የጋብቻ ጥያቄውን ውድቅ ያደረገችውን ሴት የገደለው ግብጻዊ በሞት ተቀጣ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የጋብቻ ጥያቄውን ውድቅ ያደረገችውን ሴት የገደለው የዩኒቨርስቲ ተማሪ የግብጽ ባለስልጣናት በሞት ቀጡት።
ግለሰቡ የጋብቻ ጥያቄየን አልተቀበለችም በሚል የገደላት ባለፈው ዓመት ነበር።
መሃመድ አደል የተባለው ግለሰብ የጋብቻ ጥያቄውን ውድቅ ያደረገችውን ነይራ አሽራፍን በስለት ወግቶ ሲያርዳት የሚያሳይ ዘግናኝ ቪዲዮ ወጥቷል።
ግድያው የተፈጸመው ሁለቱም በሚማሩበት ማንሱራ ዪኒቨርስቲ ግቢ ውጭ ሲሆን በርካቶችም ቪዲዮውን ተጋርተውታል።
ቪዲዮውም በመላው አገሪቱ ድንጋጤና ሽብር የለቀቀ ሲሆን በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትንም አስመልክቶ ውይይቶች እንዲነሱ መንገድ ከፍቷል።
የመሃመድ አደል የፍርድ ሂደት የተፋጠነ ሲሆን አቅዶና ሆን ብሎ ነፍስ በማጥፋትም ነው የሞት ፍርድ የተፈረደበት።
መሃመድ አደል በችሎቱ ላይ በቀረበበት የግድያ ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።
በግብጽ የሞት ፍርድ ከተበየነ በኋላ በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው ተፈጻሚ የሚሆነው።
ነገር ግን በአደል ጉዳይ አቃቤ ህግ የሞት ቅጣቱ እንዲፋጠንም በመጠየቁ በአስቸኳይ ተግባራዊ ሆኗል።
የሟቿ ነይራ አባት በልጃቸው ገዳይ ላይ የተፈጸመው የሞት ቅጣት ልጃቸውን የማይመልስ ቢሆንም ፍትህ አተገኝቷል ሲሉ ተናግረዋል።












