በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተቃዋሚዎች ድምጽ እየተዳከመ የመጣው ለምንድን ነው?

መንግሥት ካዘጋጀው የተቃውሞ ሰድልፍ የሚመለሱ ባንዲራ የያዙ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በብሔር እና በአገር አቀፍ ፓርቲነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ከአንድ መቶ የዘለለበት ወቅት ነበር።

በእርግጥ ለአንድ አገር ምን ያህል ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ ለሚል ጥያቄ መልስም ሆነ ልኬት ማስቀመጥ የሚቻል ባይሆንም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የፓርቲዎች ቁጥር መብዛት እንደ አንድ መነጋገሪያ ርዕስ የሚነሳ ነው።

የብዛታቸውን ያህል ግን ጠንካራ ሆነው፣ ለሚወክሉት ሕዝብ እና ማኅበረሰብ ድምጽ ከመሆን ይልቅ አሉ ሲባሉ ሲከስሙ ይስተዋላል።

ያሉትም ቢሆኑ ተዳክመው፣ የሕዝቡን አጀንዳ አንስቶ ከመታገል ይልቅ እርስ በእርስ ሲቆራቆሱ ይታያል።

በተጨማሪም በጎምቱ ፖለቲከኞች እና ምሁራን ሳይቀር የሚቋቋሙ ፓርቲዎች ብዙ አባል እና ደጋፊ ካፈሩ በኋላ ሲፍረከረኩ እና ሲከስሙ ታይተዋል።

ለመሆኑ የዚህ ምክንያት ምን ይሆን? ተጠያቂውስ ማን ነው?

በትግራይ እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስማቸው ከሚነሳ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆኑት የዓረና ትግራይ ፓርቲ መስራች እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ገብሩ አስራት፣ በአገሪቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መውጣት የጀመሩት በ1960ዎቹ እንደነበረ ያስታውሳሉ።

“ሆኖም ግን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ማለትም ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ፓርቲዎች በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው አያውቅም። ኢህአዴግ ሕብረ-ፓርቲያዊ ሥርዓት እፈጥራለሁ ብሎ ቢነሳም የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ሆኖ ነበር የቀጠለው” የሚል ግምገማ አላቸው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ራሄል ባፌም (ዶ/ር) ይህንን ሐሳብ ይጋሩታል።

“ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም ቢሆን መድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንደሚፈጠር እና አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ እንደምትሻገር አቅጣጫ ነበር። በተግባር ግን እንደዚያ አልነበርም። የአንድ ፓርቲ፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት የበላይነት ነው የሰፈነው” ይላሉ።

ለዶ/ር ራሄል የፓርቲ ፖለቲካው ሥርዓት ላለፉት 50 ዓመታት ነጻ ካለመሆኑም በላይ በሴራ ጭምር የተሳሰረም ነው። ፓርቲዎች ሲቋቋሙ እንዲጠፉ እንደሚደረግ ይናገራሉ።

“የሚከተሉት አቅጣጫ አጭበርብረውም ይሁን አሳምነው ወደ አንድ ፓርቲ ማቀላቀል ወይ ደግሞ በጠላትነት ተፈርጆ ማጥፋት፣ ካልሆነም አወዛግቦ ውሳኔ እና ድምጽ አልባ አድርጎ ማኖር ዋና መመሪያቸው ነበር” ሲሉ ይገልጻሉ።

ይህ ሁኔታ አሁንም በብልፅግና ስር መቀጠሉን የሚናገሩት ራሄል (ዶ/ር) ሥርዓቱ በዚህ መልኩ ከመሄዱም በላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹም ከሴራው መጽዳት ባለመቻላቸው በተደጋጋሚ የመፍረስ አደጋ እንደሚያጋጥማቸው ያስረዳሉ።

ፖለቲከኛው አቶ ገብሩ አስራት “ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በፓርቲዎች እምነት አልነበረውም። ብልፅግናም የዚያው ተቀጥላ ነው። ለስሙ ሕብረ-ፓርቲነትን እቀበላለሁ ቢልም አሁንም ግን ፓርቲዎች በሚችሉት በነፃነት መንቀሳቀስ አልቻሉም። መደለል እና ማስፈራራት አለ” ባይ ናቸው።

“ፖለቲካዊ ግብይት”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከደርግ ሥርዓት መውደቅ ወዲህ ባሉት 32 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈጥረው አንዳንዶቹ ዛሬም ድረስ ሲቀጥሉ በተለያየ ምክንያት መንገድ ላይ የቀሩም አሉ።

በተለይ በ1990ዎቹ የኢህአዴግን ወንበር እስከ መነቅነቅ የደረሱበት ሁኔታ እንደነበር ይታወሳል። በ1997 የተካሄደው አገራዊ ምርጫ ገዢው ፓርቲን ከፍተኛ ስጋት እና አለመረጋጋት ውስጥ ያስገባበት ሁኔታም ለዚህ እንደማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ኃይሉ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት አስርት ዓመታት የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ የሦስተኛ ዲግሪ ዕጩ ነው።

“ኢትዮጵያ ውስጥ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት ያስፈለገው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገሪቱ ውስጥ በሚያደረጉት ውድድር የማኅበረ-ኢኮኖሚ እድገት እንዲመጣ ታስቦ ነው። የተቃዋሚ ኃይሎች እንቅስቃሴ መውረዱ ሕብረተቡን አማራጭ ያሳጣዋል” ይላል።

አክሎም “ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች በሕብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ካገኙ መንግሥትን በመተካት ፖሊሲያቸውን ይተገብራሉ። ወንበር ካላገኙም ለሕብረተሰቡ መብት ይቆማሉ” በማለት ያስረዳል።

ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን ይናገራል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚከተሉት ሠላማዊ ትግል የሕዝብ ድጋፍ እንደሚጠይቅ የሚያምኑት ዶ/ር ራሄል በበኩላቸው ከሕዝቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት ከመንግሥት ጋር ለሚኖራቸው ሠላማዊ ትግል መሠረት መሆኑንም አጽንኦት ይሰጣሉ።

ሕዝቡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ካለው አለመተማመን በተጨማሪ መንግሥትም አለመተማመን እንዳይኖር እንደሚያደርግ ይገልጻሉ።

“ሥርዓቱ በዚህ በ32 ዓመታት ውስጥ የሚያራምደው ነገር ‘ተቃዋሚዎቹ እኮ አይጠቅሙም አይመጥኑም’፤ ‘ብቁ ሰው በውስጣቸው የለም’፤ ‘ሲደራጁ ይፈርሳሉ’ የሚል ነገር እንዲመጣ ነው እሳቤው እንጂ ተመጋጋቢ ሆኖ፣ ለአገር የሚጠቅም ነገር እንደሚያመጣ ለመንግሥት እና ለሥርዓቱ አስፈላጊ መሆኑን ስላላመነ፤ ይሄ ነገር ሆን ተብሎ ተሰርቶበታል” ሲሉ በፓርቲዎችና በሕዝብ መካከል መተማመን እንዳይፈጠር የሚደርግ ጥረትን ያስረዳሉ።

አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው በአገሪቱ ፓርቲዎች ውስጥ ፖለቲካ ግብይት እንደሚካሄድ በመግለፅ “ፓርቲ እና ፖለቲካ በገንዘብ የሚሸጥ እና የሚለወጥበት ሁኔታ ነው ያለው። የሕዝብን ጥቅም እና መብት ለመጠበቅ የሚቆረቆሩ እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ፓርቲዎች ልክ እንደ ዕቃ የሚሸጡ እና የመንግሥት ተለጣፊዎች እየሆኑ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

“ለምሳሌ በትግራይ ውስጥ በፓርቲ እና በቅድመ ፓርቲ ደረጃ የሚገለፁ ወይም ፓርቲ ነን ብለው ራሳቸው ያወጁ ወደ 13 ድርጅቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል ግን ከግማሽ በላይ በገዢው ፓርቲ ማለትም በህወሓት እንዲሁም በብልፅግና ወይም በውጭ ኃይሎች የተፈጠሩ ናቸው። በአገር ደረጃም ከገዢው ፓርቲ ተለጣፊ የሆኑ ወይም በውጭ ኃይሎች የሚደገፉ አሉ” ሲሉ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ራሄል፣ ሁሉም ወደ ፓርቲዎች ሚመጣው የአገር ጉዳይ ጉዳዩ ሆኖ ላይሆን ይችላል የሚል እምነት አላቸው።

እንደ ደሃ አገር ከታየ ብዙ መሰናክሎች ይኖራሉ የሚሉት ዶ/ር ራሄል “ብዙ ጥቃቶች ስላሉ ከእነዚያ ጥቃቶች ሽሽት እንደ መጠለያ የመሰባሰብም አካሄድ አለ። ብዙ ችግሮች ስላሉ ከዚያ አንጻር ነው ማየት እንጂ እንደ ሌሎቹ ዴሞክራሲን እየተለማምዱ እንዳሉ አገሮች ነጻ የሆነ የፖለቲካ ሜዳ የለምና እነዚህ ችግር ሆነው እየመጡ ነው” ይላሉ።

መክሰም ለምን እና እንዴት?

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምሁርም ሆኑ ፖለቲከኞች፣ አሁን ላይ በአገሪቱ ያለው የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እንደሚጠበቀው እንዳልሆነ የሚገልፁ ሲሆን፣ ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው ፓርቲዎች እስከ መፍረስ እና መክሰም እየደረሱ መሆናቸውን ያነሳሉ።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና የተሻለ መፃኢ ላይ ተስፋ የሚጣልባቸው ፓርቲዎች ከጊዜ በኋላ የሚከስሙበት ምክንያት በሁለት እንደሚከፈሉም በአንድ ድምጽ ይናገራሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ አገሪቷን የሚያስተዳድረው መንግሥት ሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎች ላይ የሚይደርሰውን ጫና ያነሳል።

“ገዢው ፓርቲ እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች እና የፀጥታ አካላት ያሉ የፖለቲካ ተቋማትን እንዲመቸው አድርጎ ያደረጃል። ከዚህ ውጪ አገሪቷን የሚያስተዳድረው መንግሥት የሚደግፉትን ‘ሳምሶናይት’ (የውሸት የፖለቲካ ፓርቲዎችን) ያደራጃል” የሚለው ፕሮፌሰሩ እነዚህ ፓርቲዎች ከመንግሥት ድጋፍ እንደሚያገኙም ይናገራል።

መንግሥት በትክክልም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከማብቃት በተጨማሪ፣ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ይፈልጋል ወይ? ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ራሄል “የሚባለው እና የሚደረገው ነገር እንደሚጋጭ” ይናገራሉ።

ዋናው አካሄድ የፖለቲካ ሴራ መሆኑን በመጥቀስ “በተለይ ለአገር የሚቆሙ ፓርቲዎች አመራሮቻቸው ይታሰራሉ፣ ይገደላሉ ወይም ይጠፋሉ። ዋናው መሳሪያ እኮ ፓርቲዎችን ከሕዝቡ መለየት ነው። ሕዝብ ነው መሳሪያቸው። ሕዝብ ደግሞ በስጋት እና በአንድ ለአምስት የታሰረ ስለሆነ የእሱ ዕድል ነው የሚገጥመኝ እያለ ዝም ይላል። ይህ ደግሞ ትልቅ ጉዳት ነው” ይላሉ።

ሆኖም ግን ችግሩ ከመንግሥት ብቻ የሚመነጭ አለመሆኑን በመግለፅ “እንዳለመታደል ሆኖ በፓርቲዎች በኩል አለመደማመጥ አለ” ሲሉ ፓርቲዎችን ለራሳቸው መዳከም እና መጥፋት ተጠያቂዎች ያደርጋሉ።

በፓርቲዎች አካሄድ ውስጥ በአንድ ጉዳይ ላይ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በሃሳብ በመስማማት መወሰን ያለመለመዱን ያነሳሉ።

“በዚህ አግባብ በመተማመን እና ነገሮችን በመፍታት ከመሄድ ይልቅ አንጻራዊ ተጽዕኖ ይስተዋላል። ሥራ አሰፈጻሚው የፈለገውን ወደ መወሰን እና ሌላው ወደ አለመስማት ሲሄድ ነገሮች ክፍተት ይፈጠራል” ይላሉ።

ነፃ መድረክ ከሌለ የፓርቲዎች መኖር ትርጉም አልባ እንደሚሆን የሚያነሱት አቶ ገብሩ አስራት፣ ከፓርቲዎቹ የሚመነጩ ልዩነቶች እና ከመንግሥት በኩል የሚደርስባቸው ጫና ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ያስቀምጣሉ።

“ፓርቲዎች ለገዢው ፓርቲ ተገዢ የሚሆኑበት ሁኔታ እያየን ነው። ስለዚህ አንደኛው ምክንያት ብልፅግና ሆነ እዚህ ትግራይ ውስጥ ያለው ህወሓት ፓርቲዎችን አስፈራርተው ሆነ በገንዘብ ደልለው ዝም ያሰኟቸዋል። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በውስጣቸው የሚፈጠር የሥልጣን ሽኩቻ የሚያስከትለው አለመግባባት ነው” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፖለቲከኛው እንደሚሉት ከአመሠራረት ጀምሮ ሲፈተሽ ልዩነት መፍጠር የሚችል ሃሳብ ወይ ርዕዮተ-ዓለም ይዘው የሚነሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እጅግ ጥቂቶች ናቸው።

በተለይ በአሁኑ ጊዜ ገዢው ብልፅግና በተለያዩ ትልልቅ አገራዊ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉትን መሥራች እና ከፍተኛ አመራሮችን ወደ መንግሥታዊ ሥልጣን የሚያመጣበት መንገድ “ሆነ ተብሎ የተቃዋሚዎች ጎራን ለማዳከም” ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ነው የሚያምኑት።

በተቃዋሚው የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ለዓመታት የታዩ ፖለቲከኞች አሁን በብልፅግና መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ከያዙ በኋላ በፓርቲያቸው ውስጥ የሚያዳክሙ ችግሮች ተፈጥረዋል ወይም እንደተቃዋሚ የሚጠበቅባቸውን እየሰሩ አይደለም ይላሉ አቶ ገብሩ።

“እነዚህ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በሃገሪቱ ብዙ ችግሮች ሲፈጠሩ ቆምንለት ለሚሉት ዓላማ ድምፅ ሲሆኑ አይታይም።”

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምን ይፈርሳሉ ሲባሉ ተጠይቀውም ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ። ውስጣዊ የሚሉት በተቃዋሚ ፓርቲዎች በውስጥ ዲሞክራሲያዊ አሰራር አለመኖር ነው። እንዲሁም የፖለቲካ አደረጃጀት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ አብዛኛዎቹ የላቸውም ይላሉ።

“አንዳንዶቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ ሰው ወይም በጥቂት ግለሰቦች የተመሠረቱ ናቸው። የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች የጋራ ጠላት እንጂ የጋራ አጀንዳ የላቸውም።”

“የጋራ ጠላት እንጂ የጋራ አጀንዳ የላቸውም”

በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ታይተው የሚጠፉ ፓርቲዎች በብዛት የመታየታቸውን ያህል አዲስ የሚቋቋሙም በርካታ ናቸው። በክልልም በአገርም ደረጃ ብቅ የሚሉ ፓርቲዎች አሉ።

ፖለቲከኛው አቶ ገብሩ አስራት ይህንን “መበታተን” ሲሉ ገልፀውት፣ ይህ መበታተንም ጠንካራ ተቃዋሚ ኃይል እንዳይፈጠር ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።

“ለምንድን ነው የሚበታተኑት? መጠናት ያለበት ይመስለኛል። ለምሳሌ ትግራይ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ካነሳሁ፤ ለምንድን ነው በዚህ መልኩ እየተፈለፈሉ ያሉት ካልን እዚያ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ውጤት ነው የሚሆነው። ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መወያየት በማትችልበት፣ ሐሳብህን በማትገልፅበት እና ነፃነት በሌለበት ሁኔታ መፍትሔ ለማምጣት የምትወስደው እርምጃ በአካባቢ እና በቡድን መደራጀት ነው” በማለት አስቀምጠዋል።

ገዢው ፓርቲ ብልፅግና በፖለቲካው ምኅዳር ላይ የሚያሳድረው ጫና ከሚያስከትለው የተቃዋሚዎች መዳከም ውጤት በተጨማሪ ፓርቲዎቹም በተበታተነ መልኩ ለመሄድ መምረጣቸው ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስቸግራቸው ያስረዳሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ግን አንድ ላይ ሲደራጁም ምርጫ አሸንፈው አገሪቷን የሚመራውን መንግሥትን ለመጣል ነው የሚያስቡት እንጂ መንግሥት ከሆኑ በኋላ እንዴት እንደሚያስተዳድሩ መንግሥት ካልሆኑም እንዴት እንደ ፓርቲ መቀጠል እንደሚችሉ ብዙም እንደማያስቡ ይናገራል።

“በኢትዮጵያ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ የተቃዋሚ ኃይሎች ይፈርሳሉ” ይላል።

አክሎም “በ1997 ፓርቲዎች ግንባር ፈጥረው ከተደራጁ በኋላ ፈርሰው ነበር። መድረክ ሁለት ምርጫዎች ላይ ከተሳተፈ በኋላ ፈርሷል። አሁንም ኢዜማ የሚባለው ፓርቲ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ተፍረክርኳል። የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች የጋራ ጠላት ነው ያላቸው እንጂ የጋራ አጀንዳ የላቸውም። በውጭም በውስጥም ጫና ይፈርሳሉ” ሲል ያስረዳል።

መደራጀት እና ኅብረት ፈጥሮ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ ሃሳብ የሚሰጡት ፖለቲከኛው አቶ ገብሩ በበኩላቸው “የተበታተኑ ፓርቲዎች ናቸው የተፈጠሩት። ሃሳብ ላላቸው ትልልቅ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር አካሄድ የለምም፣ አልነበረምም። እንዳንዳቹ እዚህ ግባ የማይባል የአባላት ቁጥር የያዙ ናቸው። ሃሳባቸውም ወደ ሌላ ፓርቲ መጠቃለል የሚችል ነው” ይላሉ።

መፍትሔው ምን ይሆን?

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ራሄል ባፌ፣ በዋናነት ሕዝቡ እንደ አገር መፍትሔው ላይ መምከር እንዳለበት ይገልጻሉ።

“አማራጭ ስለሌለ ወደ ብሔራዊ ምክክር አምርቶ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ የጋራ መፍትሔ ላይ ይደረስ ተብሎ እየተኬደ ነው ያለው። ግን አሁን የሚስተዋለው ሥርዓቱ ራሱ ይህ ነገር መሬት ላይ እንዳይወርድ እየሠራ ነው” ይላሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሕዝቡ የተከፈለውን ዋጋ ከፍለው ወደዚያ የሚደረስበትን አካሄድ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ መሄድ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ “ከፊትም ያለው ዋጋ የሚያስከፍል ሥራ ነውና በዚያ አግባብ ነው መሄድ ያለብን ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ሃሳባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስም መፍትሔ ሲል ሁለት ሃሳቦችን ያነሳል። ፓርቲዎች የራሳቸው አደረጃጃት እና ፖሊሲ በውስጣቸው ደግሞ የዴሞክራሲ ባህል ማሳደግ ያስፈልጋቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመቀጠል አገራዊ የጋራ ስምምነት ሊኖር ይገባል ብሎ ያምናል።

“ኢትዮጵያዊ ማነው የሚለው ላይ መስማማት አለባቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ምርጫ ቦርድ፣ የፀጥታ አካላት እና የጋራ ሕገ መንግሥት ሊኖር ይገባል ይላል” በማለትም ሐሳቡን ይቋጫል።

የሃሳብ እና የለውጥ ፓርቲዎች እንጂ ‘የአክቲቪስቶች ሥራ የሚሰሩ ፓርቲዎች’ ሊኖሩ እንደማይገባ የሚገልፁት ፖለቲከኛ ገብሩ አስራት በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሌላውን ለመንጠቅ መሯሯጥ እንጂ ተቀራርቦ መስራት፣ መወያየት እና ሰጥቶ መቀበል ብዙም እንዳልተለመደ ይገልጻሉ።

“ፓርቲዎቹ በብዙ ነገሮች መገናኘት የሚችሉ ናቸው። ብዙዎቹ በዓላማቸው ወደ አንድ መጠቃለል ይችላሉ። መጠቃለል ባይችሉም እንኳ ኅብረት መፍጠር ይችላሉ። በብዙዎቹ ዘንድ ግን ይህ የሚታይ አይደለም። እየተባዙ እንጂ ወደ መጣመር የሚመጡ ፓርቲዎች እያየሁ አይደለም። ስለዚህ ፓርቲዎቹ ወደ ውህደት እና መቀራረብ የሚወስዳቸውን መንገድ መከተል ይኖርባቸዋል። አሁን እየሄዱበት ባለ አካሄድ ግን አቅም እና ኃይል ያለው ፓርቲ መፍጠር የሚችሉ አይመስለኝም” ብለዋል።