የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ ማቋረጥ ‘ፖለቲካዊ’ እርምጃ ነው ሲል ተቃወመ

የእርዳታ ምግብ የሚሰፍሩ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት - ዩኤስኤአይዲ የተወሰደውን የእርዳታ አቅርቦትን የማቋረጥ ውሳኔ ‘ፖለቲካዊ’ ነው ሲል ተቃወመ።

ዩኤኤአይዲ በአገሪቱ ለተረጂዎች የሚያቀርበው የምግብ እርዳታ ከታለመለት ዓላማ ውጪ ጥቅም ላይ መዋሉን በመግለጽ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያሂደውን የእርዳታ አቅርቦት ማቋረጡን ከቀናት በፊት አሳውቆ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 03/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ላይ፣ ውሳኔው በመንግሥት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመግለጽ ተችተውታል።

ሚኒስትሩ እርምጃው “የጅምላ ውሳኔ” መሆኑን በመግለጽ፣ በዚህም ሚሊዮኖችን መቅጣት “ፖለቲካዊ እንጂ ሰብአዊ ገጽታ የለውም” ብሎ መንግሥታቸው እንደሚያምን አመልክተዋል።

በተጨማሪም የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማትን መልካም ስም አጉድፏል ሲሉ ዶክተር ለገሰ ወቅሰዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ድርጅት ለተረጂዎች የታለመውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ከታለመለት ዓላማ ውጪ በማዋሉ በኩል የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ተቋማትን እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱ ተሳታፊ መሆናቸውን አመልክቶ ነበር።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ የምግብ እርዳታ አቅርቦት ያላግባብ ጥቅም ላይ መዋሉን በተመለከተ የሚደረገውም ምርመራ ሳይጠናቀቅ ዩኤስኤአይዲ ያወጣው መግለጫ የፌደራል፣ የክልል መንግሥታትን እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱን “መልካም ገጽታን የሚያጠለሽ ነው” ብለዋል።

ሚኒስትሩ ጨምረውም ምርመራ በተደረገባቸው ቦታዎች የእርዳታ አቅርቦቱ እና ሥርጭቱ በራሱ መዋቅር የሚከናወን ሆኖ ሳለ “ዩኤስኤአይዲ መንግሥትን ብቻ ተጠያቂ ለማድረግ የተጓዘበት ርቀት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም” በማለት ተቃውመውታል።

የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው “ለኢትዮጵያ ሕዝብ መቅረብ የነበረበት የምግብ እርዳታ በከፍተኛ መጠን እና በተቀናጀ ሁኔታ ከታቀደለት አላማ ውጪ ጥቅም ላይ በመዋሉ” መሆኑን ገልጿል።

የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት ውሳኔውን ባሰወቀበት ጊዜ “የተደረገውን አገር አቀፍ ቅኝት ተከትሎ ዩኤስኤአይዲ፣ በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ ለውጥ እስኪደረግ ድረስ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል፣ አስቸጋሪ ነገር ግን አስፈላጊ ውሳኔ አሳልፈናል” ማለቱ ይታወሳል።

የሰብአዊ እርዳታ ምግብ ከታለመለት አላማ ውጪ “በፌደራል እና በክልል የመንግሥት አካላት ተባባሪነት በመላው አገሪቱ ላሉ ለኢትዮጵያ ሠራዊት ክፍሎች ቀርቧል” ብሎ የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት እንደሚያምን ሮይተርስ ተመለከትኩት ያለው አንድ ሰነድ ማመልከቱን ዘግቦ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፉት ሁለት ወራት የተካሄደ ምርመራ በለጋሾች የተገዛ የምግብ እርዳታ ከታለመለት አላማ ውጪ መዋሉን እና ለገበያ መቅረቡን እንዲሁም በአንዳንድ ሁኔታዎችም ወደ ውጪ አገራት ጭምር መላኩን ብሉምበርግ ተመለከትኩት ያለው ሰነድ አሳይቷል።

ይህንንም ተከትሎ ዩኤስኤአይዲ በመላው ኢትዮጵያ በግጭት እና በድርቅ ምክንያት በእርዳታ ጥገኛ ለሆኑ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ መቋረጡን ያሳወቀ ሲሆን፣ መንግሥት ግን ውሳኔውን ተቃውሞታል።

በተመሳሳይ ከዚሁ የእርዳታ ምግብ አቅርቦትን ከታሰበለት ዓላማ ውጪ ተጠቅሟል በሚል ስሙ የተነሳው የመከላከያ ሠራዊትን በተመለከተ የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የቀረበበትን ክስ አስተብብሏል።

ሚኒስቴሩ እንዳለው ሠራዊቱ አስፈላጊው አቅርቦት እና ድርጅት ያለው መሆኑን አመልክቶ፣ በመሆኑም በውስጡ “ለእርዳታ ተብሎ የቀረበን ስንዴ የሚጠቀም ተቋም ወይም ዩኒት ወይም ወታደር የለም” ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል።

የእርዳታ ምግብ አቅርቦትን አላግባብ ከመጠቀም ጋር በተያያዘ የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) አቅርቦቱን ማቋረጡን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራምም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዱን አርብ ዕለት አሳውቋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከአንድ ወር በፊት ለተረጂዎች የቀረበ ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ እርዳታ ለሌላ ዓላማ ውሏን በሚል በትግራይ ክልል ውስጥ ሲያካሂድ የነበረውን የምግብ አቅርቦት ማቋረጡ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እናዳለ የሰብአዊ እርዳታ ተቋሙ ‘ሪፊዩጂ ኢንተርናሽናል’ ለቢቢሲ በላከው መግለጫ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ “የእርዳታ አቅርቦት በከፍተኛ መጠን በተቀናጀ ሁኔታ ለሌላ አላማ መዋሉ” መታወቁን ተከትሎ፣ የአሜሪካ መንግሥት “ይህ አይነቱ ድርጊትን እንደማይታገስ” በግልጽ ማሳየት አለበት ብሏል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን በበኩሉ የእርዳታ አቅርቦት እንዲቋረጥ መደረጉ ሚሊዮኖችን ለችግር የሚዳርግ እና ለቀውስ የሚያጋልጥ በመሆኑ “እንደማይቀበለው” በመግለጽ ውሳኔው መለስ ተብሎ እንዲጤን ጠይቋል።

እንዲሁም በዚህ የእርዳታ አቅርቦትን ከታለመለት ዓላማ ውጪ እንዲውል በማድረግ በኩል የተሳተፉ አካላት በምርመራ በማስረጃ ተረጋግጦባቸው ሲገኝ እርምጃ ለመውሰድ መንግሥት ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በግጭት እና በድርቅ ምክንያት የእርዳታ ድጋፍን የሚሹ ወደ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች እንዳሉ ይነገራል።

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሊዮኖች ከፍተኛውን ሰብአዊ እርዳታን በማቅረብ ዋነኛው ሲሆን፣ የእርዳታ አቅርቦቱ ሥርዓት አስተማማኝ መሆኑ ከተረጋገጠ እርዳታውን መልሶ እንደሚጀመር ገልጿል።