የሕዝብ ቁጥሯ ክፉኛ ያሽቆለቆለባት ደቡብ ኮሪያ ዜጎቿ መውለድ የማይፈልጉት ለምንድን ነው?

ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ የደቡብ ኮሪያዋ ዋና ከተማ ሴዑል በዝናብ እየታጠበች ነው። ዬጂን ለጓኞቿ ምሳ እያበሰለች ነው። የትዳር አጋርም ሆነ የፍቅር ጓደኛ የላትም።
ምሳው ደርሶ መመገብ ጀመሩ። ጓደኛዋ ከስልኳ ላይ የዳይኖሰር ምስል ታሳያቸው ጀመር። “ተጠንቀቅ! እንደ እኛ መጥፋትን አትፍቀድ” የሚል ጽሑፍ ምስሉን አጅቦታል።
ሴቶቹ ሁሉ ምስሉን እና ጽሑፉን አይተው ሳቁ።
የ30 ዓመቷ ዬጂን የቴሌቪዥን ፕሮዲዩሰር ናት። “በጣም የሚያስቅ ነገር ቢሆንም መልዕክቱ መራራ ነው። ምክንያቱም ለራሳችን መጥፋት መንስኤ እንደምንሆን እናውቀዋለን” ትላለች።
እሷም ሆነች ጓደኞቿ ልጅ የመውልድ ዕቅድ ከሌላቸው ሴቶች መካከል ናቸው።
ደቡብ ኮሪያ በዓለም ዝቅተኛው የወሊድ መጠን ያላት አገር ናት። አሃዙም ከዓመት ዓመት ማሽቆልቆሉን ቀጥሏል።
የ2023 (እአአ) አሃዝም 8 በመቶ ቀንሶ ወደ 0.7 መውረዱን ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ አንዲት ሴት በሕይወቷ ዘመኗ የምትወልዳቸው ልጆች ቁጥር ነው። የአንድ አገር የሕዝብ ቁጥር እንዲረጋጋ አሃዙ 2.1 መሆን አለበት።
የቁጥሩ መቀነስ በዚሁ ከቀጠለ እአአ በ2100 የሰሜን ኮሪያ ሕዝብ በግማሽ እንደሚቀንስ ይገመታል።

“ብሔራዊ አደጋ”
በዓለም አቀፍ ደረጃ የበለፀጉ አገራት የወሊድ ምጣኔ እየቀነሰ ነው። ማናቸውም ግን ከደቡብ ኮሪያ ጋር አይነጻጸሩም።
ትንበያዎቹ አስፈሪ ናቸው።
በ50 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለሥራ የደረሱ ሰዎች ቁጥር በግማሽ ይቀንሳል። በአገሪቱ አስገዳጅ የውትድርና አገልግሎት ለመሳተፍ ብቁ የሚሆኑት ደግሞ በ58 በመቶ ይቀንሳል። ግማሽ የሚጠጋው የአገሪቱ ሕዝብ ዕድሜ ከ65 ዓመት በላይ ይሆናል።
ይህ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት፣ የጡረታ ዕዳ እና ደኅንነትን ክፉኛ የሚጎዳ በመሆኑ ፖለቲከኞች “ብሔራዊ አደጋ” ሲሉ አውጀዋል።
ወደ 20 ለሚጠጉ ዓመታት መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ 286 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ አድረጓል።
ልጆች ያሏቸው ጥንዶች ከወርሃዊ ስጦታዎች እስከ ቤቶች ድጎማ እና ነፃ ታክሲ እስከመጠቀም የሚደርስ ሽልማት ይጎርፍላቸዋል።
በሆስፒታል እና በሳይንሳዊ ዘዴ ከወላጆች በሚገኝ ዘር ፍሬ ልጅ ለማግኘት ሲሞክሩም ክፍያቸውም ይሸፈንላቸዋል። ይህ ግን በትዳር ለተጠማሩት ብቻ የተዘጋጀ ነው።
እንደዚህ አይነት የገንዘብ ማበረታቻዎች ፍሬያማ አልሆኑም። ፖለቲከኞች ከደቡብ ምሥራቅ እስያ የመጡ ህጻናት ጠባቂዎችን መቅጠር እና 30 ዓመት ሳይሞላቸው ሦስት ልጆች የወለዱትን ከአስገዳጅ ወታደርነት አገልግሎት ነፃ ማድረግን የመሳሰሉ የ“ፈጠራ” መፍትሔዎችን እንዲያቀርቡ አድርጓቸዋል።
በሚያስገርም ሁኔታ ግን ፖሊሲ አውጪዎች ወጣቶችን በተለይም ሴቶች ያላቸውን ፍላጎት አይሰሙም ተብሏል።
ዬጂን በ20ዎቹ የዕድሜዋ አጋማሽ ብቻዋን ለመኖር ስትወስን የማኅበራዊ ደንቦችን ጥሳ ለመውጣት ተገዳለች። ኮሪያ ውስጥ ጥንድ ሳይሆኑ መኖር በአብዛኛው ጊዜያዊ ምዕራፍ ይቆጠራል።
ከዚያ ከአምስት ዓመት በፊት ደግሞ ላለማግባት ወሰነች። በተዘዋዋሪ ልጅ ላለመውለድ ወሰነች ማለት ነው።
“በኮሪያ ውስጥ የቤት ውስጥ ሥራዎችን እና የልጅ እንክብካቤን በእኩልነት የሚጋራ ወንድ ማግኘት ከባድ ነው። የሕይወት አጋር ሳይኖራቸው የወለዱ ሴቶች በጥሩ መንፈስ አይታዩም” ብላለች።
እአአ በ2022 በደቡብ ኮሪያ ከተወለዱት ውስጥ 2 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ከጋብቻ ውጭ የተወለዱት።

“ዘላለማዊ የሥራ ዑደት”
ከዚህ ይልቅ ዬጂን በቴሌቪዥን ሥራዋ ላይ ትኩረት ማድረግን መርጣለች። ይህም ልጅ ለማሳደግ በቂ ጊዜ እንደማይሰጣት ትገልጻለች። በኮሪያ የሥራ ሰዓታት ረዥም ናቸው።
ዬጂን ከጠዋት 3 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ትሠራለች። ብዙ ጊዜ ግን ከቢሮዋ እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት አትወጣም። በዚያ ላይ የትርፍ ሰዓት ሥራ እንደምትሠራ ትናገራለች። ቤቷ ስትመለስም ከመተኛቷ በፊት ቤቱን ለማጽዳት ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚሆን ጊዜ ብቻ ነው የሚኖራት።
“ሥራዬን እወዳለሁ፤ ደስታን ይፈጥርልኛል። ኮሪያ ውስጥ መሥራት ግን ከባድ ነው። ሕይወት በዘላለማዊ የሥራ ዑደት ውስጥ ትጣበቃለህ” ትላለች።
ዬጂን የሥራ ዕድገት ለማግኘትም በትርፍ ጊዜዋ ትማራለች። “ኮሪያውያን እራስን በማሻሻል ላይ ያለማቋረጥ ካልተሠራ ወደ ኋላ ይቀራል የሚል አስተሳሰብ አላቸው። የውድቀት ፍርሃት እጥፍ ድርብ እንድንሠራ ያደርገናል።”
“አንዳንድ ጊዜ ቅዳሜ እና እሁድ ሄጄ ጉልኮስ በጠብታ መልክ አገኛለሁ። ይህም ሰኞ ወደ ሥራ ለመመለስ በቂ ጉልበት ለማግኘት ያግዘኛል” ስትል ታክላለች።
እሷም ልጅ ለመውለድ እረፍት ከወሰድኩ ወደ ሥራ መመለስ አልችልም የሚለውን የሌሎችን ሴቶች ፍራቻ ትጋራለች።
“ስንወልድ ሥራችንን መልቀቅ አለባችሁ የሚል ስውር ጫና ከኩባንያዎች እየደረሰብን ነው” ትላለች። በእህቷ እና በሁለት ተወዳጅ የዜና አቅራቢዎች ላይ ሲደርስም ተመልክታለች።
“ብዙ አውቃለሁ”
በሰው ሀብት አስተዳደር ውስጥ የምትሠራ አንዲት የ28 ዓመት ኮሪያዊት፣ ሴቶች ሥራቸውን እንዲለቁ ሲገደዱ ወይም የወሊድ ፈቃድ ከወሰዱ በኋላ የሥራ ዕድገት ሲያልፋቸው መታዘቧን ተናግራለች። ይህም ልጅ እንዳትወልድ በቂ ምክንያት ነበር።
በልጆቻቸው የመጀመሪያዎቹ ስምንት ዓመታት ውስጥ አባቶችም ሆኑ እናቶች የአንድ ዓመት ፈቃድ የማግኘት መብት አላቸው። እአአ በ2022 ግን ከአዲስ አባቶች 7 በመቶዎቹ ብቻ የተወሰነውን ፈቃድ ሲጠቀሙ፣ አዲስ እናቶች ደግሞ 70 በመቶውን ተጠቅመውበታል።
ከብዙ አገራት አንጻር የኮሪያ ሴቶች በጣም የተማሩ ናቸው። ነገር ግን የአገሪቱ ክፍያ ከጾታ አንጻር ከፍተኛ ልዩነት ያለው ነው። ከሥራ ውጪ የሆኑ ሴቶች ቁጥርም ከወንዶች አንጻር ከፍ ያለ ነው።
ተመራማሪዎች ሥራቸውን ወይም ቤተሰባቸው እንዲመርጡ ያደርጋቸዋል ይላሉ። ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥራቸውን በመምረጥ ላይ ናቸው።
ስቴላ ሺን ከትምህርት በኋላ የአምስት ዓመት ልጆችን እንግሊዝኛ ታስተምራለች።
“ልጆቹን ተመልከት በጣም ቆንጆዎች ናቸው” ትላለች። የ39 ዓመቷ ስቴላ ልጆች የሏትም። በንቃት የተደረገ ውሳኔ አልነበረም ትላለች።
በትዳር ዓለም ውስጥ ለስድስት ዓመታት አሳልፋለች። እሷም ሆነች ባለቤቷ ልጅ ቢፈልጉም በሥራ እና በመዝናናት የተጠመዱ ስለነበሩ ጊዜያቸውን አሳልፈዋል። አሁን አኗኗሯ ልጅ መውለድን “የማይቻል” እንዳደረገው ተቀብላለች።
“እናቶች ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ልጃቸውን ሙሉ ጊዜ ሰጥተው ለመንከባከብ ሥራ ማቆም አለባቸው። ይህ ደግሞ በጣም ያስጨንቀኝ ነበር። ሥራዬን እና እራሴን መንከባከብ እወዳለሁ” ስትል ተናግራለች።
ስቴላ በትርፍ ጊዜዋ የኬ-ፖፕ የዳንስ ትምህርት በዕድሜ ከገፉ ሴቶች ጋር ትማራለች።

ሴቶች ልጅ ሲወልዱ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ከሥራ እረፍት ይወስዳሉ የሚለው ተስፋ በሴቶች ዘንድ የተለመደ ነው። ስቴላ የወላጅነት ፈቃዱን ከባለቤቷ ጋር መካፈል ትችል እንደሆነ ስትጠየቅ “ዕቃ እንዲያጥብ ስነግረው ሁሌም ትንሽ አንከን አላጠበትም። በእሱ መተማመን አልቻልኩም” ብላለች።
ሥራ ለመተው ወይም ቤተሰብን እና ሥራን በጋራ ለማስኬድ ብትፈልግ እንኳን የመኖሪያ ቤት ዋጋ በጣም ውድ ስለሆነ አቅሟ እንደማይችል ትገልጻለች።
ከግማሽ በላይ የሚሆነው የደቡብ ኮሪያ ሕዝብ በዋና ከተማው ሴዑል ወይም በአካባቢው ይኖራሉ። ይህም በመኖሪያ ሕንጻዎች እና ሀብት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል። ስቴላ እና ባለቤቷ ቀስ በቀስ ከዋና ከተማው ርቀው ወደ አጎራባች ግዛቶች ተገፍተዋል። አሁንም የራሳቸውን መኖሪያ ቤት መግዛት አልቻሉም።
በዋና ከተማዋ ሴዑል ያለው የመውለድ ምጣኔ ወደ 0.59 አሽቆልቁሏል። ይህም በአገሪቱ ዝቅተኛው ነው።
መኖሪያ ቤት ጎን ለጎን የግል ትምህርት ዋጋም ይነሳል።
ከአራት ዓመታቸው ጀምሮ ልጆች ወደ ውድ ትምህርት ቤቶች ይላካሉ። ትምህርት ቤቶቹ ከሒሳብ እና ከእንግሊዝኛ እስከ ሙዚቃ እና ቴኳንዶ ያስተምራሉ።
ይህን አለማድረግ ልጆችን እንዲወድቁ እንደማዘጋጀት ይቆጠራል። ይህም ከፍተኛ ውድድር ባለባት ኮሪያ ውስጥ የማይታሰብ ነው። ስለሆነም ልጅን በማሳደግ በዓለም ላይ በጣም ውድ አገር አድርጓታል።
እአአ በ2022 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው 2 በመቶ ወላጆች ብቻ ልጆቻቸውን ወደ ግል ትምህርት የማይልኩ ሲሆን፣ 94 በመቶ የሚሆኑት የገንዘብ ሸክም ነው ብለዋል።
መምህር ሆነችው ስቴላ ሸክሙን በደንብ ተረድታዋለች። ወላጆች በወር ለአንድ ልጅ እስከ 890 ዶላር ሲያወጡ ትመለከታለች። አብዛኞቹ ደግሞ አቅሙ የላቸውም።
“ያለ ትምህርት ልጆቹ ወደ ኋላ ይቀራሉ። ከልጆች ጋር ስሆን አንድ ልጅ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። ግን ደግሞ በጣም ብዙ አውቃለሁ” ብላለች።

ስሟ እንዳይጠቀስ የምትፈልገው “ሚንጂ” ልጅ መውለድ እንደማትፈለግ ወላጆቿ እንዲያውቁ አትፈልግም። “በጣም ይደነግጣሉ፣ ያዝናሉ” ታላለች።
ሚንጂ በልጅነቷ እና በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እያለች ደስተኛ እንዳልነበረች ትናገራለች።
“ሕይወቴን ሙሉ በትምህርት አሳልፌያለሁ” ትላለች። ከረዥሙ ጉዞ በኋላ በ28 ዓመቷ የመጀመሪያ ሥራዋን አሳካች።
“ህልሜን ለማሳካት ብቻ ሳይሆን መካከለኛ ሕይወት ለመኖር ብዙ ለፍቻለሁ። በጣም አሰልቺ ነበር” ስትል ተናግራለች።
አሁን በ32 ዓመቷ ሚንጂ ነፃነት ይሰማታል። መዝናናት ትችላለች። መጓዝም ትወዳለች።
ልጅ ወልዳ በተመሳሳይ መከራ ውስጥ እንዲያልፍ አትፈልግም።
“ኮሪያ ህጻናት በደስታ የሚኖሩባት ቦታ አይደለችም” ትላለች። ባሏ ልጅ ይፈልጋል። በዚህ ምክንያት በተደጋጋሚ ይጣሉ ነበር። በኋላ ግን ምኞቷን ተቀበለ። አልፎ አልፎ ልቧ ቢፈልግም ለምን ሊሆን እንደማይችል ታስታውሳለች።
ተስፋ አስቆራጭ ማኅበራዊ ክስተት
ጁንግዮን ቹን እሷ “ለብቻ በምትለው ሁኔታ” ልጅ እያሳደገች ትገኛለች። የሰባት ዓመት ሴት ልጇን እና የአራት ዓመት ወንድ ልጇን ከትምህርት ቤት አውጥታ ባሏ ከሥራ እስኪመለስ ለሰዓታት በአቅራቢያው ባለው የመጫወቻ ሜዳ ታሳልፋለች። ባለቤቷ ከመኝታ ሰዓት በፊት ቤት የሚደርሰው አልፎ አልፎ ነው።
“ልጆች ለመውለድ ትልቅ ውሳኔ እንደወሰንኩ አልተሰማኝም ነበር። ወደ ሥራ በፍጥነት መመለስ እንደምችል አስቤ ነበር” ትላለች።
ማኅበራዊ እና የገንዘብ ግፊቶች መጡ። ባለቤቷ በልጆቹ እንክብካቤ ወይም በቤት ውስጥ ሥራ አልረዳትም።
“በጣም ተናድጃለሁ። እኔ በደንብ የተማርኩ ነኝ። ሴቶች እኩል መሆናቸውን ስለማምን ይህንን መቀበል አልቻልኩም።”
ይህ የችግሩ ዋና ጉዳይ ነው።
ላለፉት 50 ዓመታት የኮሪያ ኢኮኖሚ በፍጥነት ሲያድግ ነበር። ሴቶችን ወደ ከፍተኛ ትምህርትና እና ወደ ሠራተኛነት በማሸጋገር ምኞታቸውን እያሰፋ ቢሄድም የሚስትነት እና የእናትነት ሚና በተመሳሳይ ፍጥነት አልዳበረም።
ጁንጊዮን ሌሎች እናቶችን መመልከት ጀመረች። “ልጅ የምታሳድገው ጓደኛዬም በጭንቀት ተውጣለች። ጓደኛዬም ጭንቀት ውስጥ ገብታለች። ኧረ ይሄ ማኅበራዊ ክስተት ነው” ማለት ጀመርኩ።
ልምዶቿን በበይነ መረብ ማጋራት ጀመረች። “ታሪኮቹ ከውስጤ ይወጡ ነበር” አለችኝ። ይህም ትልቅ ስኬት አስገኘላት። ጁንግዮን አሁን ሦስት የታተሙ የቀልድ መጽሐፍት ደራሲ ነች።
አሁን የንዴት እና የጸጸት ደረጃውን ማለፏን ትገልጻለች። “ስለ ልጆች አስተዳደግ እና እናቶች ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የበለጠ ባውቅ እመኛለሁ። አሁን ሴቶች ልጅ የማይወልዱበት ምክንያት ስለ ጉዳዩ ለመናገር ድፍረት ስላላቸው ነው።”
“በሚገደዱበት አሳዛኝ ሁኔታ” ምክንያት ሴቶች የእናትነት ድንቅ ስጦታ እየተነፈጋቸው በመሆኑ ማዘኗን ትገልጻለች።
ሚንጂ ኤጀንሲ ስላላት እንደምታመሰግን ትናግራለች። “እኛ መምረጥ ተፈቀደልን የመጀመሪያዎቹ ትውልዶች ነን። በፊት ልጆች መውለድ ይጠበቅብን ነበር። እኛ ግን መምረጥ ችለናል።”

“ብችል 10 ልጆች ይኖሩኝ ነበር”
ወደ ዬጂን መኖሪያ ቤት እንመለስ። ከምሳ በኋላ ጓደኞቿ ስለመጽሐፎቿ እና ሌሎች ዕቃዎቿ እያወሩ ነው።
በኮሪያ ያለው ሕይወት አደክሟት ዬጂን ወደ ኒውዚላንድ ለመሄድ ወስናለች። አንድ ቀን ጠዋት ከእንቅልፏ ስትነቃ ማንም ሰው ኮሪያ እንድትኖር የሚያስገድዳት እንደሌለ ለራሷ ነገረች።
የትኞቹ አገራት በፆታ እኩልነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አጥንታ ኒውዚላንድ ቀዳሚ ሆነች። “ወንዶች እና ሴቶች እኩል የሚከፈላቸው አገር ናት።”
ዬጂንን እና ጓደኞቿን ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ምን ሊያሳምናቸው እንደሚችል ጥያቄ ቀረበላቸው።
ሚንሱንግ “ልጆች መውለድ እወዳለሁ። ከቻልኩ 10 ይኖረኝ ነበር።”
ታዲያ ምን አገዳት? የ27 ዓመቷ ሚንሱንግ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ በመሆኗ ጓደኛዋ ሴት ናት።
በደቡብ ኮሪያ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ሕገወጥ ነው። ያላገቡ ሴቶች ለመጸነስ የወንድ ዘር ለጋሾችን እንዲጠቀሙም አይፈቀድላቸውም።
“አንድ ቀን ይህ እንደሚለወጥ ተስፋ እናደርጋለን። እናም ከምወደው ሰው ጋር ተጋብቼ ልጅ መውለድ እችላለሁ” ትላለች።
ኮሪያ ካለችበት አሳሳቢ የሥነ-ሕዝብ ሁኔታ አንፃር እናት መሆን የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች እንዳይሆኑ መከልከላቸው አስቂኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፖለቲከኞች ቀስ በቀስ የቀውሱን ጥልቀት እና ውስብስብነት የሚቀበሉ ይመስላል።
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ከችግሩ ለመላቀቅ ያደረጉት ሙከራ “ያልተሳካ” እና ደቡብ ኮሪያ “ከልክ በላይ እና አላስፈላጊ ፉክክር” እንዳደረገች አምነዋል።
መንግሥታቸው ዝቅተኛውን የወሊድ ምጣኔ እንደ “መዋቅራዊ ችግር” እንደሚቆጥረው ተናግረዋል። ወደ ፖሊሲ እንዴት እንደሚተረጎም ግን ወደፊት የሚታይ ይሆናል።
ዬጂን ኒውዚላንድ ከከተመች ሦስት ወራት አለፉ።
ከአዲሱ ሕይወቷ እና ጓደኞቿ ጋር እየተላመደች ነው። በመጠጥ ቤት ውስጥ በአብሳይነት ትሠራለች። “የሥራ እና የሕይወት ሚዛኔ በጣም የተሻለ ነው” ብላለች። በሥራ ቀናት ጭምር ከጓደኞቿ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ መያዝ ትችላለች።
“በሥራ ላይ በጣም የተከበርኩ እንደሆነ ይሰማኛ” ስትልም አክላለች።
“ይህም ወደ አገሬ እንዳልሄድ እያደረገኝ ነው።”












