ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ የተደረጉት በሙሉ ስደተኞች ወይም ጥገኝነት ጠያቂዎች አይደሉም ተባለ

ኤርትራውያን ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, UNHCR/PETTERIK WIGGERS

የስደተኞች እና ከስደተኞች ተመላሾች አገልግሎት ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ የተደረጉት በሙሉ ስደተኞች ወይም ጥገኝነት ጠያቂዎች አይደሉም አለ።

አገልግሎቱ ይህን ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቅርቡ በኃይል ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ የተደረጉ ኤርትራውያን ጉዳይ አሳስቦኛል ማለቱን ተከትሎ ነው።

ኢሰመኮ ሕጻናትን ጨምሮ ወደ 200 የሚጠጉት ኤርትራውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በኃይል ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ ከተደረጉ በኋላ ደኅንነታቸው አሳሳቢ ነው ብሏል።

ኮሚሽኑ ቅዳሜ ሰኔ 17/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ‘ያለመመለስ መርኅ’ ማንኛውም ሰው ስቃይ፣ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ፣ ኢሰብዓዊ ወይም አዋራጅ አያያዝ አልያም ቅጣት እና ሌላ ጉዳት ሊጠብቀው ወደሚችለው አገር መመለሰን ይከለክላል ብሏል።

ኮሚሽኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ኤርትራውያኑ ኢትዮጵያ ያሉት ‘ሕጋዊ ሳይሆኑ ነው’ በሚል ምክንያት በኃይል ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ያደረጋቸውን ኤርትራውያንን በተመለከተ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ማጣራቱን እንደሚቀጥል አመለክቷል።

ይህን የኢሰመኮ መግለጫ ተከትሎ የኢፌድሪ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት በሰጠው ምላሽ ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉት ኤርትራውያን በሙሉ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አይደሉም ብሏል።

አገልግሎቱ እሁድ ሰኔ 18/2015 ዓ.ም. ባወጠው መግለጫ የኢሰመኮ መግለጫ “የስደተኞችን እና የጥገኝነት ጠያቂዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚወሰደውን ጥብቅ እርምጃዎች የዘነጋ ነው” ብሎታል።

አገልግሎቱ የስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ “እንደመቋቋሜ የየትኛውም ስደተኛ እና ጥገኝነት ጠያቂን ደኅንነት ለማስጠቅ ጥብቅ እርምጃዎችን እወስዳለሁ” ካለ በኋላ፤ በስህተት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉ 4 ስደተኞች ወይም ጥገኝነት ጠባቂዎች ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ እየተደረጉ ነው መሆናቸውን ገልጿል።

ኤርትራውያኑ ወደ ትውልድ አገራቸው መቼ እና ከየትኛው የኢትዮጵያ ክፍል ተይዘው እንዲመለሱ ስለመደረጋቸው የተባለ ነገር የለም።

ይሁን እንጂ ኢሰመኮ ግንቦት 25/2015 ዓ.ም. አውጥቶት በነበረው መግለጫ፣ በተለይ በአዲስ አበባ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ለእስር ተዳርገዋል ብሎ ነበር።

ኤርትራውያኑ ለእስር የተዳረጉት “ስደተኛ መሆናቸውን የሚገልጽ የሰነድ ማስረጃ አለመያዝ፣ ከመጠለያ ካምፕ ያለፍቃድ መውጣት እንዲሁም ያለ ሥራ ፍቃድ በሥራ መሰማራት የሚሉ ምክንያቶች እንደሚገኙበት” ኮሚሽኑ ገልጾ ነበር።

እነዚህ በቁጥር ወደ 200 የተገመቱት ኤርትራውያን አገራቸው ከደረሱ በኋላ ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።

ከዚህ ቀደም ከሰሜን አፍሪካ አገራት ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ የተደረጉ ስደተኞች ለእስር ተዳርገው እንደነበር መገለጹ ይታወሳል።

የፖለቲካ እና የፕሬስ ነጻነት የለባትም፣ ሰዎች የፈቀዱትን ሃይማኖት እንዳይከተሉ ይከለከላሉ እንዲሁም አስገዳጅ የብሔራዊ አገልግሎት ታካሂዳለች ተብላ በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ከምትከሰሰው ኤርትራ በመሸሽ በርካቶች አገር ጥለው ይሰደዳሉ።

በዚህም ምክንያት አገራት ኤርትራውያንን ወደ ትውልድ አገራቸው በኃይል ሲመልሱ እምብዛም አይስተዋልም።