ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነታቸው የሻከረው ኤርትራ፣ ግብፅ እና ሶማሊያ ለመተባበር ተስማሙ

የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ፣ የግብፁ ፕሬዝደንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ እና የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ

የፎቶው ባለመብት, Eritrean Information Ministry

ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት የሻከረው ግብፅ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ላይ ደረሱ።

የሦስቱ አገራት መሪዎች በኤርትራ ዋና ከተማ አሥመራ ሐሙስ መስከረም 30/2017 ዓ.ም. ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ነው የሦስትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክር ስምምነት ላይ የደረሱት።

ውይይታቸውን ተከትሎ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ “የአገራት ሉዐላዊነት መከበር አለበት. . . በቀጣናው ያሉ አገራት የግዛት አንድነትም መጠበቅ አለበት” ብሏል።

ምንም እንኳ ይህ መግለጫ የባሕር በር የሌላትን ኢትዮጵያን የሚመለከት እንደሆነ ቢታመንም መግለጫው የየትኘውንም አገር በስም አልጠቀሰም።

በቅርቡ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ቁርሾ ሞቃዲሾ ከግብፅ እና ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታጠናክር አድርጓል። ግብፅ እና ኤርትራ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት በተለያዩ ምክንያቶች የሻከረ ነው።

ኢትዮጵያ ነጻነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የመግብቢያ ሰነድ በመፈረሟ ከሶማሊያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ስትሆን፣ ከግብፅ ጋር ደግሞ ግንባታው ሊጠናቀቅ በተቃረበው የሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከአስር ዓመታት በላይ አለመግብባት ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ከኤርትራ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምንም ችግር እንደሌለበት ቢናገሩም በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ካበቃ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መቀዛቀዙ ሲነገር ቆይቷል።

አሁን በኤርትራ ጋባዥነት ሦስቱ አገራት የጋራ ትብብር ለማድረግ መስማማታቸው የቀጣናውን አለምግባባት አለመግባባት ወደ ግጭት እንዳያመራ ስጋት ፈጥሯል።

“ይህ ጥምረት አዲስ አበባን ለመቃወም ያለመ ነው” ሲሉ የሆርን ስትራቴጂክ ስተዲስ ዓለም አቀፍ ተቋም ኃላፊ ሐሰን ኻኔንጄ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ተናግረዋል።

“እኔ እንደሚመስለኝ ሦስቱ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር አዲስ አበባ ላይ ጫና ለማሳደር እያደረጉ ያለው ጥረት ነው” ብለዋል።

ነገር ግን የሶማሊያው ማስታወቂያ ሚኒስትር ዳውድ አወይስ የውይይቱ ዓላማ በሦስቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ነው ሲሉ ያስተባብላሉ።

“እኛ ከአዲስ አበባ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማበላሸት አስበን የምናደርገው ነገር የለም” ሲሉ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ ጎረቤታችን ናት። ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ትብብር አለን። ቢሆንም ከአስተዳደሩ በኩል በቀጣናው አለመረጋጋት የሚያስከትል ጉዳይ መጥቷል። ሆኖም እኛ በሰላም እናምናለን፤ በአሥመራ ያደረግነው ስብሰባ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘው ነገር አለ ብለን አናምንም።”

ከስብሰባው በኋላ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ያወጣው ፎቶ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ከግብፁ ፕሬዝደንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ፣ ከሶማሊያ አቻቸው ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው አሳይቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኤርትራ መግለጫ እንደሚለው ሦስቱ መሪዎች “ከውስጥ እና ከውጭ የሚመጡ ተግዳሮቶችን መቋቋም ለማስቻል፣ የሶማሊያን ተቋማት ለማጠናከር እና የሶማሊያ ብሔራዊ ፌዴራል ሠራዊት ሽብርተኝነትን መዋጋት እንዲችል ለማድረግ” ተስማምተዋል።

አል-ሲሲ ወደ አሥመራ ተጉዘው ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የሶማሊያ ፕሬዝደንት በበኩላቸው በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ አራት ጊዜ ወደ አሥመራ አቅንተዋል።

ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የሞቃዲሾ አስተዳደር ከአል-ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለውን አል-ሸባብ ለመዋጋት የሚያደርገውን ጥረት ስትደግፍ ቆይታለች።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ተከትሎ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ሻክሯል። ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላት ነው። ሶማሊያ ራስ ገዟ ሶማሊላንድን እንደ ግዛቷ አካል ነው የምትቆጥራት።

በሌላ በኩላ በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ አማካይነት ለዓመታት ሻክሮ ቆይቷል። ግብፅ አባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ ወደታች የሚፈሰውን ውሀ መጠን ይቀንሰዋል ስትል ትሞግታለች።

ባለፈው ወር አንድ የግብፅ መርከብ በርካታ የጦር መሣሪያዎች ጭኖ ወደ ሶማሊያ ማምራቱ ተዘግቧል። ይህ የሆነው ሁለት የግብፅ ወታደራዊ አውሮፕላኖች የጦር መሣሪያዎች ጭነው ወደ ሞጋዲሹ ካቀኑ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2018 ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ለሁለት አስርት ዓመታት የነበራቸውን አለመግባባት ሽረው ስምምነት ላይ መድረሳቸው አይዘነጋም።

በወቅቱ ወደ ሥልጣን የመጡት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኤርትራ ጋር “የሰላም እና ወዳጅነት ስምምነት” ፈርመው ነው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ተሻሽሎ የነበረው።

ይህን ስምምነት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።

ነገር ግን ጎረቤታሞቹ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ያላቸው ግንኙነት ድጋሚ መቀዛቀዝ የጀመረው ሁለት ዓመት የፈጀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በስምምነት ከተቋጨ በኋላ ነው።

በዚህ ግጭት ወቅት ኤርትራ የኢትዮጵያ መንግሥት አጋር ነበረች። ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ስምምነት ፈርሞ ጦርነቱ ከቆመ በኋላ በአጅመራ እና አዲስ አበባ መካከል ያለው ግንኙነት ድጋሚ ሻክሯል።

የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ያሻከረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፈው ዓመት ቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር ሊኖረን ይገባል ማለታቸውን ተከትሎ ነው።