ጎዳና ማደር የጀመሩት ሊባኖሳዊያን

መዲና የ7 ወር ጨቅላ ይዛ ጎዳና ማደር ጀምራለች

የፎቶው ባለመብት, Goktay Koraltan / BBC

የምስሉ መግለጫ, መዲና የ7 ወር ጨቅላ ይዛ ጎዳና ማደር ጀምራለች

ሊባኖስ ጦርነትን አሳምራ ታውቃለች። ከ1975 ዓ/ም የጀመረው የሶሪያና ሊባኖስ ጦርነት 15 ዓመታት አስቆጥሮ ያበቃው በፈረንጆቹ 1990 ላይ ነው።

ከዚያ ደግሞ ሔዝቦላህና እስራኤል በፈረንጆቹ 2006 ጦርነት አድርገዋል።

ሊባኖሳዊያን ጦርነት ምን መሆኑን አሳምረው ያውቃሉ። ኖረውበታል።

ያም ሆኖ እንዲህ እንደ አሁኑ ዓይነት አስቀያሚ ጦርነት አላየንም ይላሉ። ይህን የሚሉት ገና በ9ኛ ቀኑ ነው።

የቤይሩት ዋና አስተዳዳሪ ማርዋን አቡድ በዚህ ይስማማሉ።

ባለፉት 10 ቀናት ሊባኖስ መአት የወረደባት ያህል ነው የተሰማት። ዜጎች ጎዳና ወጥተዋል። ሕንጻዎች አፈር ሆነዋል። ሕጻናት በረንዳ ማደር ጀምረዋል።

ሐሰን ነስረላህ መገደላቸውን ተከትሎ እስራኤል ጥቃቷን አጠናክራለች። ሔዝቦላህ በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ እንዳለ ይነገራል።

የቤይሩት ዋና አስተዳዳሪ ‘’ለአገሬ ሊባኖስ የከፋው ጊዜ አሁን ነው” ይላሉ። እርሳቸው ከሔዝቦላህ ጋር ግንኙነት የላቸውም።

“አዝናለሁ፤ በንጹሐን ሞት ክፉኛ ደንግጫለሁ፤ ከሁሉም በላይ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዝምታ ደንግጫለሁ” ይላሉ።

ቢቢሲ ዋና አስተዳዳሪውን ያነጋገራቸው በቤይሩት ''ሰማዕታት አደባባይ'' ነው። በዚያ በርካታ ዜጎች ጎዳና ወጥተው ይታያሉ። ከሰሞኑ አደባባይ የሚያድሩ ዜጎች ቁጥር ብዙ ነው። እነዚህ ዜጎች ወደዚህ አደባባይ የመጡት ከደቡባዊ ሊባኖስ ዳኒህ ነው። ያ አካባቢ ደግሞ የሔዝቦላህ ዋና መናኸሪያ የነበረ ነው።

ይህ ሁሉ አደባባይ የሚያድር ሕዝብ መቼ ወደ ቀዬው እንደሚመለስ አያውቅም። የሚደረግለት ድጋፍም የለም።

የእስራኤል ዓላማ ምን ይመስልዎታል? ተብለው የተጠየቁት የሊባኖስ ዋና አስተዳዳሪ፣ “እኔ ምኑን አውቄው፤ እስራኤል እንደሁ መግደል አይሰለቻት፣ ዛሬም ግድያ ነው፤ ነገም ግድያ ነው፤ በግድያ ላይ ግድያ፤ ፈጣሪ ይጠብቀን እንጂ ሌላ ምን ይባላል” ብለዋል።

ዋና አስተዳዳሪው ለቢቢሲ ሲናገሩ ድምጻቸው ከፍተኛ ሐዘን ተጭኖት፣ እንባ እየተናነቃቸው ነው። “ይህ ጊዜ በሕይወቴ መጥፎው ወቅት ነው” ይላሉ ሳግ በተናነቀው ድምጽ።

ከዚያ አደባባይ ብዙም ሳይርቅ በድንጋይ ላይ ቁጢጥ ብለው የተቀመጡ፣ ሐዘን ያኮራመታቸው እናቶች ይታያሉ።

መዲና ሙስጠፋ አሊ የሰባት ወር ልጇን አቅፋ እሽሩሩ ስትል ትታያለች። ገና ከዓርብ ዕለቱ ሰቀቀን አልወጣችም።

“ፍንዳታው አስደነገጠን። ፈራን። ልጆቼ አለቀሱ። እንደምንም ብለን አመለጥን። አሁን ጎዳና እናድራለን-የት መሄጃ አለን ታዲያ?” ትላለች።

ሌሎች ደግሞ ወደ ሰሜን ሊባኖስ እየተሰደዱ ነው። ደቡብ ሊባኖስ ሕይወትና ሞት ተወዳጅተውበታል ፣ለጊዜው።

ቢቢሲ በከተማዋ በተዘዋወረባቸው ጊዜ ሁሉ ሰዎች ባገኙት ተሽከርካሪ እየተንጠላጠሉ ከጦርነት በመሸሽ ላይ ነበሩ። ጎዳናዎች ነፍስን ለማዳን በሚደረግ ተጋድሎ ተሞልተዋል።

ባልዲ፣ ፍራሽና ሌሎች ቁሳቁሶችን ተሸክመው ወዲያ ወዲህ የሚንከላወሱም ብዙ ናቸው።

ከነስረላህ መገደል በኋላ ያለችው ቤይሩት ታስፈራለች። ሰዎች በስጋት ተሸብበው ይታያሉ። በዳሂያህ ግዛት አሁንም ቦምብ ይዘንባል። ፎቆች ወደ ትቢያን እየተቀየሩ ነው። ጭሱ ከሩቅ ይታያል።

አንዳንድ የሔዝቦላህ አባላት ጦር መሣሪያ ደግነው ነገር ግን ምን እንደሚያደርጉ ግራ ገብቷቸው ይታያሉ።

ክላሺንኮቭ ታጥቀው የአየር ክልል ጥቃትን ለመከላከል የሚሞክሩ ይመስላሉ። ወትሮ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች እንዲህ በግላጭ የጦር መሣሪያቸውን አንግተው አይታዩም ነበር። ምናልባት ይህ ተስፋ ማጣታቸውን አመላካች ይመስላል።

ሊባኖስ አሁን የጦር ቀጠና ሆናለች። ቀጠናው በሙሉ በጦርነት እንዳይማገድ ነው አሁን የሚፈራው።

ከዚህ በኋላ ሄዝቦላህ እስራኤልን የመምታት አቅም ይኖረዋል? ኢራን ለሔዝቦላህ ብላ እጇን ታስገባለች?

ኢራን ለጊዜው ለዘብ ማለትን መርጣለች። ኢራቅ፣ ሶሪያ እና የመን ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

የሦስት ቀናት ብሔራዊ የሐዘን ቀን ዛሬ ሰኞ ተጀምሯል። የሐዘን ቀናቱ ግን ሊራዘሙ ይችላሉ። የማብቂያ ቀናቸውም ቅርብ አይመስልም።