እስራኤል በእግረኛ ጦር ሊባኖስን ብትወር ምን ሊፈጠር ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል በሊባኖስ ላይ እየፈጸመችው ያለው የአየር ጥቃት እግረኛ ጦር እንዲገባ የሚደረግ ዝግጅት መሆኑን የእስራኤል መከላከያ ኃላፊ ኸርዚ ሀሌቪ ተናግረዋል።
“የጀቶቹ ድምጽ ይሰማል። ቀኑን ሙሉ የአየር ድብደባ ስንፈጽም ነበር፤ ይህን ያደረግነው እግረኛ ጦር አስገብተን ሄዝቦላህን ለመውጋት ነው” ብለዋል።
በእስራኤልና ሊባኖስ መካከል ከሰሞኑ የተባባሰው ግጭት ብዙዎች እአአ በ2006 የተደረገውን ጦርነት እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል።
ያኔም እስራኤል የአየር ድብደባ ካደረገች በኋላ እግረኛ ጦሯ ወረራ ፈጽሟል።
ሐማስ እስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ሄዝቦላህም ከደቡባዊ ሊባኖስ በእስራኤል ላይ ጥቃቶች እየፈጸመ ነው።
እስራኤል የእግረኛ ወረራ ብትፈጽም ምን ሊከሰት ይችላል? የሚለውን ይህ ዘገባ ይዳስሳል።
በሰሜን እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር ባለው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወደ 60,000 የሚጠጉ ነዋሪዎችን በሰላም እንደሚመልሱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ደጋግመው ተናግረዋል።
ረቡዕ መስከረም 15/2017 ዓ.ም. እስራኤል ሄዝቦላህን ለማጥፋት ወደ ሊባኖስ መግባት እንደምትፈልግ ግልጽ ሆኗል።
የእስራኤል መከላከያ ኃላፊ ኸርዚ ሀሌቪ “እንገፋበታለን። አናቆምም። በየአቅጣጫው ድብደባ እንቀጥላለን። ግባችን ግልጽ ነው። የጠላት ግዛት እንገባለን። ሄዝቦላህ ወታደራዊ መቀመጫ ያደረጋቸው መንደሮች ውስጥ እንገባለን” ብለዋል።
እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት እስካሁን የተገደሉ ሰዎች ከ550 በላይ ናቸው። እስራኤል በሊባኖስ ዒላማ ያደረገችው ሄዝቦላህን መሆኑን ተናግራለች።
የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ግን ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ የሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም ንጹሃን ዜጎች ከተገደሉት መካከል ይገኙበታል ብሏል።
የአየር ጥቃቱ የቀጠለ ሲሆን፣ የእግረኛ ጦር ወረራ ሊኖር እንደሚችልም ተንታኞች ገምተዋል።
እስራኤል በሊባኖስ ምን ልታደርግ ትችላለች?
ከዚህ ቀደም እስራኤል በሊባኖስ የተለያዩ ኦፕሬሽኖችን አካሂዳለች።
አሁን ሊፈጠር የሚችለውን ለመረዳት ወደኋላ መለስ ብሎ የእስራኤልን ወረራዎች መቃኘት ያሻል። በአውሮፓውያኑ ከ1982 እስከ 2006 ወረራዎች ተፈጽመዋል።
በ1982 የእስራኤል ኃይሎች ሊባኖስ ገብተው የፍልስጤማውያንን ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት ለማስቆም ሞክረዋል።
በወቅቱ የፍልስጤማ ነጻነት ተቋም (ፒኤልኦ) እና መሪው ያሲር አራፋት ለእስራኤል ዕውቅና አይሰጡም ነበር። እስራኤልም ለፍልስጤም ዕውቅና አትሰጥም ነበር።
ወረራው መጠነ ሰፊ ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች፣ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ታንኮችን አሳትፏል።
የአየር፣ የባሕር እና የእግረኛ ጦር ጥቃት ተፈጽሟል። እስራኤል በተለያየ አቅጣጫ ወረራ ከከፈተች በኋላ በሳምንት ውስጥ የሊባኖስ መዲና ቤሩት አቅራቢያ ደርሳለች። ከተማዋ ላይም ከበባ ተፈጽሟል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የ1982ቱን ወረራ ዓለም እንዴት ያየዋል?
ያሲር አራፋት እና ይደግፏቸው የነበሩ ወደ 2,000 የሚጠጉ የሶሪያ ወታደሮች ከሊባኖስ ለመውጣት ተገደዋል።
በወቅቱ የኤቢሲ ጋዜጠኛ “በመርከብ ወደ ግሪክ እየተጓዙ ያሉት ያሲር አራፋት በሊባኖስ ያላቸው ቆይታ ካስከተለው ቀውስ በኋላ ሌላ የሚያስጠጋቸው የአረብ መንግሥት ያለ አይመስልም” ብሎ ነበር።
ያኔ እስራኤል በመላው ዓለም ወቀሳ ደርሶባታል።
በመስከረም 1982 በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ቤይሩት ውስጥ በክርስቲያን ታጣቂዎች ሲገደሉ የእስራኤል ወታደሮች ምንም አላደረጉም።
‘የሳብራ እና ሻቲላ ጭፍጨፋ’ በሚል ይታወቃል።
ይህ ከመሆኑ ከአራት ዓመታት በፊት የተመረጡት ፕሬዝዳንት በሽር ገማልን ግድያ ለመበቀል የተፈጸመ እንደሆነ ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እአአ በ2006 የተፈጸመው የእስራኤል ወረራ በ1982 ከተፈጸመው ጋር ሲነጻጸር ዘገም ያለና ውስን ነበር።
በሊባኖስ የሚገኙ ከተሞች ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን ያዳረሰ ነበር።
የእስራኤል የፖለቲካ ተንታኝ ዮአቭ ስተርን ቀጣዩ የእስራኤል የእግረኛ ጦር ወረራ በ1982 እንደነበረው ይሆናል ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ።
እስራኤል ከፍተኛ እና ሙሉ ወረራ ከመፈጸም ይልቅ በደቡብ ሊባኖስ ከተሞችን አንድ በአንድ ልትይዝ እንደምትችልም ያክላሉ።
ይህም በ2006 ከነበረው ወረራ ጋር ተመሳሳይ ነው።
ሆኖም በሊባኖስ ግዛቶች ውስጥ የበለጠ ዘልቆ መግባትን እስራኤል አማራጭ ልታደርግ ትችላለች።
እስከ ሊታኒ ወንዝ ድረስ ልትደርስም ትችላለች። ይህ ወንዝ በሁለቱም ወገኖች በኩል ቁልፍ ስፍራ ነው።
ተንታኙ ግምታቸውን ያስቀመጡት ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ ያለውን የረዥም ጊዜ ይዞታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
እስራኤል በቶሎ አካባቢውን እንዳትቆጣጠር ሊያደርግም ይችላል።
የቀድሞ ጄኔራል እና ወታደራዊ ተንታኝ ሒሻም ጃባር እንደሚሉት፣ የእስራኤል ወታደሮች ደቡባዊ ሊባኖስ ቢገቡም የመቆየት ዕድል አይኖራቸውም።
“እስራኤል በ2006 በእግረኛ ጦር ወረራ ምን ሊገጥማት እንደሚችል አይታለች። አሁን ወረራው ሌላ ቅርጽ ሊይዝ ይችላል” ይላሉ ተንታኙ።
ወረራው በድንበር አካባቢ ሊሆን እንደሚችል እና ጠባብ እንደሚሆን ይገምታሉ። ይህም ከአንድ ቀን በላይ ሊዘልቅ አይችልም ይላሉ።
እስራኤል ከእግረኛ ጦር ወረራ ይልቅ የአየር ጥቃት ላይ ትኩረት ልታደርግ እንደምትችል ይገልጻሉ።
ወረራው የት አካባቢ ሊሆን ይችላል?
የቀድሞ ጄኔራል እና ወታደራዊ ተንታኝ ሒሻም ጃባር እንደሚሉት፣ የአሁኑ ዘመቻ በሊባኖስ የድንበር አካባቢ የሚወሰን ጥቃት ነው ሊሆን የሚችለው። ሆኖም እስራኤል በሌሎች የሊባኖስ አካባቢዎች ‘የኮማንዶ ኦፕሬሽኖች’ እንደምታካሂድ ይገልጻሉ።
የእስራኤል የፖለቲካ ተንታኝ ዮአቭ ስተርን፣ ወረራው ደቡባዊ ሊባኖስን እንደሚያዳርስ ያምናሉ። ይህን በሊባኖስ እና በእስራኤል መካከል ያለ የሊታኒ ወንዝ ድንበር ነው ይላሉ።
ከወንዙ በስተሰሜን እስራኤል ጥሳ ለመግባት የምታደርገውን ጥረት ሳይጠቅሱ አላለፉም።
በአካባቢው ገብታ ልትወጣ እንደምትችል ያስረዳሉ። እስራኤል ወደ ሊባኖስ ዘልቃ ከገባች ለወደፊት የመደራደር አቅሟን ከፍ ሊያደርገው እንደሚችልም ያክላሉ።
በ1982 የተካሄደው ወረራ ሦስት ዋነኛ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነበር። እነዚህም ደቡባዊ ሊባኖስ አካባቢ ያሉት ጋሊሌ ፊንገር እና ቤካ ቫሊ እንዲሁም በደቡባዊ ቤይሩት ያለው ተራራማ ስፍራ ናቸው።
በሲዶን ከተማ የባሕር ጥቃት እና የእግረኛ ጦር ወረራም ተከናውኗል።

የፎቶው ባለመብት, Copyright Israel Defense Forces
የወረራው ግብ ምን ይሆናል?
የ1982 ጦርነት ግብ በእስራኤል ደቡባዊ ክፍል የፍልስጤም ተዋጊዎች ያደርሱት የነበረውን የሮኬት ጥቃት መከላከል ነበር።
ተዋጊዎቹን ወደ እስራኤል እና ሊባኖስ ድንበር አቅጣጫ 25 ማይሎች ለመግፋት ሙከራ ተደርጓል።
የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት መሠረተ ልማት ማውደም ሌላው የእስራኤል ግብ ነበር። ይህም በቤይሩት ያለውን ዋና መቀመጫ ይጨምራል።
እስራኤል የሶሪያን ጦር ከሊባኖስ ለማስወጣትም አስባ ነበር።
የያኔው ወረራ በደቡባዊ ሊባኖስ የተወሰነ ሳይሆን ቤካ ሸለቆ እና የቤይሩት ተራራማ አካባቢ ቻኡፍን የጨመረ ነበር።
የቀድሞ ጄኔራል እና ወታደራዊ ተንታኝ ሒሻም ጃባር እንደሚሉት፣ የእስራኤል ጠባብ የእግረኛ ጦር እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ወታደራዊ አካሄድ ላይ ዘለቄታዊ ውጤት ላያመጣ ይችላል።
የእስራኤል የፖለቲካ ተንታኝ ዮአቭ ስተርን እንደሚሉት፣ የእስራኤል ዋነኛ ግብ በደቡባዊ ሊባኖስ የሄዝቦላህ ተዋጊዎችን መጋፈጥ እና ከሊታኒ ወንዝ ባሻገር መግፋት ነው።
ይህም ዓላማው በመስከረም 26/2016 ዓ.ም. እስራኤል ከሐማስ የረፈጸመባትን ድንገተኛ ጥቃት የመሰለ እንዳይሰነዘርባት ቀድማ ለመከላከል ያለመ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።












