ኔታኒያሁ ሊባኖስ “እንደ ጋዛ ትፈራርሳለች” ሲሉ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የሊባኖስ ሕዝብ ሄዝቦላህን አውጥቶ ካልጣለ “እንደ ጋዛ ያለ መፈራረስ ሊገጥመው ይችላል” ሲሉ አስጠነቀቁ።
ማክሰኞ ዕለት የቪድዮ መግለጫ የለቀቁት ኔታኒያሁ በሺዎች የሚቆጠር እግረኛ ጦራቸውን ደቡብ ምዕራብ ሊባኖስ ልከዋል።
የእስራኤል ጦር ኃይል (አይዲኤፍ) በለቀቀው መግለጫ ሰኞ ዕለት ባደረሰው የአየር ድብደባ 50 የሚሆን የሄዝቦላህ ተዋጊዎች ተገድለዋል ብሏል።
የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር እንሚለው ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ የእስራኤል ጦር ባደረሰው ጥቃት 36 ሰዎች ሲገደሉ 150 የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል።
በተያያዘ ዜና ሄዝቦላህ ወደ እስራኤሏ የባሕር ዳርቻ ከተማ ሀይፋ ለሶስት ተከታትይ ቀናት በተኮሰው ሮኬት ምክንያት 12 ሰዎች መቁሰላቸው ተሰምቷል።
ኔታኒያሁ በቪድዮ በለቀቁት መግለጫቸው “የሊባኖስ ሕዝብ ሆይ ልክ እንደ ጋዛ ስቃይ እና መፈራርስ ከማጋጠሙ በፊት ሀገርህን ለመጠበቅ ጥሩ ዕድል አለህ” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ለሊባኖስ ሕዝብ አንድ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡ ይህ ጦርነት በቶሎ እንዲገባደድ ሀገራችሁን ከሄዝቦላህ ቀንበር ነፃ አውጡ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ኔታኒያሁ፤ የእስራኤል ጦር ኃይል የሐሰን ናስራላሕ ተተኪ ይሆናሉ የተባሉት መገደላቸውን ቢናገሩም የእስራኤል ጦር ኃይል ግን ሀሺም ሳፊየዲን ስለመገደላቸው ማረጋገጫ የለኝም ብሏል
ምንም እንኳ እስራኤል ላለፉት ሶስት ሳምንት ሄዝቦላህ ላይ ከባድ የተባለ ጥቃት ብትፈፅምም ቡድኑ አሁንም የመልስ እርምጃ ማድረጉን ቀጥሏል።
የሊባኖስ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ባለፉት ሳምንታት በደረሱ ጥቃቶች 1400 ሰዎች ሲገደሉ 1.2 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሐሰን ናስራላሕ ምክትል የነበሩት ናይም ቃሲም ማክሰኞ ዕለት ሲናገሩ ሄዝቦላህ ከእስራኤል የደረሰበትን “ኪሳራ” ተቋቁሞ አሁንም “እየተንቀሳቀሰ” ይገኛል ብለዋል።
በጋዛ ያለውን ጦርነት ተከትሎ በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል የድንበር ግጭት መባባሱ ይታወሳል። ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ድንበር ሮኬቶችን ሲተኩስ እስራኤል ደግሞ ድንበር አካባቢ ያሉ ዜጎቼን እጠብቃለሁ ብላ የመልስ ምት ስትሰጥ ከርማለች።
አይዲኤፍ ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው 146ኛው ክፍለ ጦር በደቡብ ምዕራብ ሊባኖስ “ውሱን እና ዒላማውን የጠበቀ” ጥቃት ማድረግ ጀምሯል።
እስራኤል እግረኛ ጦሯን ወደ ሊባኖስ የላከችው በአውሮፓውያኑ መስከረም 30 ሲሆን በጠቅላላው 15 ወታደሮች እንደተሰማሩ ተነግሯል።
አይዲኤፍ እንደሚለው ወታደሮቹ ድንበር ላይ የምትገኘው እና የሄዝቦላህ “ጠንካራ የውጊያ ቀጣና” የምትባለው ማሩን አል-ራስ ከተማን ተቆጣጥረዋል። ከሥፍራው የወጡ ናቸው የተባሉ ፎቶዎች እንደሚያሳዩት የወይራ ዘይት ማሳ ውስጥ የተተከለ የሄዝቦላህ ሮኬት ማስወንጨፊያ እና ሌሎች የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በሌላ በኩላ በድሮን የተቀረፁ ምስሎች ደግሞ ያሩን በተባለችውና የእስራኤል እግረኛ ጦር በተቆጣጠራት መንደር አቅራቢያ ከፍተኛ ውድመት አሳይተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሊባኖስ አስተባባሪ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል ኃላፊ በግጭቱ ምክንያት እየደረሰ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ “እጅግ አሳሳቢ” ነው ብለዋል።
የሊባኖስ መንግሥት 1.2 ሚሊዮን ሰዎች መሰደዳቸውን አስታውቆ 180 ሺህ የሚሆኑት በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል።
የዓለም የምግብ ድርጅት ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት ሊባኖሳዊያን ራሳቸውን መመገብ አልቻሉም ሲል ስጋቱን አጋርቷል።
አይዲኤፍ ሰኞ ዕለት በዋና ከተማዋ ቤይሩት ባደረሰው ጥቃት የሄዝቦላህ ዋና መሥሪያ ቤት አዛዥ የሆኑት ሱሀይል ሁሴኒ መገደላቸውን ቢናገርም ሄዝቦላህ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም።
ሐሰን ናስራላህን ይተካሉ ተብሎ የሚጠበቁት ነባሩ የሄዝቦላህ አባል ሀሺም ሳፊየዲን አድራሻቸው አይታወቅም።












