የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም - አይኤምኤፍ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም - አይኤምኤፍ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES/AFP

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም - አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ በሚችለው ድጋፍ አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ የድርጅቱ ባለሥልጣናት አዲስ አበባ መሆናቸው ተዘገበ።

ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ አይኤምኤፍን ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር የነበራት ግንኙነት ተቀዛቅዞ መቆየቱ ይታወቃል።

የተቋሙ የባለሙያዎች ቡድን ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ ሊደረግላት ስለሚችለው ድጋፍ አስፈላጊውን “ቴክኒካዊ ሥራ ለማከናወን” ወደ አዲስ አበባ እንዳመራ ብሉምበርግ ዘግቧል።

በዚህ ሳምንት የተቋሙ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ቆይታ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት ካበቃ ከወራት በኋላ ሲሆን፣ አገሪቱም በግጭት እና በድርቅ የተጎዳውን ምጣኔ ሃብቷን እንዲያገግም ለማድረግ ጥረት በጀመረችበት ወቅት ነው።

ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ በተመለከተ ውይይት እና አስፈላጊውን ሁኔታ እንዲያመቻቹ የተላኩት የአይኤምኤፍ ባለሥልጣናት ለአስር ቀናት ያህል እንደሚቆዩ ብሉምበርግ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላት ተቋሙን እንደጠየቀች የአይኤምኤፍ ቃል አቀባይ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

“ሊሰጥ የሚችለው ድጋፍ አገሪቱ ለምታካሂደው አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ እና ምጣኔ ሀብቷን በማረጋጋት ለሰብአዊ ድጋፍ፣ ለሥራ ፈጠራ እና ለድህነት ቅነሳ የሚውል ይሆናል” ብለዋል ቃል አቀባዩ።

የአይኤምኤፍ ባለሥልጣናት በዚህ ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ የሚያደርጉት ቴክኒካዊ ውይይት፣ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና በተቋሙ መካከል ሰብአዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮችን ለማሻሻል የተደረገ ንግግር ተከታይ መሆኑን ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መካከል ሲካሄድ የነበረው የድጋፍ፣ የብድር ስረዛ እና ሽግሽግ ንግግር በከፊል በትግራይ ሲካሄድ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ ምላሽ ሳያገኝ ቆይቶ ነበር።

በመቶሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት እና በቢሊዮን ዶላሮች የሚያወጣ ውድመትን ያስከተለው የእርስ በርስ ጦርነት ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ተቋማት እና አገራት ታገኝ በነበረው ምጣኔ ሀብታዊ ድጋፍ ላይ ከፍተኛ ጫናን አስከትሎ ነበር።

ብሉምበርግ እንዳለው ኢትዮጵያ ጦርነቱ ያስከተለውን ውድመት መልሶ ለመገንባት እና የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመሸፈን አስፈላጊ ለሆኑ የገቢ ምርቶች ክፍያ ለመፈጸም ድጋፍ ያስፈልጋታል።

ጦርነቱ ካስከተለው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት ባሻገር በአፍሪካ ካሉ የመዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች መዳረሻ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን እና ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተነሳ ከዓለም ባንክ አንዲሁም ከአይኤምኤፍ የምታገኘውን ድጋፍ ገትቶት መቆየቱን ብሉምበርግ ዘግቧል።

በጦርነቱ እና በዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር የገጠማት ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ከመመዝገቡ በላይ እጥረትም ተከስቷል።

ጥቅምት መጨረሻ ላይ ደቡብ አፍሪካ ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈረመውን ዘላቂ ግጭትን የማቆም ስምምነትን ተከትሎ ጦርነቱ ቆሞ በሰሜን ኢትዮጵያ የሕዝቡን ሕይወት ወደ መደበኛው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው።

በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት 20 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፍልግ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በቅርቡ ተናግረዋል።