የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ያቋረጠውን የምግብ እርዳታ ሊያስቀጥል እንደሚችል ተጠቆመ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን የምግብ እርዳታ ሊያስቀጥል እንደሚችል ተጠቆመ።
ተረጂዎች በምን መልኩ እንደሚመረጡ የሚያስችለው ቁጥጥር ማደግ ከቻለ በሚቀጥለው ወር የተወሰኑ የምግብ እርዳታዎችን ማቅረብ ሊጀምር እንደሚችል አንድ ከፍተኛ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለሥልጣንን ዋቢ በማድረግ ሮይተርስ ዘግቧል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የእርዳታ ምግብ ላልተገባ ዓላማ በመዋሉ የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ ሰኔ 02/2015 ዓ.ም. ማቋረጡ ይታወሳል።
በረሃብ ለተጎዱ ሰዎች የተላከ እርዳታ በከፍተኛ ሁኔታ ዝርፊያ ተፈጽሞበታል፣ እንዲሁም ሽያጭ ላይ ውሏል በሚል የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅትም (ዩኤስኤአይዲ) ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዱ ተዘግቧል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የፖሊሲ ልማት ረዳት ዋና ዳይሬክተር ቫለሪ ጓርኒየር ተቋሙ ማን መረዳት አለበት የሚለውን የአካባቢው እና የክልል መንግሥት ባለሥልጣናት ያላቸውን የወሳኝነት ሚና መቀነስ እንደሚፈልግ መናገራቸው በዚሁ ዘገባ ላይ ሰፍሯል።
“ተረጂዎችን በመምረጥ ሂደት እኛ እንደ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ እንዲሁም አጋር የሆኑት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች የበለጠ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖረን እንፈልጋለን” ሲሉ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም መርማሪዎች በድርጅቱ የክትትል ሥርዓቶች ላይ ያሉ ድክመቶችን በተለይም በትግራይ ክልል ለይተው ማወቃቸውንም ተናግረዋል።
በህወሓት እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎም ተቋርጠው የነበሩ የእርዳታ አቅርቦቶች እንደገና በክልሉ መጀመራቸው ይታወሳል።
ተቋሙ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት አዎንታዊ መልስ ካገኘ በትግራይ እና በስደተኛ መጠለያ ካምፖች የሚደረገው እርዳታ በመጪው ሐምሌ ወር አጋማሽ ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁመው፣ በአጠቃላይ እርዳታው በፍጥነት እንደገና እንደሚጀመር ተስፋ አድርገዋል።
የረድዔት ድርጅቶቹ እርዳታው በትግራይ ክልል በረሃብ ለተጎዱ ሰዎች ሳይሆን፣ ከታለመለት ዓላማ ውጪ ገበያ ላይ ለሽያጭ መቅረቡን፣ እንዲሁም ስርቆት ተፈጽሟል በሚል በተመሳሳይ ሁኔታ ባለፈው ወር አቅርቦቱ መቋረጡ ይታወሳል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተቋቋመ ኮሚቴ በክልሉ ለተረጂዎች መድረስ የነበረበት እርዳታ ላልተገባ ዓላማ ከመዋሉ ጋር ባደረገው ምርመራ የፌደራል መንግሥት አካላት እና የኤርትራ ኃይሎች ሰፊ ሚና እንደነበራቸው ከሰሞኑ በወጣው ሪፖርት አመላክቷል።
የምርመራ ኮሚቴው አስተባባሪ እና የክልሉ የሰላም እና የፀጥታ ቢሮ ጊዜያዊ ኃላፊ ጄኔራል ፍስሐ ኪዳኔ ለትግራይ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት እርዳታውን ላልተገባ ዓላማ በማውሉም የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት፣ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ አስተባባሪዎች እና የእርዳታ ሠራተኞችም ተሳትፈውበታል ብለዋል።
ኮሚቴው የፌደራል መንግሥት አካላት፣ የኤርትራ ኃይሎች እንዲሁም የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ላልተገባ ጥቅም አውለውታል ያለውን ስንዴ፣ አተርና ዘይትም መጠን በዝርዝር ጠቅሷል።
ይህንን ክስ በተመለከተ የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የኤርትራ መንግሥት የሰጡት ምላሽ የለም።
ሆኖም ዩኤስኤአይዲ የእርዳታ አቅርቦት ማቋረጡን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት የተወሰደውን የእርዳታ አቅርቦትን የማቋረጥ ውሳኔ ‘ፖለቲካዊ’ ነው ሲል ተቃውሞታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ባለፈው ሳምንት እርምጃው “የጅምላ ውሳኔ” መሆኑን በመግለጽ፣ በዚህም ሚሊዮኖችን መቅጣት “ፖለቲካዊ እንጂ ሰብአዊ ገጽታ የለውም” ብሎ መንግሥታቸው እንደሚያምን አመልክተዋል።
ሮይተርስ ተመልክቼዋለሁ ባለው የውጭ አገራት ለጋሽ ድርጅቶች ውስጣዊ ማስታወሻ፣ የምግብ እርዳታዎች ለኢትዮጵያ ሠራዊት መቅረቡን የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት ያምናል ብሏል።
“በፌደራል እና በክልል የመንግሥት አካላት አቀናባሪነት በመላው አገሪቱ ያሉ ወታደራዊ ክፍሎች ከሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ ተጠቃሚ ሆነዋል” በማለት ዩኤስኤአይዲ አባል የሆነበት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ቡድኖች ሰነድ አመልክቷል።
ለተረጂዎች መድረስ የነበረበት የምግብ እርዳታ ላይ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ መፈጸሙ በምርመራ መረጋገጡን እና የአሜሪካ መንግሥትም በዚህ ምክንያት እርዳታውን ማቋረጡን ዋሽንግተን ፖስት በቅርቡ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል።
ለለጋሾች የተሰጡ እና ዋሽንግተን ፖስት የተመለከታቸው ሾልከው የወጡ ሰነዶች እንደሚያመለከቱት የእርዳታ ዝርፊያው በፌደራል እና በክልል መንግሥታት አካላት የተቀነባበሩ ናቸው ብሏል።
በዚህም መሠረት ለተራቡ ተጎጂዎች የተላከውን እርዳታ ባለሥልጣናቱ ለጦር ሠራዊቱ እና ለቀድሞ ተዋጊዎች ሲመግቡ ነበር ብሏል።
በተጨማሪም እርዳታው በገበያ ላይ የተሸጠ ሲሆን ነጋዴዎችም ፈጭተው ወደ ውጭ አገራት ማከፋፈላቸውንም የዩኤስኤይዲ ምርመራ ማመላከቱንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሥልጣን ለዋሽንግተን ፖስት መግለጻቸው ተዘግቧል።
በተመሳሳይ ከዚሁ የእርዳታ ምግብ አቅርቦትን ከታሰበለት ዓላማ ውጪ ተጠቅሟል በሚል ስሙ የተነሳው የመከላከያ ሠራዊትን በተመለከተ የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የቀረበበትን ክስ አስተብብሏል።
ሚኒስቴሩ እንዳለው ሠራዊቱ አስፈላጊው አቅርቦት እና ድርጅት ያለው መሆኑን አመልክቶ፣ በመሆኑም በውስጡ “ለእርዳታ ተብሎ የቀረበን ስንዴ የሚጠቀም ተቋም ወይም ዩኒት ወይም ወታደር የለም” ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል።
በአፍሪካ ቀንድ ለአራት አስርት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
የረድዔት ድርጅቶቹ የሚያደርጉት እርዳታ መቋረጡንም ተከትሎ በትግራይ ክልል በምግብ እጥረት ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩንና ሁኔታዎች መክፋታቸው ተዘግቧል።
በክልሉ ባለፉት አምስት ወራት በምግብ እጥረት 13 ሕጻናት መሞታቸውን የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ለቢቢሲ ተናግሯል።
በመቀለ በሚገኘው የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ገብተው ሕክምና ሲደረግላቸው ከነበሩት መካከል በግንቦት ወር ብቻ ሰባት ሕጻናት ሕይወታቸው ማለፉንም የሕክምና ባለሙያዎች ገልጸዋል።












