ10 ዓመታት በላይ አብረው ከቆዩ በኋላ ነው የተለያዩት።

ጥንዶቹ አንድ ላይ በቆዩባቸው ጊዜያት ሁለት ልጆችን አፍርተዋል።

በዚህ የአራት ደቂቃዎች የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ ሻኪራ እና አርጀንቲናዊው የሙዚቃ ፕሮዲዩሰር እና ዲጄ ቢዛራፕ ለመጀመሪያ ጊዜ አብረው ሰርተዋል።

ፒኬ እና ሻኪራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፒኬ እና ሻኪራ

ሻኪራ ከትዳር አጋሯ ጋር ስለመለያየቷ ስታዜም ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም፣ ከሦስት ወራት በፊት “ሞኖቶኒያ” የተባለ ዘፍን አውጥታ ነበር። ነገር ግን ዘፈኑ እንዳሁኑ የበቀል አይነት ሳይሆን ስለልብ ስብራቷ ያንጎራጎረችበት ነበር።

በአዲሱ የሙዚቃ ቪዲዮዋ ሻኪራ የቀድሞ አጋሯ ፒኬ ከአንዲት የ23 ዓመት ወጣት ጋር ጀምሮታል የተባለውን አዲስ ግንኙነት የሚተች ነው።

ኮሎምቢያዊቷ ዘፋኝ ሻኪራ በዘፈኗ ላይ ከስፔን ባለሥልጣናት በሚሊዮን የሚቆጠር የገቢ ታክስ አልከፈለችም በሚል ስለገባችበት የሕግ እሰጣገባም ጠቅሳለች።

በዘፈኗ ላይ ሻኪራ እዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ በገባችበት ጊዜ ፒኬ ትቷት እንደሄደ ወቅሳዋለች።

በተጨማሪም የቀድሞ አጋሯ ስፖርት ላይ ብቻ እንደሚያተኩር በመጥቀስ “ብዙ ጊዜ ጂም ውስጥ ታጠፋለህ፣ ነገር ግን አእምሮህም በትንሹም እንዲሰራ ማድረግ አለብህ” በማለት በዘፈኗ ተችታዋለች።

ጄራርድ ፒኬ የቀድሞ አጋሩ ስላወጣችው እና ሚሊዮኖች በአጭር ጊዜ ተመልክተውት ክብረ ወሰን በሰበረው ሙዚቃ ላይ እሱን በሚመለከት ስለተነሳው ጉዳይ አስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

ሻኪራ እና ፒኬ ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ስለመለያየታቸው ይፋ ባደረጉበት ጊዜ፣ ግንኙነታቸው ማብቃቱንና ከዚህ በኋላ በጋራ ልጆቻቸውን በማሳደግ ላይ እንደሚያተኩሩ ገልጸው ነበር።