ጆ ባይደን የቻይናውን ፕሬዝዳንት ‘አምባገነን’ ሲሉ ጠሩ

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ሺንፒንግን ‘አምባገነን’ ሲሉ ገለጿቸው።

ባይደን የቻይናውን ፕሬዝዳንት በተመለከተ ይህን አስተያየት የሰጡት ትናንት በካሊፎርኒያ ገንዘብ ለማስባሰብ በተዘጋጀ ስነ-ስርዓት ላይ ነው።

ባይደን ጨምረውም በቅርቡ የቻይና ሰላይ የተባለች ፊኛ አሜሪካ ሰማይ ላይ ታይታ ተመትታ እንድትወድቅ መደረጓ ሺ ሺንፒንግን አሳፍሯል ብለዋል።

"በሰላለ መሳሪያዎች የተሞላችውን ፊኛ መትቼ በመጣሌ ሺ ሺንፒንግ በጣም የተበሳጨው፤ ፊኛው እዛ እንዳለ አላወቀም” ብለዋል ባይደን።

“ይህ ለአምባገነኖች ትልቅ ውርደት ነው። ምን እንደተፈጠረ ሳያውቁ ሲቀሩ” ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።

የባይደን አስተያየትን ተከትሎ ቻይና በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሰጠችው አስተያየት የለም።

ይህ የባይደን አስተያየት የመጣው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ከፕሬዝዳንት ሺ ጋር በቤይጂንግ ከተነጋገሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

ከዚህ ውይይት በኋላ ሺ በሰጡት አስተያየት አዎንታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል ያሉ ሲሆን ብሊንከን በበኩላቸው አሁንም በሁለቱ አገራት መካከል መሠረታዊ ልዩነቶች መኖራቸው ገልጸው ተጨማሪ ንግግሮችን ለማድረግ ግን በሁለቱም ወገን ፍላጎት አለ ብለዋል።

የብሊንከን የቤይጂንግ ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካከል የከፍተኛ ባለስልጣናት ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ንግግር መንገድን ከፍቷል።

ዋሽንግተን እና ቤይጂንግ በንግድ፣ በቻይና ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና በታይዋን ጉዳይ ልዩነቶቻቸው ሰፍተው ውጥረት ውስጥ ከገቡ በርካታ ጊዜያት አልፈዋል።

ቻይና ታይዋን አንድ የራሴ ግዛት አካል ነች የምትል ሲሆን አስፈላጊ ከሆነም በኃይል ጠቅልዬ እወስዳታለሁ ትላለች።

በሌላ በኩል የራሷ የሆነ ሕገ-መንግሥት ያላት፣ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡ መሪዎች እና ከ300 ሺህ ያላነሰ የጦር ሠራዊት ባለቤት ከሆነችው ታይዋን እራሷን እንደ ሉዓላዊ ግዛት የምትቆጥር ሲሆን የአሜሪካም ጠንካራ ድጋፍ አላት።

ከወራት በፊት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ታይዋን ከቻይና ጥቃት ቢሰነዘርባት ታይዋንን ትከላከላለች ብለው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ በቻይና በገፍ እየተመረተ በአሜሪካ ገበያ እየቀረብ በርካቶችን ለከፋ ጉዳት እያጋለጠ ነው ይባላል።