ያልተገነባ ቤት የሚሸጡ ሪል ስቴት አልሚዎች የሚሰበስቡትን ገንዘብ በዝግ አካውንት እንዲያስቀምጡ ሊገደዱ ነው

ሪል ስቴት ቤቶች መንደር

የፎቶው ባለመብት, Sunrise Real Estate

ግንባታ ከማከናወናቸው አስቀድመው ቤት የሚሸጡ ሪል ስቴት አልሚዎች፤ ከደንበኞቻቸው የሚሰበስቡትን ገንዘብ በዝግ የባንክ አካውንት እንዲያስቀምጡ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፤ ቤት ለመገንባት የመሬት የይዞታ ማረጋገጫ እና የግንባታ ፈቃድ ያላገኙ የሪል ስቴት አልሚዎች ደንበኞችን እንዳይመዘግቡ እና ቅድመ ክፍያ እንዳይሰበስቡም ይከለክላል።

“የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ” የተሰኘው ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ዛሬ ሐሙስ መስከረም 30/2017 ዓ.ም. በተደረገው የፓርላማው አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው።

በዛሬው ስብሰባ ላይ ከቀረቡት ስድስት ረቂቅ ሕጎች መካከል የሆነው ይህ አዋጅ፤ ከዚህ ቀደም ራሱን የቻለ ሕግ ላልነበረው የሪል ስቴት ቤቶች የግንባታ እና ግብይት ሂደት አዲስ እና አሳሪ አሠራሮችን ያስተዋወቀ ነው። እንደ ሕንጻ ያሉ የማይንቀሳቀስ ንብረቶች ያላቸው ዋጋ በመንግሥት እንዲሁም በግል ባለሙያዎች የሚገመትበት እንዲሁም ግመታው አገልግሎት ላይ የሚውልበት አሠራርም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተቀምጧል።

ከረቂቅ አዋጁ ጋር አብሮ ለምክር ቤቱ የቀረበው ማብራሪያ የሪል ስቴት ልማት፣ ግብይት እና የዋጋ ትመና “በቂ የሕግ ሥርዓት የሌለው በሕገወጥ ደላሎዎች ተጽዕኖ ስር የወደቀ” እንደሆነ ያስረዳል። የሪል ስቴት ልማት ካለው የቤት ፍላጎት “በእጅጉ የራቀ” እንዲሁም “በሕገወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱ ደላላ ተብለው በሚታወቁት አካላት” ተፅዕኖ ስር የወደቀ እንደሆነ በማብራሪያው ላይ ሰፍሯል።

አዋጁን ማዘጋጀት አስፈላጊ ከሆነባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፤ “ቤት ለመግዛት እና ለመከራየት የሚፈልጉ ወገኖች በከፍተኛ ሁኔታ የሚቸገሩበት ሁኔታ መቀየር ስላለበት የሪል ስቴት ኢንቨስትመንትን ማበረታታት እና የቤት አቅርቦት እንዲሻሻል መደገፍ ማስፈለጉ” እንደሆነም ተጠቅሷል።

በአሁኑ ጊዜ ባለው አሠራር መሠረት የንግድ ፈቃድ በማውጣት ብቻ ወደ ሪል ስቴት ገበያው ሲቀላቀሉ የነበሩት አልሚዎች፤ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ “የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ” የማውጣት ግዴታ ተጥሎባቸዋል። የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብት ሪል ስቴት አልሚዎች ይህንን ፈቃድ ለማግኘት ቢያንስ 50 ቤቶችን ገንብተው የሚያስከረክቡ መሆን እንዳለባቸው በረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

የአገር ውስጥ እና የውጭ አልሚዎች ግንባታውን ለማከናወን የሚያስፈልገውን “የፋይናንስ አቅርቦት ምንጭ” የማቅረብ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦባቸዋል። ይሁንና ረቂቁ፤ “የቅድሚያ ቤት ሽያጭ ተጠቃሚነት” መብትን ከቅድመ ሁኔታ ጋር ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሰጥቷል።

ይህ አሠራር የሪል ስቴት አልሚዎች የቤት ግንባታውን ሳያከናውኑ ወይም በሂደት ላይ እያለ ለግንባታው የሚውልን ፋይናንስ የሚያሰባስቡበት እና ገንዘቡን ለግንባታው የሚያውሉበት መንገድ ነው። የቤት ግንባታው ሳይከናወን በፊት ከገዢዎች ጋር ውል ማሰር እና ክፍያ መፈጸም ኢትዮጵያ ውስጥ በሪል ስቴት ልማት ላይ በተሰማሩ አልሚዎች በኩል የተለመደ አሰራር ነው።

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፤ በዚህ ዓይነት መልኩ ለግንባታ የሚውለውን ሀብት ማሰባሰብ የሚፈልጉ አልሚዎች “አግባብ ካለዉ አካል ፈቃድ ማቅረብ” እንደሚጠበቅባቸው ያስረዳል። ረቂቁ፤ “የሪል ስቴት አልሚው በቤት ቅድሚያ ሽያጭ ስልት ለመሥራት መፈለጉን አግባብ ላለው አካል አሳውቆ ፈቃድ ማግኘት [አለበት]” ሲል አዲሱን ግዴታ አስቀምጧል።

የቅድመ ሽያጭ ዘዴን መጠቀም የሚፈልጉት ሪል ስቴት አልሚዎች፤ ከቤት ገዢዎች የሚሰበስቡት ገንዘብ የሚቀመጥበት የባንክ ሂሳብ እና የገንዘብ አወጣጥ ላይም አስገዳጅ አሠራር በረቂቅ አዋጁ ተጥሎባቸዋል። አልሚዎቹ ከቤት ገዢዎች የሚሰበስቡትን ገንዘብ “የዝግ የባንክ ሂሳብ ገቢ ማደረግ ወይም ማስያዝ” እንዳለባቸው ረቂቅ ሕጉ ላይ ሰፍሯል።

የቤት ሽያጭ ፕሮግራም ማስታወቂያ ባነር

የፎቶው ባለመብት, ovid real estate

የምስሉ መግለጫ, ጥቂት የማይባሉ ሪል ስቴት አልሚዎች ለሚገንቧቸው ቤቶችን የሚውለውን ፋይናንስ የሚያሰባስቡት ቤቶችን አስቀድመው በመሸጥ ነው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ገንዘቡ የሚቀመጥበት ዝግ የባንክ አካውንት የሚከፈተው “አግባብ ባለው አካል ፈቃድ መሠረት” እንደሆነም አዲሱ ሕግ ያስረዳል። በዝግ የባንክ ሂሳብ ገቢ የተደረገው ገንዘብ የሚለቀቅበት ሁኔታ ከረቂቅ አዋጁ መፅደቅ በኋላ በሚወጣ ደንብ እንደሚወሰንም ተጠቅሷል።

ከዚህም ባሻገር በቅድሚያ የተሸጠው ቤት ተገንብቶ ለተጠቃሚዎች እስከሚተላለፍ ድረስ የቤት መሥሪያ ቦታው የይዞታ ማስረጃ “በሚመለከተው አካል እንዳይሸጥ፣ እንዳይለወጥ” እንደሚታገድ ረቂቁ ይገልጻል። ቤት ቀድመው በሚሸጡ ሪል ስቴት አልሚዎች ላይ እነዚህ አስገዳጅ አሠራሮች የተቀመጡት “ደንበኞች የሚደርስባቸውን እንግልት እና ኪሳራ ለመቀነስ በማሰብ” እንደሆነ የአዋጁ ማብራሪያ ያስረዳል።

ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ይህ ረቂቅ አዋጅ፤ በሪል ስቴት አልሚዎች ላይ ሌሎች ግዴታዎችንም ጥሏል። በረቂቁ መሠረት፤ የሪል ስቴት አልሚዎች ግንባታው 80 በመቶ ላይ ያልደረሰን ቤት ለደንበኞች እንዳያስተላልፉ ተከልክለዋል።

ረቂቁ፤ “ያለደንበኛው ፍላጎት እና ፈቃድ አጠቃላይ ግንባታው ቢያንስ 80 በመቶ ያልተጠናቀቀ ቤት ለደንበኞች ሊያስተላልፍ አይችልም” ሲል ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀ ቤት ለማስረከብ በቅድሚያ ደንበኛው መስማማት እንዳለበት ያመለክታል። ሪል ስቴት አልሚዎች ቤት ገዢዎችን መመዝገብ እና ቅድመ ክፍያ መሰብሰብ የሚችሉበት ጊዜም ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦበታል።

አልሚዎች ምዝገባ ማድረግ እና ክፍያ መሰብሰብ የሚችሉት “የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ እና የግንባታ ፈቃድ ከሚመለከተው አካል ከተረከቡ” በኋላ እንደሆነ ረቂቁ ላይ ተካትቷል። “በሕጋዊ መንገድ የተረከበው መሬት ሊያስተናግድ ከሚችለዉ የቤት ደንበኛ በላይ መመዝገብ አይችልም” የሚለውም ሪል ስቴት አልሚዎች ላይ ከተቀመጡት ግዴታዎች መካከል ነው።

ለሪል ስቴት ልማት አሠራር የሚዘረጋው አዲሱ አዋጅ፤ ከግዴታዎች ባሻገር አልሚዎች ከመንግሥት “መሬት በስፋት” ማግኘት የሚችሉበትን ሂደትም ያስቀመጠ ነው። ከመንግሥት መሬት “በስፋት” የሚቀርብላቸው አልሚዎች ረቂቁ ላይ ከተጠቀሱ ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ቢያንስ አንዱን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።

ከእነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል በብዛት ቤቶችን መገንባት እና ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ “40 በመቶውን ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍል ተደራሽ” ማድረግ የሚለው አንዱ ነው። ይህንን ቅድመ ሁኔታ የሚከተሉ አልሚዎች የሚገነቡት ቤት ብዛት “እንደ ከተሞች ደረጃ በአንድ ጊዜ ከ500 እስከ አምስት ሺህ” ሊሆን እንደሚችል በረቂቁ ላይ ተጠቅሷል።

መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ መሬት “በስፋት” የሚያቀርበው “በአዲስ አበባ ከ5 ሺ በላይ ቤት ለሚገነባ እና ለሚያስተላልፍ” አልሚ እንደሆነ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። በሌሎች ከተሞች መሬት “በስፋት” የሚቀርበው እደሚኖራቸው “ተጨባጭ የቤት ፍላጎት” ሲሆን፣ “ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለበት አካባቢ ባሉ ከተሞች” ደግሞ ከአንድ ሺህ በላይ ቤቶችን ለሚገነቡ አልሚዎች እንደሚቀርብላቸው ረቂቁ ያስረዳል።

ከመንግሥት መሬት “በስፋት” ማግኘት የሚፈልጉ አልሚዎች የተቀመጠባቸው ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ከውጭ ምንዛሬ ጋር የተገናኙ ናቸው።

በአገር ውስጥ “በጥራት እና በብዛት የማይገኙ” ግብአቶችን በራሳቸው የውጭ ምንዛሬ (ፍራንኮ ቫሉታ) የሚያስገቡ እንዲሁም የሚያገኙትን ትርፍ እስከ አስር ዓመት ከአገር ሳያወጡ አገር ውስጥ መልሰው የሚጠቀሙ አልሚዎች የዚህ አሠራር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

“የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይት እና ግመታ” የተሰኘው ይህ ረቂቅ አዋጅ የቀረበለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተጨማሪ ዕይታ ወደ ከተማ፣ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ መርቶታል።