“የቦምብ ጥቃቱ ሲበረታ አሠሪዎቼ ቤት ቆልፈውብኝ ነፍሳቸውን ለማዳን ሸሹ” የሊባኖሷ የቤት ሠራተኛ

እጇን ያጣጠፈች ሴት

እስራኤል ከጋዛ አልፋ በደቡባዊ ሊባኖስ የምታደርገው የተቀናጀ የአየር እና የምድር ጥቃት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚህ ደግሞ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በሊባኖስ ውስጥ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው ያሉ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ እና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የመጡ ስደተኞች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

በደቡባዊ ሊባኖስ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ የምትሠራው አንዳኩ (ትክክለኛ ስሟ አይደለም) የቀጣሪዎቿ የመኖሪያ ቤት የአየር ጥቃት ሲደርስበት በቤት ውስጥ ብቻዋን ነበረች።

አሠሪዎቿ ነፍሳቸውን ለማዳን ሲሸሹ በቤት ውስጥ ብቻዋን ቆልፈውባት ስለነበር በፍርሃት ተርበደበደች።

የ24 ዓመቷ ኬንያዊት በሊባኖስ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ መሥራት ከጀመረች ስምንት ወራትን አስቆጥራለች።

ሆኖም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የምታደርገውን የቦምብ ጥቃት ማጠናከሯን ተከትሎ ሕይወት ፈተና ሆናባታለች።

“በርካታ የቦምብ ጥቃቶች ነበሩ። ለመቁጠር ይከብዳል። አሠሪዎቼ ቤት ውስጥ ብቻዬን ቆልፈውብኝ ነፍሳቸውን ለማትረፍ ትተውኝ ሸሹ” ትላለች።

የቦምብ ፍንዳታው ድምጽ አዕምሯዋን አናወጠው። ቀን እና ሌቱ ተደነጋገራት። አሠሪዎቿ ወደ ቤታቸው ከመመለሳቸው በፊት ለምን ያህል ቀናት እንደቆየች አታውቀውም።

ይባስ ብሎ አሠሪዎቿ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ከቤታቸው አስወጥተው አባረሯት።

“ሲመለሱ ከቤት አስወጡኝ። የሠራሁበትን ደመወዝ አልከፈሉኝም። የምገባበት ጠፋብኝ” ትላለች አንዳኩ።

እንደ ዕድል ሆኖ በእጇ ላይ ገንዘብ ስለነበራት ወደ መዲናዋ ቤይሩት በአውቶብስ ተሳፍራ ሄደች።

አንዳኩ ብቻ ሳትሆን በሊባኖስ የሚገኙ 900 መጠለያዎች መሄጃ ባጡ ሠራተኞች መሞላታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አመልክቷል።

በሊባኖስ የእስራኤል ጥቃት መባባሱን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በአብዛኞቹ ሴት የቤት ሠራተኞች በአሠሪዎቻቸው ከቤት እንዲወጡ መደረጋቸው ስጋት እንዳሳደረበት ተቋሙ ገልጿል።

በሊባኖስ ወደ 170 ሺህ የሚጠጉ ከሌሎች አገራት የመጡ ስደተኞች በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) መረጃ ያሳያል። አብዛኞቹም ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳን፣ ከሲሪላንካ እና ከባንግላዴሽ የመጡ ሴቶች ናቸው።

እስራኤል በሊባኖስ ላይ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ስደተኛ የቤት ሠራተኞች በሊባኖሳውያን አሠሪዎቻቸው ጎዳና ላይ ተጥለው ወይም ቀጣሪዎቻቸው ሲሸሹ በቤት ውስጥ ብቻቸውን ተቆልፎባቸው እንደሚገኙ የሚገልጹ ሪፖርቶች እየጨመሩ ነው” ሲሉ በሊባኖስ የሚገኘው የአይኦኤም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ማቲዩ ሉቺያኖ ከጄኔቫ ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

በርካቶች ለተሻለ ኑሮ በተለይም ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ወደ ሊባኖስ ይሰደዳሉ። አፍሪካውያን የቤት ሠራተኞች የሚቀጠሩበት አማካይ ወርሃዊ ደመወዝ ወደ 250 ዶላር ወይም 30 ሺህ ብር አካባቢ ሲሆን፣ እስያውያን ግን የዚህን እጥፍ ገደማ 450 ዶላር ወይም 450 ሺህ ብር ያገኛሉ።

ስደተኛ ሠራተኞቹ ከባርነት አይተናነስም በሚባልለት የአረብ አገራት የሠራተኞች ሕግ ወይም ካፋላ ይተዳደራሉ።

ካፋላ የዋስትና ወይም “የስፖንሰርነት ሥርዓት”' ተብሎ በግርድፉ ሊተረጎም ይችላል።

በዚህም አንድ አሠሪ ከሌላ አገር የሚቀጥረውን የቤት ሠራተኛ በተመለከተ በርካታ መብቶችን ያገኛል።

አንድ ሠራተኛ ከአሰሪዎቹ/ቿ ቤት ወይም ቁጥጥር ስር ከወጣ/ች ሕገ ወጥ ስደተኛ መሆንን ያስከትላል ይህ የካፋላ ሕግ።

በዚህ ሕግ (ሥርዓት) አማካኝነት ሠራተኞቹ መደራጀት አይችሉም። በአጠቃላይ ሕይወታቸው በቀጣሪያቸው እጅ ስር እንዲወድቅ በማድረጉ ለጥቃት እንደሚያጋልጣቸው የሚያሳዩ በርካታ ጥናቶች ተሠርተዋል።

የካፋላ ሥርዓትን አስከፊ ከሚያደርጉት መገለጫዎቹ መካከል የቤት ሠራተኞቹ አገሩን ጥለው መውጣት ቢፈልጉ እንኳን ከአሠሪያቸው የተጻፈ ፍቃድ ሊሰጣቸው ይገባል። ያ ካልሆነ በሕግ ይጠየቃሉ።

ሕጉ አሠሪዎች ሠራተኞቻቸውን ፓስፖርታቸውን እንዲቀሙ እንዲሁም ደመወዛቸውን እንዲከለክሉ የሚያስችል አደገኛ ሥርዓት ነው።

“በካፋላ ሥርዓት ውስጥ ሠራተኞች የሕግ ከለላ ስለማይሰጣቸው እንዲሁም እንቅስቃሴያቸው መገደቡን ተከትሎ እንዲበዘበዙ መንገድ ይከፍታል። በዚህም ሥርዓት ምክንያት ሠራተኞች የተለያዩ ጥቃቶች፣ መገለል እንዲሁም ለተለያዩ ሥነ ልቦና ጉዳቶች ተጋላጮች አድርጓቸዋል” ይላሉ ማቲዩ ሉቺያኖ።

አክለውም በተለይም በዚህ ወቅት የእስራኤልን ጥቃት ፈርተው እየሸሹ ያሉ አሠሪዎች ንብረታቸውን እና ቤታቸውን እንዲጠብቁ በሚል በስደተኛ የቤት ሠራተኞች ላይ “ቤት ቆልፈውባቸው እንደሚሄዱ ተረድተናል” ይላሉ።

በሊባኖስ የሚገኙ የቤት ሰራተኞች

መሄጃ አጣሁ

ኡጋንዳዊቷ ሚና (ትክክለኛ ስሟ አይደለም) በሊባኖስ ለአንድ ዓመት ከአራት ወራት በቤት ሠራተኝነት ቆይታለች።

የአሠሪዎቿን እንግልት መቋቋም አቅቷት ከቤቱ አምልጣ ወዳስቀጠራት ኤጀንሲ መሄዷን ለቢቢሲ ተናግራለች።

እርዳታ አገኛለሁ በሚል ተስፋ የሄደችበት ኤጀንሲ አገሯ ከመመለሷ በፊት በሌላ ውል ለሁለት ዓመታት ያህል ለሌላ ቤተሰብ መሥራት እንዳለባት ሲነገራት እንዳስደነገጣት ለቢቢሲ አልደበቀችም።

“የኤጀንሲው ቢሮ ሄጄ ቲኬቴን ገዝቸ ወደ አገሬ ለመመለስ በበቂ ሁኔታ ሰርቻለሁ አልኳቸው። ገንዘቤን ወሰዱ እና ለተጨማሪ ሁለት ዓመት እንድሠራ ጠየቁኝ” ስትል የ26 ዓመቷ የቤት ሠራተኛ ተናግራለች።

አማራጭ እንደሌላት የተረዳችው ሚና ለአዲሶቹ አሠሪዎቿ ተቀጥራ እየሠራች ባለቸበት ወቅት ሌላ መከራ ተጨመረባት።

እስራኤል የጀመረችው እረፍት የለሽ ጥቃት አዕምሯዋን ረበሸው። ጆሮ በሚሰነጥቅ የፍንዳታ ድምጽ መካከል ለአፍታ እረፍት የማይሰጣትን የቤት ሥራ ማከናወን ስለተሳናት አሠሪዎቿን ልወጣ ነው አለቻቸው።

“አሰሪዎቼ ደበደቡኝ እንዲሁም ገፍትረው ከቤት አስወጡኝ። በወቅቱም የአየር ጥቃቶች ነበሩ። የምሄድበት መላው ጠፋኝ” ትላለች።

ሌላኛዋ የ24 ዓመቷ ኬንያዊት ፋናካም ሥራ የሚያስቀጥራት ኤጀንሲ በየሁለት ወሩ ወደተለያዩ ቤቶች እንድትሠራ እንደሚልካት ለቢቢሲ የተናገረች ሲሆን፣ በከፍተኛ የራስ ህመም እየተሰቃየች ትገኛለች።

እስራኤል ያጠናከረችውን ጥቃት ተከትሎ በርካታ የቤት ሠራተኞች ጎዳና የወጡ ሲሆን፣ መጠለያዎቹም ለተፈናቀሉ ሊባኖሳውያን እንጂ ለውጭ ዜጎች አይደሉም በማለት አላስገባም እንዳሏቸው ይናገራሉ።

ሦስቱም የቤት ሠራተኞች ለስደተኛ ሠራተኞች እርዳታ እና ከለላ በሚሰጠው ካሪታስ ሊባኖስ በተባለ የሊባኖስ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።

ከሴራሊዮን የመጡ በርካታ ስደተኛ የቤት ሠራተኞች በቤይሩት ጎዳናዎች ላይ የፈሰሱ ሲሆን፣ የሚበሉት ምግብ እንኳን ማግኘት እንዳልቻሉ ለቢቢሲ የተላኩ የድምጽ መልዕክቶች ያስረዳሉ።

ሌሎች ደግሞ የሊባኖስ ዜግነት ስለሌላቸው በመንግሥት ወደተቋቋሙ መጠለያዎች እንዳይገቡ መከልከላቸውን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ቢቢሲ የአካባቢውን ባለሥልጣናት ስለ ጉዳዩ የጠየቀ ሲሆን፣ እነሱም ምንም ዓይነት መድልዎ እየተፈጸመ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።

የሊባኖስ የትምህርት ሚኒስቴር ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለውጭ አገር ሠራተኞች ተብለው የተለዩ የመጠለያ ማዕከላት ባይዘጋጁም ባሉት መጠለያዎች ለመግባት እንዳልተከለከሉ ነው።

አንዳንድ የቤት ሠራተኞች ያሏቸው የመኖሪያ እና የሥራ ሰነዶች ያልተሟሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ እነዚህን መንግሥታዊ መጠለያዎች በመፍራት እየራቁ መሆናቸውን ቢቢሲ ተገንዝቧል።

የካሪታስ ሊባኖስ ተቋም ኃላፊ የሆኑት ሄሰን ሳያህ ኮርባን ድርጅታቸው በአሁኑ ወቅት ወደ 70 የሚጠጉ ስደተኛ የቤት ሠራተኞችን አስጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አይኦኤም በበኩሉ ከአውሮፓውያኑ ጥቅምት ወር ጀምሮ ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ እርዳታ የሚሹ 700 ጥያቄዎች እንደቀረቡለት ገልጿል።

ካሪታስ ሊባኖስ ከሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከተለያዩ ኤምባሲዎች ጋር በመቀናጀት መሄጃ ያጡ የቤት ሠራተኞችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ይገኛል።