ትንታኔ፡ የእስራኤል አዲስ ጥቃት እና እጅግ የተቆጣው፣ እስከ አፍንጫው የታጠቀው ሄዝቦላህ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
- ፀሐፊ, ጄሬሚ ቦዌን
- የሥራ ድርሻ, ዓለም አቀፍ አርታዒ
የእስራኤል ባለሥልጣናት በሄዝቦላህ ላይ እየወሰዱት ባለው እርምጃ ኩራት የተሰማቸው ይመስላል ይላል የቢቢሲው ተንታኝ ጀሬሚ ቦዌን።
እስራኤል ሄዝቦላህ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ማድረስ የጀመረችው ባለፈው ሳምንት ፔጀር እና ዎኪ ቶኪ በተባሉ የመገናኛ መሣሪያዎች በመታገዝ ነው።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮኣቭ ጋላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰኞ ዕለት አገራቸው የሰነዘረችውን ጥቃት ሲያወድሱ ተሰምተዋል።
ሚኒስትሩ እንደሚሉት እስራኤል በሰነዘረችው የአየር ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ የሄዝቦላህ ሮኬቶች መውደማቸውን ሲኣሳውቁ፤ ሊባኖስ ደግሞ በአየር ጥቃቱ 50 ሕፃናትን ጨምሮ ከ550 በላይ ዜጎች ተገድለዋል ብላለች።
ሄዝቦላህ እና እስራኤል በአውሮፓውያኑ 2006 ለአንድ ወር የቆየ ደም አፋሳሽ ጦርነት ማካሄዳቸው ይታወሳል።
እስራኤል ሄዝቦላህ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ማድረሷ የቡድኑ መሪ ሐሰን ናስራላህ እና የሄዝቦላህ ደጋፊ የሆነችው ኢራን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያደርጋቸዋል የሚል እምነት አላት።
የእስራኤል ፖለቲከኞች እና ጄኔራሎች ድል ይፈልጋሉ። በጋዛ ያለው ጦርነት አንድ ዓመት ሊሞላው ነው። አሁን የሐማስ ታጣቂዎች ከተደበቁበት እየወጡ የእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት ያደርሳሉ፤ እስራኤላውያንን አፍነው ይወስዳሉ።
ሐማስ እስራኤል ላይ የፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ብዙዎች ያልጠበቁት ነበር። እስራኤል ሐማስን በጣም የሚያሰጋ ቡድን ነው ብላ አታስብም። የሊባኖስ ጉዳይ ከዚህ የተለየ ነው።
በ2006 ጦርነት በኋላ የእስራኤል መከላከያ ኃይል እና የስለላ ድርጅቱ ሞሳድ ሄዝቦላህ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲዘጋጁ ነው የቆዩት።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አሁን አገራቸው እያደረሰችው ያለችው ጥቃት የሄዝቦላህን አቅም ሊያዳክመው ይችላል ብለው ያምናሉ።
ኔታኒያሁ፤ ሄዝቦላህ በድንበር በኩል እስራኤል ላይ የሚተኩሳቸውን ሮኬቶችን እንዲያቆም ይፈልጋሉ። የእስራኤል ጦር ዓላማ ደግሞ ድንበር አካባቢ ያሉ የቡድኑ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ማውደም እና ሄዝቦላህን ከአካባቢው ማባረር ነው።
ሌላ ጋዛ?
በሊባኖስ እያየነው ያለው ነገር ባለፈው ዓመት በጋዛ ካየነው ጋር ተመሳሳይነት አለው።
እስራኤል ልክ እንደ ጋዛ ሊባኖስ ለሚገኙ ሰላማዊ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች። መልዕክቱ ጥቃት ከሚያሰጋቸው ቦታዎች ጥላችሁ ውጡ የሚል ነው። እስራኤል ልክ እንደ ሐማስ ሄዝቦላህ ሰላማዊ ሰዎችን መሸሸጊያ እያደረገ ነው ስትል ትከሳለች።
አንዳንድ ተቺዎች እና እስራኤል ጠላቶቼ ናቸው የምትላቸው ሰዎች የእስራኤል ማስጠንቀቂያ ሰላማዊ ዜጎች ቤታቸውን ጥለው እንዲወጡ በቂ ጊዜ አልሰጠም ይላሉ።
የጦርነት ሕግ ሰላማዊ ዜጎች በየትኛውም መንገድ እንዲጠበቁ፣ ያልተገደበ ጥቃት እንዳይደርስባቸው እንዲሁም መጠን አልባ ውድመት እንዳይወርድባቸው ያትታል።
እስራኤል የጦር ኃይሏ የሞራል ልዕልና ያለው እና ሕግ አክባሪ እንደሆነ ነው የምትናገረው። ነገር ግን በጋዛ ባካሄደችው ዘመቻ ከበርካቶች ከፍተኛ ነቀፌታ ገጥሟታል። አሁን ትልቅ ስጋት የሆነው በቀጣናው የለየለት ጦርነት ይነሳ ይሆን የሚለው ጥያቄ ነው።
የፔጀር ጥቃቱን እንመልከት። እስራኤል ይህ ጥቃት የሄዝቦላህ አባላትን ነጥሎ ለመምታት የተዘጋጀ ነው ትላለች።
ነገር ግን ፔጀሮቹ ሲፈነዱ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች የት ሊሆኑ ይችላሉ የሚለውን ማወቅ አትችልም። ለዚህ ነው በፔጀር ጥቃት ሕፃናትን ጨምሮ ሌሎች ሰላማዊ ዜጎች የተገደሉት።
አንዳንድ ጉምቱ የሕግ አዋቂዎች እስራኤል ሕይወት አጥፊ የሆነ መሣሪያ ሰላማዊ ዜጎች ባሉበት አካባቢ ተጠቅማለች፤ ይህ ደግሞ የጦርነት ሕግን የጣሰ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።
የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ግጭት የተጀመረው በአውሮፓውያውኑ 1980ዎቹ ነው። ነገር ግን ይህ አሁን እያየነው ያለው ግጭት የሐማስን ጥቃት ተከትሎ የመጣ ነው።
በወቅቱ ናስራላህ አባሎቻቸው ለሐማስ ድጋፍ ለማሳየት ድንበር አካባቢ በየቀኑ የተገደበ ጥቃት እንዲያደርጉ አዘው ነበር። ይህ ጥቃት የእስራኤል ጦርን ያጨናነቀ እና በሥፍራው ይኖሩ የነበሩ 60 ሺህ ገደማ ሰዎች ያፈናቀለ ነው።
የስድስት ቀናቱ ጦርነት ቃጭል
የተወሰኑ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ከሰሞኑ ሄዝቦላህ ላይ የደረሰውን ጥቃት ከ“ኦፕሬሽን ፎከስ” ጋር እያነፃፀሩት ነው። ኦፕሬሽን ፎከስ በአውሮፓውያኑ 1967 እስራኤል ግብፅ ላይ የሰነዘረችው ቅፅበታዊ ጥቃት ነው።
ይህ ጥቃት የግብፅ አየር ኃይል አውሮፕላኖች ተደርድረው ቆመው ሳለ የደመሰሰ ነው። እስራኤል በስድስት ቀናት ውስጥ ግብፅ፣ ሶሪያ እና ጆርዳንን አርበደበደች። በዚህ ድል ሳቢያ እስራኤል ዌስት ባንክን፣ ምሥራቅ እየሩሳሌምን፣ የጋዛ ሰርጥን እና የጎላን ኮረብታዎችን ተቆጣጠረች።
እርግጥ ነው አሁን እያየነው ያለው ግጭት ከስድስት ቀናቱ ጦርነት ጋር የሚነፃፀር አይደለም። እስራኤል ሄዝቦላህ ላይ ከባድ ኪሳራ አድርሳለች። ነገር ግን አሁንም ሄዝቦላህ ሮኬቶቹን ከመተኮስ ወደኋላ አላለም።
ምንም ያህል እስራኤል ከባድ ጥቃት ሄዝቦላህ ላይ ብታደርስ ውጤቱን መገመት አዳጋች ነው። ለዚህ ነው ከሄዝቦላህ ጋር የገባችው ግጭት ቁማር ነው የሚባለው። ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት አቁሞ ሊያፈገፍግ ይችላል። ታዛቢዎች ግን ሄዝቦላህ ጥቃቱን ያቆማል ብለው አያስቡም። የሄዝቦላህ ኅልውና ዋና ዓላማ እስራኤል ላይ ጥቃት ማድረስ ነው።
እስራኤል ግጭቱን አፋፍማ የመሬት ላይ ዘመቻ በመጀመር ድንበር አካባቢ አንድ መሬት ይዛ እንደ መከላከያ ቀጣና ልትጠቀምበት ትችላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል ሊባኖስን ስትወር የመጀመሪያዋ አይደለም። በአውሮፓውያኑ 1982 የእስራኤል ወታደሮች ፍልስጤማውያን የሚያደርሱትን ጥቃት ለመመከት ወደ ቤይሩት ዘልቀው ገብተው እንደነበር ይታወሳል። በ1990ዎቹ እስራኤል የሊባኖስን የተወሰነ መሬት ይዛ ነበር።
የዛሬዎቹ የእስራኤል ጄኔራሎች በወቅቱ ለጋ ወታደሮች ነበሩ። እስራኤልን ከሊባኖስ ምድር ለማስወጣት ሲታገል የነበረውን ሄዝቦላህን ተዋግተዋል። በ2000 እስራኤል ሊባኖስን ለቃ ወጣች።
በ2006 ደግሞ ሄዝቦላህ ባልተጠና መንገድ ወደ እስራኤል ገብቶ የእስራኤል ወታደሮችን ገድሎ የተወሰኑትን ደግሞ ማርኮ ተመለሰ። አስራኤል በአየር ኃይሏ እና በምድር ጦሯ ታግዛ አፀፋዊ ጥቃት ፈፀመች።
የ2006ቱ ጦርነት ተጠናቆ የእስራኤል ወታደሮች ወደ ግዛታቸው ሲመለሱ እንኳ ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬት ይተኩስ ነበር።
ጦርነት ዛሬ እና ነገ
የእስራኤል የጦር አዛዦች ወደ ሊባኖስ ማቅናት ወደ ጋዛ እንደማቅናት ቀላል እንዳልሆነ ያውቁታል። ልክ እንደ እስራኤል ሁሉ ሄዝቦላህም ከ2006 ጀምሮ ለጦርነት ሲዘጋጅ ነበር። ዝግጅቱን ሲያደርግ የነበረው በጣም ተራራማ እና ለሽምቅ ውጊያ አመቺ በሆነው የደቡብ ሊባኖስ ግዛት ነው።
እስራኤል ሐማስ የገነባቸውን ዋሻዎች አውድማ አልጨረሰችም። ሄዝቦላህ ደግሞ ላለፉት 18 ዓመታት በደቡብ ሊባኖስ ዋሻዎችን ሲገነባ ነው የከረመው። ከሐማስ የተሻለ የጦር መሣሪያ ክምችት አለው። ኢራን ከሐማስ ይልቅ ሄዝቦላህን ለመደገፍ መልክዓ ምድራዊ ሁኔታው ያመቻታል።
ሄዝቦላህ 30 ሺህ ገደማ ውጊያ ላይ ያሉ እና 20 ሺህ ተጠባባቂ ወታደሮች እንዳሉት ይገመታል። አብዛኞቹ ወታደሮች በሶሪያ የአሳድ መንግሥትን በመደገፍ የጦርነት ልምድ ያካበቱ ናቸው።
ቡድኑ ከ120 ሺህ እስከ 200 ሺህ የሚገመት ሚሳዔል እና ሮኬቶች እንዳሉት ይታመናል። አንዳንዶቹ የጦር መሣሪያዎች ወደ እስራኤል ዘልቀው ከተማዎችን የመምታት አቅም አላቸው።
እስራኤል የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን እኒህን ረዥም ርቀት ተጓዥ መሣሪያዎች አይጠቀምባቸውም ብላ ታስባለች። ኢራንም ሄዝቦላህ እኒህን መሣሪያዎች ለክፉ ጊዜ ማለትም እስራኤል ኢራን ላይ ጥቃት ስትነዘር እንዲጠቀምባቸው ነው የምትፈልገው። ይሄም ሌላ ቁማር ነው። ሄዝቦላህ በእስራኤል ከመጥፋቱ በፊት ያሉትን የጦር መሣሪያዎች ሊጠቀም ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተስፋ የሌለው ዲፕሎማሲ
በዩናይትድ ስቴትስ የሚመሩት የእስራኤል አጋሮች እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር የገባችውን ግጭት አባብሳ ወደ ሊባኖስ እንድትገባ አይፈልጉም። ሰላም ወርዶ ዜጎች ወደ ቀያቸው ሊመለሱ የሚችሉት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ነው ይላሉ።
አንድ የአሜሪካ ልዑክ የ2006ቱ ጦርነት እንዲቆም ምክንያት በሆነው የተባበሩት መንግሥታት ስምምነት ላይ ተመሥርቶ አዲስ ስምምነት እያረቀቀ ነው።
ነገር ግን ዲፕሎማቶች በጋዛ ያለው ጦርነት እስካላበቃ ድረስ ምንም ማድረግ አንችልም ይላሉ። ሐሰን ናስራላህ ቡድናቸው ጥቃት የሚያቆመው በጋዛ ያለው ጦርነት ሲያበቃ ብቻ ነው ይላሉ። አሁን ባለው ሁኔታ እስራኤልም ሆነች ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ የሆኑ አይመስሉም።
ምጣኔ ሀብቷ የደቀቀው ሊባኖስ አሁን የእስራኤል አየር ኃይልን ጥቃት እየቀመሰች ትገኛለች። በርካታ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው በመሸሽ ላይ ይገኛሉ።
እስራኤል ሄዝቦላህን ከድንበሯ ለማባረር ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ብላ ያመነች ይመስላል። ቢሆንም እየተጋፈጠች ያለችው ጠላት “በጣም የተቆጣ እና እስከ አፍንጫው የታጠቀ” ነው። ይህ ግጭት በጊዜ ካልተቋጨ ማቆሚያ ወደሌለው ቀውስ ሊያመራ እንደሚችል ለመናገር ተንታኝ መሆን አያሻም።













