ሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከሞቃዲሾ በ72 ሰዓት እንዲወጡ አዘዘች፣ አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ ጠራች

የፎቶው ባለመብት, Villa Somalia
ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ በመወሰን በአገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደር እና ዲፕሎማቶች ለቀው እንዲወጡ ስታዝ አዲስ አበባ ያሉትን አምባሳደሯን ጠርታለች።
የሶማሊያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስቴር ይፋ እዳደረገው በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ሞሐመድ ዋሬ በ72 ሰዓታት ውስጥ ሞቃዲሾን ለቀው እንዲወጡ አዛለች።
በተጨማሪም ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ባወጀችው ሶማሊላንድ እና በከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ ውስጥ የሚገኙት ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች በሰባት ቀናት ውስጥ እንዲዘጉ መወሰኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በተመሳሳይም ሶማሊያ በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን “ለአጠቃላይ ምክክር” ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸው ተገልጿል።
የሶማሊያ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ውሳኔውን የዘገበው ሮይተርስ የዜና ወኪል የሶማሊያን ውሳኔ በተመለከተ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላን ጠይቆ የነበረ ቢሆንም መረጃ እንደሌላቸው ገልጸው ነበር።
የሶማሊያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ውሳኔውን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ “በቅርቡ የተከሰቱ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን መሠረት አድርጎ” በርካታ ዲፕሎማሲያው እርምጃዎችን መውሰዱን ገልጿል።
ጨምሮም ውሳኔው ኢትዮጵያ “በሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የውስጥ ጉዳይ” ጣልቃ በመግባት ለወሰደቻቸው እርምጃዎች ምላሽ መሆኑን ቢገልጽም፣ የትኞቹ የኢትዮጵያ እርምጃዎች ለዚህ እንዳበቁ ያለው ነገር የለም።
በዚህም መሠረት በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን በሚል የኢትዮጵያ አምሳደር ከሐሙስ መጋቢት 26/2016 ዓ.ም. ጀምሮ በሦስት ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ፣ በሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሐርጌሳ እንዲሁም በፑንትላንድ ዋና ከተማ ጋሮዌ የሚገኙት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲዘጉ ወስኗል።
በአዲስ አበባ የሚገኙት የሶማሊያ አምባሳደርም ወደ ሞቃዲሾ እንደሚመለሱ መታዘዛቸውን ያመለከተው መግለጫው፣ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ መሆኑን አመልክቷል።
ባለፈው ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት የፈረመች ሲሆን፣ ይህም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት አበላሽቶት መቆየቱ ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እውቅና በመንፈግ የውጭ ግንኙነቷን በራሷ እንደምታካሂድ ያሳወቀቸው ፑትላንድ በሶማሊያ ፖለቲካ ውስጥ ውጥረትን ፈጥራለች።
ይህንንም ተከትሎ የፑንትላንድ የገንዘብ ሚኒስትር ትናንት ረቡዕ መጋቢት 25/2016 ዓ.ም. ለጉብኝት አዲስ አበባ ገብተው ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ጋር ተወያይተዋል።
ምናልባትም የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አሁን የኢትዮጵያን ዲፕሎማት ለማባረር እና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶቿ እንዲዘጉ ከውሳኔ ላይ የደረሰው የገንዘብ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎ ሊሆን ይችላል።
አሁን የሶማሊያ መንግሥት በሶማሊላንድ እና በፑንትላንድ ውስጥ የሚገኙት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት እንዲዘጋ መወሰኑ ከሁለቱ ግዛቶች ጋር ያለውን ያለመግባባት አመልካች ሲሆን፣ ነገር ግን ከማዕከላዊው የሶማሊያ መንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሚገኙትን የቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን የመዝጋት ውሳኔ ተግባራዊነት አጠያያቂ ነው።
ከሦስት ወራት በፊት ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የደረሱት ስምምነት ከሶማሊያ ጋር ያለውን ግንኙነት ያደፈረሰው ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ በሁለቱ አገራት መካከል መግባባት ሳይፈጠር ቆይቷል።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ኢትዮጵያ በዚህ ስፍራ የባሕር ኃይል ሰፈር እንደምታቋቁም እና በምትኩ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች መባሉን ተከትሎም እንደ ግዛቷ አካል የምታያት ሶማሊያ ጉዳዩን ወደ አህጉራዊ እና ዓላም አቀፋዊ ድርጅቶች እስከ መውሰድ አድርሷታል።
ሁለቱ አገራት የገቡበት ውጥረትም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ መሐመድ የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ጉባኤ ላይ እንዳልሳተፍ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ተከልክያለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ነገሮች ተካረዋል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ክሱን ውድቅ ያደረገች ሲሆን፣ የሶማሊያ ልዑካን በመንግሥት የተመደቡላቸውን የፀጥታ ሠራተኞችን አንቀበልም በማለት ጠባቂዎቻቸው የጦር መሳሪያ ታጥቀው ጉባኤው ወደሚካሄድበት ስፍራ ለመግባት ሲሞክሩ በኅብረቱ የፀጥታ አካላት ተከልክለዋል ብላለች።
ከሶማሊያ በኩል ተደጋጋሚ ክሶች እና መግለጫዎች ከመቅረባቸው በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።
ኢትዮጵያም ጉዳዩ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ የታየ በመሆኑ ምክር ቤቱ ሊመክርበት አይገባም በሚል ተቃውማ ነበር።
የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሁለት ጊዜ ባደረገው ስብሰባ በሁለቱ አገራት ውጥረት ዙሪያ ተወያይቶበታል።
ምክር ቤቱ ሶማሊያን አጀንዳ ባደረገበት የካቲት 11 ስብሰባው በተጨማሪ ጥር 20/ 2016 ዓ.ም. “ሰላም እና ፀጥታ በአፍሪካ” በሚል ርዕስ የሁለቱን አገራት ውዝግብ በዝግ ሰብሰባ መክሮበታል።
በዚህም ስብሰባ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሶማሊያ ተወካይ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነትን ጦርነት ከማወጅ ጋር የሚስተካከል ነው በማለት አነጻጽረውታል።
አምባሳደር አቡካር ኡስማን ባሕር በር የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ሰፈር ለማቋቋም ስትል የሶማሊያን ግዛት የመጠቅለል ዕቅድ አላት ሲሉ ክሳቸውን ለፀጥታው ምክር ቤት አቅርበዋል።
የተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕከተኛ በበኩሉ የአምባሳደሩን ንግግር በሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት በኩል እየቀረበ ያለው ምክንያታዊነት የሌለው የማያባራ ውንጀላ አካል ነው ሲልም ወቅሷል።
ኢትዮጵያ ሌሎች አገራት እውቅና ካልሰጧት ሶማሊላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ስምምነት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ወይም ከዓለም አቀፍ አሰራር ጋር የሚቃረን እንዳልሆነም በመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አስረድቷል።
ሌሎች አገራት በሊዝ የባሕር በር መዳረሻን ለማግኘት ከተፈራረሙት ጋር ተመሳሳይ ነው ሲልም አውስቷል።
በዚህም ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ አባላት የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑትን ኦሉሴጎን ኦቦሳንጆን ልዑክ በማድረግ ሁለቱን አገራት ለማሸማገል የጀመረውን ጥረት ይደግፋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል የተባሉት አምባሳደር ሙክታር መሐመድ ሶማሊያን በሚመለከት ለአንድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለምልልስ ላይ የሰነዘሩት ሃሳብ የተሳሳተ መሆኑን በመግለጽ በቅርቡ ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል።
አምባሳደሩ በቃለ ምልልሳቸው ሶማሊያ “የቅኝ ግዛት ውጤት” እንደሆነች እና በአገሪቱ ውስጥ ስላላው የፀጥታ ሁኔታ የገለጹበትን መንገድ በማስተባበል ነው አገሪቱን ሕዝብ እና መንግሥት ይቅርታ የጠየቁት።
አምባሳደሩ በሶማሊያውያን ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰውን ይህንን ቃለምልልሳቸውን በተመለከተ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የተጠቀሟቸው “ቃላት የተሳሳቱ” እንደነበሩ ገልጸዋል።












