የኢትዮጵያን የኑሮ ውድነት እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግርን ፖለቲካው ችላ ብሎታል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዳዊት የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥሮ ከሚሠራ ወንድሙ ጋር አየር ጤና አካባቢ አንዲት አነስ ያለች ቤት ተከራይቶ ይኖራል።
ምንም እንኳ ዳዊት ቋሚ ሥራ ባይኖረውም ተሯሩጦ ከሚያገኘው ገንዘብ፤ አልፎም ወንድሙ በወር ከሚያገኘው ደመወዝ በማዋጣት የቤት ኪራይ እና አስቤዛ ያሟላሉ።
ዳዊት እንደሚለው ወንደሙ ከመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚያገኘው ቋሚ ገቢ “እዚህ ግባ” የሚባል አይደለም።
“ኑሮውን ይጨምራል። ገቢያችን ግን እዚያው ነው” ይላል ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ ተሯሩጦ ማደርን የመረጠው ዳዊት።
የአፍሪካ ዲቨለፕመንት ባንክ እንደሚለው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በፈረንጆቹ 2021 ከነበረው 6.1 ዕድገት ዝቅ ብሎ በ2022 ወደ 5.6 ወርዷል። የኑሮ ግሽበቱ ደግሞ በ2021 ወደ 26.7 በመቶ ከፍ ብሏል።
የእርስ በርስ ግጭት፣ ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት እና የኮቪድ ወረርሽኝ ለኢኮኖሚው መቃወስ ዐበይት ከሚባሉ ምክንያቶች መካከል ናቸው።
መሠረታዊ የሚባሉ እንደ ጤፍ ያሉ ምርቶች ዋጋ ከፍተኛ መናር እያሳዩ ሲሆን፣ በተለይ ቋሚ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች መቸገራቸውን ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ቀውስ ውስጥ ቢገባም አሁንም ሌሎች ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች አገሪቱን እየፈተኗት ይገኛሉ።
ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ራሱን ማራቅ የሚሻው ዳዊት ይህ የሚሳካለት አይመስልም። በአንድ በኩል የኑሮ ውድነት፤ በሌላ በኩል ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ውጥንቅጦች ወጥረው ይዘውታል።
ለመሆኑ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለኢኮኖሚ ወይስ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ ለፖለቲካው? የምጣኔ ሃብት ችግሩስ አስፈላጊውን ያህል የመፍትሄ ትኩረት የተነፈገው ምክንያት ምን ይሆን?
“አንድነት አለመኖር”
በምጣኔ ሃብት ጉዳዮች ላይ አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ።
“ከ2018 ጀምሮ በየዓመቱ ምርቶች እና አገልግሎቶች ዋጋቸው ከ200 እና 300 በመቶ በላይ እየጨመረ ነው። የዋጋ ንረቱ በየወሩ 33 በመቶ እያደገ እንደሆነ የመንግሥት መረጃም ያመለክታል።”
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህሩ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ዋጋ ንረት ከፍ እያለ ነገር ግን የነዋሪዎች ገቢ አለመጨመሩ ችግሩን የበለጠ የተወሳሰበ እንዲሆን አድርጎታል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አክለው እንደ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቱኒዚያ ባሉ የአፍሪካ አገራት ሥራ አጥነትን ጨምሮ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሰዎች ለተቃውሞ እንዲወጡ ምክንያት መሆናቸውን ያነሳሉ።
“እነዚህ አገራት በተነፃፃሪ ከእኛ የተሻለ ዲሞክራሲ ይተገብራሉ። ዜጎቻቸው ሐሳባቸውን በነፃ ይገልጣሉ” የሚሉት ምሑሩ፤ የምጣኔ ሃብት መረጃዎችን (ዳታ) ግለሰብም ሆነ ድርጅት በቀላሉ የሚያገኙባቸው አገራት እንደሆነ ይናገራሉ።
መሰል አገራት የምጣኔ ሃብት መረጃዎቻቸውን ለሁሉም ክፍት ስለሚያደርጉ ዜጎች የኢኮኖሚውን ሁኔታ በቀላሉ መከተል እንደሚችሉ ይጠቅሳሉ።
እንደ ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ የዋጋ ግሽበት ጉዳይ በቂ ትኩረት ያላገኘበት ሌላኛው ምክንያት “አንድነት አለመኖሩ” ነው።
“አንድነት፣ መደማመጥ እና ውይይት በሌለበት አገር ውስጥ አንድ ሐሳብ ይዞ ወደ ጎዳና መውጣት አሊያም በመገናኛ ብዙኃን ሐሳብን መግለጽ ከባድ ነው።”
ምሑሩ አክለውም ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች ከዋጋ ግሽበት ባሻገር ሌሎች የሚያሳስቧቸው ነገሮች መኖራቸውን ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሕይወት የመኖር ጥያቄ
ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ኣጋጠሙት የደኅንነት ችግሮች በምጣኔ ሀብቱ ላይ የራሳቸው የሆነ ተጽእኖ አላቸው።
ግጭቶች እና ጦርነቶች የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፋቸው በተጨማሪ ከፍተኛ የንበረት ውድመትን አስከትለዋል። ይህ ደግሞ የምርቶች እና የአገልግሎቶችን አቅርቦት በማሰናከል የዋጋ ውድነትን ያስከትላሉ።
የሰላም እጦት ደግሞ ዋነኛው ውጤት ደግሞ የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት ጥያቄ ውስጥ መክተቱ ነው።
ጉቱ ቴሶም (ዶ/ር) “በሕይወት የመኖር ጥያቄ ነው የዚህ አገር ሕዝብ የሚያሳስበው” ይላሉ። “እስር፣ መፈናቀል፣ የከፋ ድርቅ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ግጭቶች፤ ሰዎች ‘ወጥቼ በሰላም እመለሳለሁ?’ ብለው እንዲጠይቁ አስገድዷቸዋል።”
“በሕይወት መኖር አስጊ በሆነበት አገር ውስጥ” ስለ ዋጋ ግሽበር ማውራት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ይላሉ መምህሩ።
በሌላ በኩል በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ዋነና ወቅታዊ አጀንዳ አድርገው አይንቀሳቀሱም የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው “ኢትዮጵያ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም፤ አሉ የሚባሉትም እሥር ላይ ነው የሚገኙት” የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው።
“ከዚህ ቀደም ተቃዋሚ ፓርቲ ናቸው ያልናቸው ከመንግሥት ጋር ተቀላቅለው ይሰራሉ አሊያም ሥልጣን ይዘዋል” ይላሉ።
ምሑሩ፤ እነዚህ ፓርቲዎች “ለሰው ልጆች መብት እና ጠንካራ የሆነ የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የሚንቀሳቀሱ ናቸው” ብለው አያምኑም።
“ከጥቂት ፓርቲዎች በቀር አብዛኛዎቹ ሥልጣን፣ ምቾች እና በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚተጉ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ዛሬ የት ነው ያሉት? ከመንግሥት ጋር ናቸው። ለዚህ ሁሉ ችግር መንስዔ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ እነሱ ናቸው።”
በኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአገሪቱ ሕዝብ የተጋፈጠውን ምጣኔ ሃብታዊ ችግርን በተመለከተ የጎላ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይታዩም።
በተለያዩ ወቅታዊ ክስተቶች ላይ በመግለጫ ድምጻቸውን የሚያሰሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ስላለው የኑሮ ውድነት ለኑሮ ውድነቱ እምብዛምት ትኩረት አልሰጡትም የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል።
የፖለቲካ ወይስ የምጣኔ ሃብት መፍትሔ?
ኬንያዊው የተቃዋሚ ፓርቲ ራይላ ኦዲንጋ ከሰሞኑ ገዢው ፓርቲ ኬንያውያንን ለከፋ የምጣኔ ሃብት ችግር ዳርጓል ብለው ደጋፊዎቻቸው ለተቃውሞ አደባባይ እንዲወጡ ጠርተው ነበር።
ደጋፊዎቻቸው ‘ባባ’ እያሉ የሚጠሯቸው ኦዲንጋ፤ ምንም እንኳ አሁን ተቃውሞውን ገታ ቢያደርጉትም “ለአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ችግር መፍትሔ ማበጀት ከሚችሉ ሰዎች መካከል ነኝ” እያሉ ነው።
ለመሆኑ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ለፖለቲካዊ ችግር መፍትሔ ይሆናል? ወይስ ፖለቲካው ለምጣኔ ሃብት ችግር መፍትሔ ያመጣል?
የምጣኔ ሃብት ተንታኙ ዋስይሁን በላይ በቀደመው ጊዜ የመገናኛ ብዙኃንም ሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምጣኔ ሃብት ትንተና የሚሰጡት ትኩረት ያነሰ ነበር ይላሉ።
በምርጫ ክርክር ወቅት እንኳ ፓርቲዎች “ድህነትነት እንቀንሳለን” ከማለት ውጪ “እንዴት?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ እንዳልነበራቸው ያወሳሉ።
‘ዘ ኢትዮጵያን ኢኮኖሚስት ቪው’ በተሰኘ የማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው ምጣኔ ሃብታዊ ትንታኔዎችን የሚሰጡት ባለሙያው “በልቶ የማደር ጥያቄ እያለ ሰዎች እያተኮሩ ያሉት ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ነው” ይላሉ።
“እኛ አገር ኢኮኖሚያዊ ችግርን ዋጥ አድርጎ የማለፍ ልምድ አለ። ለምሳሌ የጎረቤት አገራት ትንሽ የኢኮኖሚ ችግር ካለባቸው ጥያቄዎች ሲያነሱ ይሰማል። የምጣኔ ሃብት ጥያቄ መሠረታዊ ተደርጎ አይታይም፤ ቅድሚያም አይሰጠውም።”
ነገር ግን ተንታኙ እንደሚሉት “ብዙ ያላለቁ የፖለቲካ የቤት ሥራዎች” አሉ።
ምጣኔ ሃብት መገንባት የሚችለው በጠንካራ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ እንደሆነ የሚያስረግጡት ዋስይሁን “ጥሩ የፖለቲካ መድረክ መፍጠር ከተቻለ የምጣኔ ሃብት ዕድገት መረጋገጥ ይችላል” ይላሉ።
ቢሆንም...ይላሉ ምሑሩ፤ “ቢሆንም የፖለቲካ ሁኔታው የሃብት ክፍፍልን፣ የምርት ሥርዓት እና ሥርጭትን ሊቆጣጠር እንዲሁም ሊያስተካክል ይችላል። ፖለቲካው ከተረጋጋ ኢኮኖሚው ሊረጋጋ ይችላል በማለት ከምጣኔ ሃብት ይልቅ ለፖለቲካው ቅድሚያ የተሰጠው ይመስለኛል።”
ዋስይሁን እንደሚሉት የኢኮኖሚ ጥያቄን ከፖለቲካ መዋቅር (ስትራክቸር) ውጭ መመለስ የሚቻል አይደለም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያወጣው በፖለቲካው ኃይል በተመረጠው ቡድን መሆኑ ነው ይላሉ።
“የፖለቲካ ሰዎች በሚወስኑት ውሳኔ ነው ምጣኔ ሃብት ማደግ የሚችለው። አንድ አካባቢ ያለ የፀጥታ ሁኔታ ካልተጋጋ በቀር የአካባቢው ሰዎች ምርታማ ሊሆኑ አይችሉም።”
ነገር ግን በአንዳንድ አገራት ምጣኔ ሃብት ለማሳደግ ሲባል የፖለቲካ መሪዎች ‘መረር’ ያለ ፖሊሲ ሊያወጡ እንደሚችሉ ቻይናን በምሳሌነት በማንሳት ያብራራሉ።
“የኮሚዩኒስት ፓርቲው [የቻይና] መሬት አስተዳዳርን በተለመከተ ፖሊሲ ያወጣል፤ የውጭ ግንኙነቱን ይመራል፤ የገንዘብ ሥርጭትን ይቆጣጠራል። ለምሳሌ ቻይን ከአንድ በላይ ልጅ መውለድ አይቻልም የሚል ፖሊሲ ነበራት። ምዕራባዊያኑ ይህን ተቃውመውት ነበር። ነገር ግን ይህ ከምጣኔ ሃብት ዕድገት አይበልጥም ብለው ነው የወሰኑት። አሁን የቻይና ምጣኔ ሃብት የት እንደደደረሰ መመልከት እንችላለን።”
ጠንካራ የፖለቲካ መሪ ከሌለ በቀር ጠንካራ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ማውጣት አይቻልም የሚለው የዋስይሁን ጠንካራ አቋም ነው።
“ኢኮኖሚስቶች የሚተገብሩት ፖለቲከኞች የፈጠሩትን የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ነው። ፖለቲከኞቹ የማያዛልቅ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ይዘው ከመጡ ቢተገበርም ዕድገት የለም።”












