የአሜሪካዋ ግዛት ቲክቶክ ህፃናትን አግባብ ላልሆኑ ይዘቶች አጋልጧል ብላ ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተጠቃሚዎች ዘንድ ዝነኛ የሆነው የቻይናው ማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ ቲክቶክ በአሜሪካዋ ግዛት ኢንዲያና ክስ ተመሰረተበት።
የኢንዲያና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቶድ ሮኪታ የቲክቶክ እናት ካምፓኒ ባይዳንስ የግዛቲቱን የሸማቾች ጥበቃ ሕጎችን ጥሷል የሚልም ክስ አቅርበዋል።
በያዝነው ሳምንት ረቡዕ በቲክቶክ ሁለት ክሶች ቀርበውበታል።
የመጀመሪያው ክስ ህፃናትን አግባብነት ለሌለው ይዘት አጋልጧል የሚል ነው። በቲክቶክ ላይ የቀረበው ሌላኛው ክስ የቻይና መንግሥት የተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃን ማግኘት መቻሉን ግልጽ አላዳረገም ይላል።
“ቲክቶክ የበግ ለምድ የለበሰ ተኩላ ነው” የሚል ወቀሳም በፍርድ ቤቱ ሰነድ ላይ ሰፍሯል።
“ቲክቶክ የኢንዲያና ተጠቃሚዎችን ለማታለል እና ለማሳሳት እስከተፈቀደለት ድረስ ግለሰቦቹም ሆነ ግላዊ መረጃዎቻቸው በቀላሉ ተጋላጭ ይሆናሉ” ብሏል ።
በተጨማሪም ቲክቶክ “የአልኮል ተጠቃሚነትን፣ ሲጋራ ማጨስን፣ አደንዛዥ ዕፆችን፣ ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን፣ እርቃን እና ስሜት ቀስቃሽ ሁኔታዎችን፣ አጸያፊ ንግግሮችን” የሚያበረታቱ ተገቢ ያልሆኑ ይዘቶችን በመድረኩ ሆን ብሎ ያስተዋውቃል ብሏል።
በአፕል እና የጉጉል መተግበሪያዎች ላይም ዕድሜያቸው 12 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ታዳጊዎችን እያታለለም ነው ተብሏል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቶድ ሮኪታ በቲክቶክ ላይ በአሜሪካ ግዛት ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሰረተ ክስ መሆኑን አስረድተዋል።
ባይትዳንስም ሆነ ቲክቶክ ቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጡም።
በኢንዲያና የተመሰረተው ክስ ይፋ የሆነው ሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች ቲክቶክን የሚከለክል ሕግ ማዘጋጀታቸው ከተሰማ በኋላ ነው።
በዚህም ቴክሳስ፣ ደቡብ ዳኮታ እና ደቡብ ካሮላይና ግዛቶች መንግሥታዊ በሆኑ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ ቲክቶን መጠቀምን ከልክለዋል።
ባለፈው ወር የፌደራሉ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ ኃላፊ ቲክቶክ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት እንደጋረጠ ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ ክሪስ ራይ ለአሜሪካ ምክር ቤት የአገር ውስጥ ደኅንነት ኮሚቴ እንደተናገሩት የቻይና ሕግ በዋናነት ኩባንያዎች “የቻይና መንግሥት የሚጠይቃቸውን እንደ መረጃን ማጋራት ወይም መሳሪያ በመሆን በማገልገል ረገድ ሁሉንም ለማድረግ ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።
የባይደን አስተዳደር በአሜሪካ የሚገኙ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎችን መረጃ ለመጠበቅ እንዲያስችል የብሔራዊ ደኅንነት ስምምነት ላይ ለመድረስ ከቲክቶክ ባለሥልጣናት ጋር ለወራት ሲነጋገሩ ቆይተዋል።












