ሄዝቦላህ ሊባኖስ ውስጥ ምን ያህል ድጋፍ አለው? የሚቃወሙትስ አሉ?

የሄዝቦላህ ደጋፊዎች በወታደራዊ ልብስ ሰልፍ ወጥተው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሊባኖስ ውስጥ የሺዓ ፓርቲ ሚናን በተመለከተ ከፍተኛ ክፍፍል ባለበት ሁኔታ ነው በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል ያለው ጦርነት የተቀሰቀሰው።

መስከረም 27 ሄዝቦላህ ፍልስጤማውያንን በመደገፍ በእስራኤል ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ከወሰደው እርምጃ ቀደም ብሎ የነበረ ክፍፍል ነው።

ክፍፍሎቹ ግን በሊባኖስ የሚገኙ የሄዝቦላህ ደጋፊዎችን እና ፀረ ሄዝቦላ የሆኑትን በቀላሉ ለመለየት አያመችም።

የሄዝቦላህ ጉዳይ አገሪቱ የፖለቲካ ውይይቶች ሁሉ ማዕከል ከሆነ ዓመታት አልፈው ዓመታት ተተክተዋል።

ከአካባቢው አገራት ተሻለ የንግግር ነጻነት ተከበረባት ነች በምትባለው ሊባኖስ፤ በአደባባይም እና በድብቅም በሚደረጉ ውይይቶች ውስጥ ከሄዝቦላህ ጎን መሰለፍ እና መቃወም የሚሉ ጉዳዮች ቁልፍ ሆነው ሰንብተዋል።

ስለ ሄዝቦላህ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ እና ወታደራዊ ትጥቅ እንዳለፉት ዓመታት ያለ የጦፈ ክርክር በሊባኖስ ውስጥ በስፋት ተስተውሎ አያውቅም።

መልከ ብዙው አቀራረብ

የሄዝቦላህ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሊባኖስ ጠንካራ ስለሆነው ወታደራዊ ቡድን እና በፖለቲካው መስክም ተጽዕኖው ከፍተኛ የሆነውን ቡድን ለመመልከት ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ።

ሊባኖስ ውስጥ ሃይማኖታዊ ማንነት በሰዎች ፖለቲካዊ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።

ብዙዎቹ የሄዝቦላህ ደጋፊዎች የሺዓ ሙስሊሞች ናቸው። አብዛኞቹ ተቺዎችቹ እና ተቃዋሚዎቹ የሱኒ ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች ናቸው።

ይህ ግን ትክክል የሚሆነው በተወሰነ መጠን ብቻ ነው።

ሄዝቦላህን ሙሉ በሙሉ የሚቃወሙ የተለያየ ሃይማኖታዊ እና ርዕዮተ ዓለማዊ አቋም ያላቸው ቡድኖች አሉ።

አብዛኞቹም በሊባኖስ ጦርነት ወይም ሰላም ስለመኖሩ የሚወስን እና የአገሪቱን መንግሥት የሚያኮስስ የኢራን ተላላኪ አድርገው ይቆጥሩታል። ኃያል የሆነው ጦሩ ትጥቅ እንዲፈታም ይጠይቃሉ።

ከሄዝቦላህ ጋር በብዙ ጉዳዮች የማይስማሙ ሆነው ለጦር መሳሪያው ድጋፍ የሰጡም አሉ።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከሄዝቦላህ ዋና ዋና የፖለቲካ አጋሮች አንዱ የሆኖ የዘለቀው ትልቁ የክርስቲያኖች ፓርቲ ፍሪ ፓትሪዮቲክ ፓርቲ (ኤፍፒኤም) ነበር። ለዓመታት ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ለመደጋገፍ የሚያስችል ስምምነት ነበራቸው።

የክርስቲያን ፓርቲ የሆነው ኤፍፒኤም በአንድ ወገን የሚደግፈው የሺዓ የፖለቲካ አጋር ሲያገኝ፣ በሌላኛው ጫፍ ደግሞ ሄዝቦላህ በፍጥነት ትጥቅ እንዲፈታ የማይጠይቅ የክርስቲያን ደጋፊ አገኘ።

ምንም እንኳን ስምምነቱ የተቋረጠ ቢሆንም በሊባኖስ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ቡድኖች እንዴት በሃይማኖታዊ መስመር ላይ ጥምረት መፍጠር እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው።

በበቂ ያልተደራጀው ጦር

አንዳንዶች ሄዝቦላህን ትጥቅ እንዲፈታ ይጠይቃሉ። ሌሎች ደግሞ ኃይሉ በጣም ጠንካራ ስለሆነ ፓርቲውን ይደግፋሉ።

የሄዝቦላህ ወታደራዊ ጥንካሬ እና የሊባኖስ ብሔራዊ ጦር ደግሞ በአንጻራዊነት ደካማ መሆኑ ብዙዎች (ሄዝቦላህን ከሚደግፉት ውጭ ያሉት ጭምር) ቡድኑ ታጥቆ መቀጠሉ አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ።

እስራኤል እአአ በ1982 ሊባኖስን ወረረች። የበዚህም አገሪቱን ደቡባዊ ክፍል እስከ 2000 ድረስ ተቆጣጥራለች። አሁንም የተወሰነውን ክፍል ይዛለች።

በአሁኑ ወቅት ሊባኖስ ውስጥ የእስራኤል ሠራዊትን ለመዋጋት ውጤታማ የሆነው ብቸኛው ኃይል የሄዝቦላህ ጦር ነው።

የሊባኖስ ጦር በደንብ የተደራጀ አይደለም። የጦር መሣሪያ የሚያገኘው ከአሜሪካ እና በከሌሎች ምዕራባውያን አገራት ነው። እነዚህም ቢሆኑ ጊዜ ያለፈባቸው ናቸው።

ይህን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለፓርቲው ድጋፍ ባይኖራቸውም ብዙዎች የሄዝቦላህ ጦር እንዲቀጥል ይደግፋሉ።

እስራኤል በርካታ ሄዝቦላህ የጦር አመራሮችን ገድላለች

“የአንድነት ግንባር”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሊባኖስ ውስጥ ያለው የተወሳሰበ የሐዘኔታ፣ የጠላትነት እና የድጋፍ ድር ባለፉት ቀናት ከእስራኤል ጋር እንደቀጠለው ዓይነት የደንበር ተሻጋሪ ግጭት ወቅት ይበልጥ ይወሳሰባል።

እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ብዙ ሰዎች ልዩነታቸውን ወደ ጎን ያደርጋሉ።

ሄዝቦላህ ጋዛን በመደገፍ በእስራኤል ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መወሰኑ አገሪቱን ወደ ከባድ ቀውስ እየጎተተ ነው ብለው የሚወነጅሉ ብዙ ተቺዎች ጭምር በቅርቡ ለተፈጸመው ግንኙነት መሳሪያዎች ፍንዳታ ጥቃት ሰለባዎች አጋርነታቸውን አሳይተዋል።

በእነዚህ በገመድ አልባ መገናኛዎች ላይ በደረሱ ፍንዳታዎች፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ጥቂት የማይባሉትም ተገድለዋል። ምንም እንኳን እስራኤል ኃላፊነቱን ባትወስድም ብዙዎች ጣታቸውን ቀስረውባታል።

በቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻ በርካቶች የሚኖሩበትን ዳሂህን ዒላማ ያደረገውን የእስራኤል ጥቃት እና በደቡብ ሊባኖስ እና በቤካ ሸለቆ የአየር ጥቃት መጀመሩን ተከትሎ ይህ የአንድነት ግንባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ይህም ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች እንዲገደሉ እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ደግሞ እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።

በቤይሩት የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ጀሚል ሙዋድ “ተፈጥሯዊ ትብብር ነበር” ብለዋል።

“ፀረ ሄዝቦላህ ቡድኖችን ጨምሮ በአገሪቱ ውስጥ ሰፊ ፀረ እስራኤል ስሜት እንዳለ ለእኔ ግልፅ ነው።”

“ብዙ ሰዎች መከፋፈሉን ለጊዜው ወደ ጎን ማለት አለብን እያሉ ነው። ይህ ርዕዮተ ዓለም ወይም ፖለቲካዊ አመለካከት ሳይሆን እስራኤል እየፈጸመች ካለው ግፍ አንፃር ትክክለኛ ነው” ሲሉም አክለዋል።

በሄዝቦላህ ዙሪያ ያለው መለያየት አሁንም ጉልህ ሲሆን፣ እስራኤልም ይህንን ክፍተት ለማስፋት እየሞከረች ይመስላል።

የእስራኤል ጄቶች በደቡብ በኩል የሚገኙትን የሊባኖስ ከተሞችን እና የቤካ ሸለቆን ባጠቀቡት ወቅት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለሊባኖስ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት “የእስራኤል ጦርነት ከእናንተ ጋር አይደለም። ከሄዝቦላህ ጋር ነው" ብለዋል።

ድንበር ተሻጋሪው ግጭት ሊመስፋፋም ሆነ ሊረግብ የሚችለው ሄዝቦላህ ሊባኖስ ውስጥ በሚኖረው የድጋፍ መጠን ነው።