በ2016 ረቂቅ በጀት ላይ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ዕይታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለቀጣዩ ዓመት 2016 ከፍተኛ የተባለውም የፌደራል መንግሥቱ ረቂቅ በጀት አዘጋጅቶ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበታል።
ለ2016 በጀት ዓመት የቀረበው አጠቃላይ በጀት 801.65 ቢሊዮን ብር ሆኗል። ከዚህ ውስጥ ለመደበኛ ወጪዎች 370.1 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች 203.4 ቢሊዮን ብር፣ ለክልሎች የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ 214 ቢሊዮን ብር፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ 14 ቢሊዮን ብር ሆኖ ቀርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ቀጣይ ዓመት በጀት በቂ ነው?
ይህ የ800 ቢሊዮን ብር በጀት በዶላር ሲሰላ ወደ 14.5 ቢልዮን ዶላር ይሆናል። ጦርነት እና የኢኮኖሚ ቀዳዳ የፈጠረውን ክፍተት ለመሸፈን እንኳን የሚችል አይሆንም የሚሉት በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ልማት ባለሙያ እና አጥኚ ሙዑዝ ሐዱሽ (ዶ/ር) ናቸው።
በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) በጀቱ ካለፈው አንጻር በትንሹ ዕድገት ቢኖረውም፣ በመሠረተ ልማቶች መውደም እና ካለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መቀዛቀዛቀዝ አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ይላሉ።
መንግሥት ለቀጣይ ዓመት ያዘጋጀው በጀት በአገሪቱ ከዕለት ዕለት እየጨመረ ከመጣው የዋጋ ግሽበት አንጻር ሲታይም አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ጉቱ (ዶ/ር) ከሆነ ገበያው የሚመራው ዶላርን በጥቁር ገበያ በማስላት መሆኑን ከግምት በማስገባት በጀቱ ከስምንት ቢሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ ይጠቅሳሉ።
“ይህ ማለት ደግሞ የዛሬ ሰባት እና አስር ዓመት አገሪቱ የነበራት በጀት ነው። ይህም የኢትዮጵያ በጀት ወደ ኋላ መመለሱን ያሳያል” ብለዋል።
በጀቱ ኢትዮጵያን ፈቀቅ ሊያደርጋት የሚችል አለመሆኑን ሙዑዝ (ዶ/ር) ገልጸው “በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት አገሪቱ የነበራትን ሃብት ስንበላ ነው የከረምነው” ይላሉ።
የሕዝብ እንደራሴዎች መንግሥት እንዳለፈው ዓመት ለአዳዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚውል በጀት አለመያዙን በተመለከተ ጥያቄ አንስተዋል።
ጥያቄው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የ2016 በጀት መግለጫን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ካቀረቡ በኋላ የተነሳ ነው።
መንግሥት በጀቱን ሲያዘጋጅ፤ “የተጀመሩ የካፒታል ፕሮጀክቶችም ቢሆኑ የክፍያ ጊዜያቸውን በማሸጋሸግ የወጪ ቅነሳ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ታሳቢ” ማድረጉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በጦርነት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መመለስ ላይ ትኩረት ለማድረግ መታሰቡንም ገልጸዋል።
ሙዑዝ (ዶ/ር) “ለስሙ አገር በቀል ኢኮኖሚ ይባል እንጂ እንደ እርሻ፣ የገጠር እና ከተማ ፖሊሲ፣ ኢንዳስትሪ፣ ጥቃቅን እና አነስተኛ፣ ንግድ እና ፋይናንስ ያሉ ሴክተሮች ላይ ምን ለውጥ እንደተደረገ አያስረዳም” ይላሉ።
አክለውም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከጫካ ፕሮጀክቶች ውጪ በአገሪቱ ተጀምረው የነበሩ እንደ ባቡር እና መስኖ ያሉ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጄክቶች ጉዳይ እንደማይነሳ እና ሲከናወኑ እንዳልታዩም ሲሉም ገልጸዋል።
የሸቀጦች ዋጋ ከፍተኛ በሆነ መጠን መጨመሩን ተከትሎ ምግብ ነክ የሆኑ ነገሮች ላይ እስከ 46 በመቶ የዋጋ ጭማሪ እየታየ ነው፤ ይህም ‘ሃይፐር ኢንፍሌሽን’ ወደ ሚባለው 50 በመቶ የተጠጋ ነው።
የዋጋ ግሽበቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል የሚገልፁት ሙዑዝ ዋነኛው ምክንያት ግን ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ ከብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ውጪ ገበያ ውስጥ መሰራጨቱ እንደሆነ ያመለክታሉ።
“ጦርነቱ ኢኮኖሚውን በሁለት መልኩ ነው ያደቀቀው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ አገሪቱ ከገቡ ሸቀጦች ይልቅ የጦር መሳሪያ ነው የገባው። ይሄም የውጭ ምንዛሬውን በልቶታል። ሁለተኛው ደግሞ ከውጭም ሆነ ከውስጥ ኢንቨስትመንት አይኖርም። ኢንቨስትመንት ከሌለ ደግሞ ዕድገት የሚታሰብ አይሆንም” ይላሉ።
ከዚህ አንጻር ለ2016 ዓ.ም. እንዲጸድቅ የታሰበው በጀት አነስተኛ መሆኑን በመጥቀስ “ብር ከዶላር አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ መምጣቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚሆን” ያስቀምጣሉ።
ይህንንም “በፖለቲካ አጭበርብሮ እና ሸፋፍኖ ማለፍ ይቻል ይሆናል፤ ኢኮኖሚ ግን እንደዚያ አይደለም። የሚታይ እና የሚለካ ስለሆነ መሸፋፈን አይቻልም” ሲሉ ገልጸዋል።
በግብር፣ በአበዳሪዎች እና ለጋሾች የሚሞላ በጀት
ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው አጠቃላይ በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ያልተጠራ የበጀት ጉድለት መሆኑ ተገልጿል።
የበጀት ጉድለቱ የሚሸፈነው ከአገር ውስጥ እና ከውጭ ብድር እንደሚሆን ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥም 39 ቢሊዮን ብር ከውጭ ብድር እንደሚሸፈንም ተናግረዋል። የተቀረው 242 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከአገር ውስጥ ብድር ይሸፈናል።
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ባለፉት ዓመታት መንግሥት ተገቢውን ግብር መሰብሰብ መቻሉን እንደማያምኑ የሚናገሩት ሙዑዝ፤ ከውጭ የገንዘብ ምንጮችም በበቂ መጠን አለመገኘቱን ይገልጻሉ።
“ጉድለቱን ይቅር እና መንግሥት ከራሴ ካዝና የማቀርበው ነው ያለውን ከፍተኛ የገንዘብ መጠንም ሙሉ በሙሉ ያለው አይመስለኝም። አገሪቱ በብጥብጥ እና መረበሽ ውስጥ ነው ያለችው። ለዚህ መፍትሄ ሳታበጅ ‘ይህንን ያክል ገንዘብ ሰብስቤ በጀቴን እሸፍናለሁ፤ ጉድለቱን እሞላለሁ’ ማለት በተግባር ቀላል አይሆንም” ይላሉ።
ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ይገኝ እንደነበር በማንሳትም “እነዚህ ሁሉ ቀርተዋል። ስለዚህ ከዚህ በመነሳት ጉድለቱ የሚሸፈን አይሆንም” ይላሉ።
ከአሁን በኋላ የሚመጣ የውጭ የገንዝብ ድጋፍም ሆነ የሚፈቀድ ብድር ካለ ጉድለቱን ሊሞላ የሚችል አለመሆኑን እና ከመጣም “የተትረፈረፈ ሳይሆን እጅግ አነስተኛ በሆነ መጠን የሚንቆረቆር ነው የሚሆነው” ብለዋል።
በ2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ መንግሥት አገኘዋለሁ ብሎ ያቀደው ጠቅላላ ገቢ 520.6 ቢሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ 84.7 በመቶውን ድርሻ የያዘው ከታክስ ገቢ ለመሰብሰብ የታቀደው 440.8 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ የገንዘብ መጠን በ2015 በጀት ዓመት ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው የ26.7 በመቶ ጭማሪ ያለው ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በመጪው በጀት ዓመት ለታክስ ገቢዎች ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ቢያስታውቅም፤ ታክስ ካልሆኑ ምንጮች የሚሰበሰቡ ገቢዎችንም ታሳቢ ማድረጉ ታውቋል።
“ይህን ከፍተኛ ገንዘብ መሰብሰብ ቀላል አይደለም” የሚሉት ኢኮኖሚስቱ ጉቱ (ዶ/ር)፤ የንብረት ታክስን ጨምሮ አዳዲስ የገንዘብ ማግኛ መንገዶች መተግበራቸውን አውስተዋል።
የአገሪቱ ኢኮኖሚ መቀዛቀዙን በማንሳት “ከዚህ በፊት የበጀት ጉድለት ሲኖር መንግሥት በብድር እና በእርዳታ ይሸፍን ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ የበጀት ጉድለቱን መሟላቱ ላይ ጥርጣሬ አለኝ” ይላሉ።
ገበያ ማረጋጋት አዳጋች ከመሆኑ ባለፈ የቻይና እና የሌሎች አገራት የውጭ ብድርን መመለስ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ደግሞ በአንድ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት ሲያድግ ነበረውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ “በነበረበት ማቆየት እንኳን አስቸጋሪ ሆኗል” ሲሉ ገልጸዋል።
የመንግሥት ወጪ በመቀነስ ግብር በመሰብሰብ ብድር እና እርዳታን የሚያገኝበትን መንገድ በመሥራት ያለውን ጫና መቀነስ ይችላል ብለው ይምናሉ።
በዘንድሮው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7.5 በመቶ እንደሚያድግ መገመቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በ2016 በጀት ዓመት 7.9 በመቶ እድገት እንደሚመዘገብ መተንበዩንም ተናግረዋል።
ሥራ የማይፈጥረው በጀት
የእርዳታ እና ብድር መቋረጡ ዘንድሮም ሆነ አምና የአገሪቷ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ጫና ማምጣቱን የሚያነሱት ጉቱ (ዶ/ር) የሥራ ዕድል ለመፍጠር ቀርቶ ሥራ ላይ ያሉትንም ለማስቀጠል እስከመቸገር ተደርሷል ብለዋል።
አቶ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ፣ መንግሥት በ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት ምንም አይነት የመንግሥት ሠራተኛ ቅጥር እንደማይፈጸም ማስታወቃቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
የ2016 የመደበኛ በጀት በየመሥሪያ ቤቱ ያለውን አዲሱን አደረጃጀት ታሳቢ በማድረግ፣ የበጀት አጠቃቀም በቁጠባ እና በውጤታማነት ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ በቀጣይ በጀት ዓመት አዳዲስ የመንግሥት ሠራተኛ ቅጥር እንደማይኖር ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ በጀት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ለጉቱ ይህ “የሰው ኃይል አያስፈልግም ማለት ሳይሆን ቅጥር የማያካሂደው መንግሥት ክፍያውን መፈጸም አልችልም ብሎ ስላሰበ ነው።”
በየዓመቱ 2.5 ሚሊዮን የሥራ ዕድል መፈጠር እንደሚገባው ገልጸው ውሳኔው ጫና እንደሚኖረው ለመረዳት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ መሆን እንደማያስፈልገው ያነሳሉ።
ከአገር እስከ ቤተሰብ ድረስ ችግሩይዘልቃል በማለት፣ የሥራ ዕድል መፈጠር አለበት፣ የውጪ እና ገቢ መመጣጠን እና ገበያ መረጋጋትም የአንድን አገር ኢኮኖሚ ለመመዘን ቁልፍ መሆናቸውን አነስተዋል።
“አንድ አገር የሥራ ዕድል መፍጠር አልችልም ማለቷ ችግር ውስጥ እየገባች ስለመሆኗ መተንበይ ያስችላል” የሚሉት ጉቱ (ዶ/ር)፣ ይህም የኢኮኖሚ ዕድገት አለ ለማለት የምርታማነት መጨመር እና የሥራ ዕድል በሌለበት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዘንድሮም ደሞዝ ያላገኙ ሠራተኞች መኖራቸውን የሚያነሱት ሙዑዝ (ዶ/ር) ደግሞ “በሆነ ምክንያት የፈረሰ የኢኮኖሚ ዓምድ ብዙ ነገር ይዞ ነው የሚፈርሰው” በማለት የኢንቨስትመንቱ መጎዳት በርካታ መዘዞችን እንዳስከተለ ያስቀምጣሉ።
የክልሎች የበጀት
መከላከያ ሚኒስቴር ለ2016 በጀት ዓመት 50 ቢሊዮን ብር እንደተያዘለት ከቀረበው ረቂቅ በጀት ለመረዳት ተችሏል።
“...ለመከላከያ የሚመደበው መቀነስ አለበት ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን አገሪቷ ችግር ውስጥ ስላለች ለመከላከያው የተመደበው በጀት በቂ ነው ብዬ አላስብም። በጠቅላላው ለተለያዩ ሴክተሮች የተመደበው በጀት በቂ ነው ብዬ አላስብም” ይላሉ ጉቱ።
በ2015 በጀት ዓመት ለመከላከያ የተመደበው በጀት 84 ቢሊዮን ብር ነበር። ተቋሙ በ2014 የበጀት ዓመት 22 ቢሊዮን ብር ከተመደበለት ከጥቂት ወራት በኋላ ተጨማሪ 90 ቢሊየን ብር በማግኘቱ በጀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ተሻግሮ ነበር።
ለ2016 በጀት ዓመት ለክልሎች ድጎማ 214 ቢሊዮን ብር ተመደቧል።
ለትግራይ ክልል 12.5 ቢሊዮን፣ ለኦሮሚያ ክልል 71.9 ቢሊዮን፣ ለአማራ ክልል 45.1 ቢሊዮን፣ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልሎች 26.9 ቢሊዮን፣ ለሶማሌ ክልል 20.8 ቢሊዮን፣ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 6.4 ቢሊዮን፣ ለሲዳማ ክልል 8.5 ቢሊዮን፣ ለአፋር ክልል 6.3 ቢሊዮን፣ ለቤንሻንል ክልል 3.8 ቢሊዮን፣ ለጋምቤላ ክልል 2.7 ቢሊዮን፣ ለሐረሪ ክልል 1.5 ቢሊዮን፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስታደዳር 5.2 ቢሊዮን እና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር 1.8 ቢሊዮን ብር ሆኖ በረቂቁ ተመድቦላቸዋል።
ለክልሎች የቀረበው የበጀት መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከሁለት በመቶ በላይ ጭማሪ አለው ተብሏል።
ከቀረበው ረቂቅ በጀት ውስጥ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ 20 ቢሊዮን ብር ተይዟል።
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከፍተኛ ገንዘብ ቢያስፈልግም አዲሱ ረቂቅ በጀት በቂ ትኩረት እንዳልሰጠው ጉቱ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል።
ሌላው ስጋት ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የሠላም እጦት ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል መባሉ ነው።
ለክልሎች የተመደበው በጀት ትልቅ አለመሆኑን የሚናገሩት ጉቱ ለበጀት ድልድል ጥቅም ላይ የሚውለው መስፈርትም በድጋሚ መታየት እንዳለበትም አንስተዋል።
“ትግራይ ውስጥ የወደመው መሠረተ ልማት ብቻ አይደለም። ኢኮኖሚው እንዳለ ነው የወደመው። ወደ 161 ሺህ ቢዝነሶች ናቸው ትግራይ ውስጥ ተዘግተው የቆዩት። ...የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና መሠረተ-ልማት ውድመት ለደረሰባት ትግራይ ብቻ እንኳን የሚበቃ አይደለም” የሚል ፅኑ አቋም ያላቸው ሙዑዝ (ዶ/ር) ናቸው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ላይ ከተወያየ በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመራው ሲሆን፣ የሰኔ ወር ከመጠናቀቁ በፊት ይጸድቃል።












