አሜሪካ የቫግነር ቡድን አመጽ በፑቲን ሥልጣን ላይ ተጨባጭ አደጋን የጋረጠ ነው አለች

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, SPUTNIK

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሩሲያ ያጋጠመው ክስተት በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ውስጥ ያለውን ትልቅ ክፍተት ያሳየ ነው አሉ።

ብሊንከን ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት የቫግነር ቡድን በፈጸመው የአመጽ ድርጊት ፑቲንን “በቀጥታ በመገዳደር” ፕሬዝዳንቱ ለቡድኑ መሪ እና አባላት ይቅርታ አድርገው ከስምምነት እንዲደርስ ያስገደደ ነው ብለዋል።

በየቭጌኒ ፕሪጎዢን የሚመራው ቡድን በሩሲያ የጦር አመራሮች ላይ በይፋ ካመጸ በኋላ፣ ሁለት የሩሲያ ከተሞችን ተቆጣጥሮ ወደ ሞስኮ ሲገሰግስ ነበር።

ይሁን እንጂ የቡድኑ መሪ በቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሸማጋይነት ከፑቲን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ወደ ሞስኮ የሚያደርጉትን ዘመቻ አቁመዋል።

በምላሹም የፑቲን አስተዳደር በቫግነር ቡድን አባላት ላይ ክስ እንደማይመሰርት የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ይፋ አደርገዋል።

በስምምነቱ መሠረት የቫግነር ተዋጊዎች ወደ ጦር ካምፖቸው እንዲመለሱ እንዲሁም የቭጌኒ ፕሪጎዢን ወደ ጎረቤት አገር ቤላሩስ እንዲያቀኑ ከስምምነት ተደርሷል።

ከዚህ ስምምነት በኋላ የፑቲን የቀድሞ የቅርብ አጋር የቭጌኒ ፕሪጎዢን የት እንደሚገኙ በትክክል አይታወቅም።

የቫግነር መሪ ለመጨረሻ ጊዜ በይፋ የታዩት ቡድናቸው ተቆጣጥሯት የነበረችውን ሮስቶቭ-ኦን-ዶን ከተማን ለቅቀው ሲወጡ ነበር።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለሲቢኤስ ቴሌቪዥን ሲናገሩ፣ በሩሲያ ለ24 ሰዓታት የቆየው አመጽ በፑቲን አስተዳደር ላይ ጥርጣሬያን የሚያጭሩ መሠረታዊ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነው ካሉ በኋላ፤ ክስተቱ በፑቲን ሥልጣን ውስጥ “ትልቅ ክፍተት” መኖሩን ያሳያል ብለዋል።

ብሊንከን ይህ የቫግነር ቡድን አመጽ በክሬምሊን ወይም ደግሞ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወረራ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ምን ሊሆን እንደሚችል አሁን ላይ ለመገመት ጊዜው ገና ነው ብለዋል።

“ይህን ከ16 ወራት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ስናነጻጽረው፤ ፑቲን የዩክሬን መዲና ኪዬቭን ለመቆጣጠር ከጫፍ ደርሶ ነበር፤ ከተማዋን ለመያዝ ቀናት ብቻ ቀርተውት ነበር፤ አገሪቱን ከዓለም ካርታ ላይ ለመሰረዝ ተቃርቦ ነበር” ያሉት ብሊንከን፤ “አሁን ግን የሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮን ከራሱ ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን መከላከል ነበረበት” ብለዋል።

ይህን የብሊንከን አስተያየትን ተከትሎ ሩሲያ ያለችው ነገር የለም።

የቢቢሲ የሩሲያ አገልግሎት አርታዒ ስቲቭ ሮሰንበርግ አርብ እና ቅዳሜ በሩሲያ ያጋጠመው ክስተት ፕሬዝዳንት ፑቲን ጠንካራ መሪ አድርጎ ላያሳይ ይችላል ይላል።

ስቲቭ የቫግነር ቅጠረኛ ቡድን መሠረታዊ የሚባሉ የሩሲያ ጦር ማዘዣዎችን በቀላሉ ተቆጣጥሮ ወደ ሞስኮ ግስጋሴ ጀምሮ እንደነበር አስታውሶ፤ የሩሲያ ወታደራዊ አመራሮችን ገለብጣለሁ ብሎ ሲዝት የነበረው እና በሩሲያ ለሰዓታት የዘለቀ ትርምስ የፈጠረው የቭጌኒ ፕሪጎዢን አሁን ላይ ነጻ ሰው ነው ይላል።