ሊባኖስን የሚመራው ማን ነው? ሄዝቦላህስ በአገሪቱ ውስጥ ምን ሥልጣን አለው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ከባድ እና ያልተቋረጠ የአየር ድብደባ በተለያዩ ክፍሎች ላይ እየፈጸሙ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ እግረኛ ወታደሮቿ ወደ ሊባኖስ ዘልቀው ገብተዋል።
በዚህም የተነሳ ከ1000 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ ቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ሲሉ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ በሊባኖስ ተጽእኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ፓርቲ እና ታጣቂ ኃይል የሆነው ሄዝቦላህ እና የቀጣናው ኃያል አገር የሆነችው እስራኤል ወደ ግልጽ ወታደራዊ ግጭት መግባታቸውን ተከትሎ ነው።
የሄዝቦላህ ታጣቂዎች ከሊባኖስ ብሔራዊ ጦር ኃይል የበለጠ ጠንካራ ሲሆኑ፣ በአገሪቱ በሚገኙ የሺዓ ሙስሊሞች ዘንድም ከፍተኛ ድጋፍ አላቸው።
ሄዝቦላህ ምንም እንኳ በሊባኖስ ውስጥ ይፋዊ መንግሥታዊ ተቋም ባይሆንም ባለፉት አራት አስርት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ የበላይ ኃይል ለመሆን ችሏል።
ሊባኖስን የሚመራው ማን ነው?
በሊባኖስ ፖለቲካዊ ሥልጣን በተለያዩ የሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል የተከፋፈለ ነው።
በአውሮፓውያኑ 1943 ሊባኖስ ነጻነቷን ከፈረንሳይ ስታገኝ ስምምነት የተደረሰበት ኮንቬንሽን መሠረት፣ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ከማሮናይት የክርስትና ቡድን የሚመረጥ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሱኒ ሙስሊሞች እንዲሁም የፓርላማው አፈ ጉባዔ ደግሞ ከሺዓ ሙስሊሞች የሚሰየሙ ይሆናሉ።
ይህም በወቅቱ በሊባኖስ ይገኙ የነበሩ የተለያዩ የሃይማኖት ቡድኖች ያላቸውን አንጻራዊ ብዛት እና ስብጥር የሚያንጸባርቅ ነበር።
በዚያ ጊዜም ክርስቲያኖች ከአገሪቱ ሕዝብ ከግማሽ በላይ በመሆን የሱኒ እና የሺዓ ሙስሊሞችን በቁጥር ይበልጡ ነበር።
ይኹን አንጂ በርካታ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በሊባኖስ ያሉት ክርስቲያኖች፣ የሱኒዎች እና የሺዓ ሙስሊሞች የሃይማኖት ቡድኖች እያንዳንዳቸው ከአገሪቱ ሕዝብ 30 በመቶ የሚሸፍኑ በመሆናቸው ኮንቬንሽኑ ጊዜው ያለፈበት ነው ብለው ይከራከራሉ።
ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት ሁለቱ የእስልምና ዘርፎች ተከታዮች ከአገሪቱ ሕዝብ ከፍተኛውን ቁጥር ያላቸው ቢሆንም፣ በኮንቬንሽኑ መሠረት ግን በፓርላማው ውስጥ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች እኩል የመቀመጫ ብዛት አላቸው።
በተግባር ግን እስካሁን በሊባኖስ ውስጥ አንድ ፓርቲ ወይም የሃይማኖት ቡድን የአገሪቱን ሥልጣን ጠቅልሎ ይዞ አያውቅም። አገሪቱን የመሩ መንግሥታትም ሲዋቀሩ የቆዩት በፓርላማ አባላት ጥምረት የሚመሠረት ሲሆን፣ ሁሉም ታላላቅ ውሳኔዎችን ለመወሰን የጋራ በስምምነት ያስፈልገዋል።
ይህም ደግሞ ብዙ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ውድቀት ሲያስከትል ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሊባኖስ የሄዝቦላህ ሚና ምንድን ነው?
ሄዝቦላህ በአውሮፓውያኑ 1982 በተካሄደው የሊባኖስ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ደቡባዊ የአገሪቱን ክፍል ተቆጣጥረው የነበሩትን የእስራኤል ኃይሎችን በመቃወም የሺዓ ሙስሊሞች ታጣቂ ቡድን ሆኖ ነበር የተመሠረተው።
ስያሜው በአረብኛ “የፈጣሪ ፓርቲ” የሚል ትርጉም ያለው ሄዝቦላህ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፊ ድጋፍ እና ትጥቅ የሚቀርብለት በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ነው።
ሄዝቦላህ በይፋ ኅልውናውን ያሳወቀው በአውሮፓውያኑ 1985 ሲሆን፣ ልክ እንደ ቅርብ ወዳጁ ኢራን በሊባኖስ እስላማዊ መንግሥት መመሥረት እንደሚፈልግ አውጇል።
በተጨማሪም በደቡባዊ የሊባኖስ ግዛትን እና በፍልስጤም ግዛቶች ላይ የነበረውን እስራኤል ወረራ እንዲያበቃ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።
በአውሮፓውያኑ 2009 ባወጣው አዲስ ማኒፌስቶ ሄዝቦላህ፣ እስላማዊ አገር መመሥረት የሚለውን ሃሳቡን የሚያመለክት ነገር አላካተተም። ነገር ግን ከእስራኤል አንጻር ላይ ያለው አቋሙ ግን ባለበት ጸንቷል።
በ1990 (እአአ) የሊባኖስ የእርስ በእርስ ጦርነት ሲያበቃ ሁሉም ታጣቂ ቡድኖች ተዋጊዎቻቸውን ሲበትኑ ሄዝቦላህ ግን ተዋጊዎቹን እንደያዘ ቆይቷል። ለዚህም ምክንያቱ ደቡባዊ ሊባኖስን በወረራቸው ሥር ያደረጉትን የእስራኤል ኃይሎችም መዋጋት የሚል ነበር።
በመጨረሻ ላይ እስራኤል በአውሮፓውያኑ 2000 ላይ ጦሯን ከደቡባዊ ሊባኖስ ስታስወጣ ሄዝቦላህ ድል ተቀዳጀሁ ሲል አውጇል።
በማስከተልም ከአውሮፓውያኑ 1992 ጀምሮ ሄዝቦላህ ተወካዮቹ በአገሪቱ ፓርላማ ውስጥ ሚና እንዲኖራቸው ዕጩዎችን ለውድድር አቀረበ።
በአሁኑ ወቅት ሄዝቦላህ በሊባኖስ መንግሥት ውስጥ ሚኒስትሮች እና በርካታ የፓርላማ አባላት አሉት።
በተጨማሪም ሄዝቦላህ በርካታ የሺዓ ሙስሊሞች በሚገኙባቸው የሊባኖስ አካባቢዎች የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ይሰጣል።
ምንም እንኳን ሌሎች ፓርቲዎችም በተመረጡባቸው አካባቢዎች ተመሳሳይ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ ሲሆን ሄዝቦላህ ግን ከሁሉም በበለጠ ሰፊ ሽፋን እንዳለው ይታመናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሄዝቦላህ በሊባኖስ ውስጥ እንዴት ኃያል ሆነ?
ሄዝቦላህ በሊባኖስ ያለው ኃያልነቱ በአብዛኛው የሚመነጨው ካለው ታጣቂ ኃይሉ ነው። ምንም እንኳ ገለልተኛ ወገኖች የቡድኑ ታጣቂዎች ቁጥር በ20 ሺህ እና 50 ሺህ መካከል ነው ቢሉም፣ ሄዝቦላህ ግን 100 ሺህ ተዋጊዎች እንዳሉት ይናገራል።
ተቀማጭነቱን አሜሪካ ባደረገው ሴንተር ፎር ስትራቴጂክ እና ኢንተርናሽናል ስተዲስ የባለሙያዎች ተቋም ግምት መሠረት ሄዝቦላህ ከ120 ሺህ እስከ 200 ሺህ ሮኬቶች እና ሚሳዔሎች አሉት።
ይህም በዓለም ላይ ከመንግሥት ውጪ የሆነ ኃያል ታጣቂ ቡድን ያደርገዋል። በዚህም ሄዝቦላህ ከሊባኖስ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይልም የበለጠ ጠንካራ ሆኖ ይታያል።
ሄዝቦላህ የሊባኖስ መንግሥት ካለው ደካማ አቋም ተጠቃሚ በመሆን ጎልቶ ወጥቷል። ለምሳሌ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገሪቱ ፕሬዝዳንት በሚሆነው ግለሰብ ላይ ስምምነት መድረስ ባለመቻላቸው ሊባኖስ ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ያለፕሬዝዳንት ቆይታለች።
በዚህም የተነሳ ማዕከላዊው መንግሥቱ ሄዝቦላህ የራሱን አጀንዳዎች በአገሪቱ ውስጥ እንዳያስፈጽም መከላከል እንዳይችል ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












