የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ በመንግሥት ውሳኔ በዓመት አንዴ ብቻ እንዲተገበር የሚያደርግ አዋጅ ጸደቀ

የፎቶው ባለመብት, ERIC LAFFORGUE
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካል በሚወስነው መሠረት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እንዲተገበር የሚያደርግ አዋጅ አጸደቀ።
አዋጁ የቤት ኪራይ የክፍያ ሥርዓት “በባንክ ወይም በሌላ ሕጋዊ በሆነ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ ብቻ” እንዲፈጸምም ያስገድዳል።
ምክር ቤቱ ይህንን “የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ” ያጸደቀው ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 24/2016 ዓ.ም. በነበረው ውሎው ነው።
በስድሰት ክፍሎች የተዋቀሩ ሰላሳ ሁለት አንቀጾችን የያዘው አዋጅ የጸደቀው ከዚህ በፊት ከነበረው ተሞክሮ በተለየ ሁኔታ ነው። ከዚህ በፊት የነበረው አሠራር አዋጆች እና ደንቦች በምክር ቤቱ ከመጽደቃቸው በፊት ለዝርዝር ዕይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴ ይመሩ ነበር።
በፓርላማው የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ይህ አዋጅ ከዚህ በፊት ከተለመደው ሂደት ውጪ እንዲጸድቅ ሞሽን አቅርበው በምክር ቤቱ ተቀባይነት አግኝቶ በቀጥታ ጸድቋል።
የአዋጁ አስፈላጊነት “የቤት ኪራይ ዋጋ የማኅበረሰቡን አቅም ያገናዘበ፣ ወቅታዊ እና ነባራዊ ሁኔታን መሠረት ያደረገ እንዲሆን” መሆኑ የአዋጁ ማብራሪያ ላይ ሰፍሯል።
በተጨማሪም አዋጁ “ያለአግባብ የሚደረግ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪን እና የቤት ኪራይ ውል መቋረጥን የሚያስቀር” ስለመሆኑ ማብራሪያው ያትታል።
የኪራይ ጭማሪ፣ አከፋፈል እና ሕጋዊነት
የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋን የተመለከተው የአዋጁ አንቀጽ የመኖሪያ ቤት አከራዮች በዘፈቀድ የኪራይ ዋጋ እንዳይጨምሩ ይከለክላል።
አዋጁ፤ “[አከራይ] የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ የሚችለው ተቆጣጣሪው አካል በዓመት አንድ ጊዜ ነባራዊ የኢኮኖሚውን ሁኔታ እና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ጉዳዮች ከግምት በማስገባት ሊወስን የሚችለውን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ መሠረት በማድረግ ነው” ብሏል።
አክሎም በአዋጁ መሠረት የሚደረገው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ፤ “በተቆጣጣሪው አካል በሰኔ አንድ ለሕዝብ ይፋ ተደርጎ ከሰኔ 30 ጀምሮ ለአንድ አመት የፀና ይሆናል” ይላል።
“የቤት ኪራይ ውል ዘመን ሳይጠናቀቅ ተከራይን ከቤት ማስወጣት ወይም በዚህ አዋጅ ከተፈቀደው ሁኔታ ውጪ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ አይቻልም” ሲል አዋጁ አስገዳጅ ድንጋጌ አስቀምጧል።
በአዋጁ መሠረት ተቆጣጣሪ አካል ማለት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውልን እና ዋጋን እንዲቆጣጠር በክልሎች ወይም በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የሚሰየም አካል ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አከራይ ከሁለት ወር የቤቱ ኪራይ በላይ ቅድመ ክፍያ መጠየቅ እንደማይችሉ አዋጁ ያትታል።
የቤት ኪራይ ክፍያዎች በባንክ ወይም በሌላ ሕጋዊ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ እንደሚፈጸሙ የሚደነግገው አዋጁ፤ አከራይ እና ተከራይ “የቤት ኪራይ ክፍያ ሰነዶችን አደራጅተው የመያዝ ግዴታ አለባቸው” ይላል።
ማንኛውም የቤት ኪራይ ውል በጽሁፍ የሚደረግ ሆኖ በተቆጣጣሪው አካል መረጋገጥ እና መመዝገብ እንዳለበት አዋጁ ላይ ሰፍሯል። አክሎም ሁለቱም ወገኖች የቤት ኪራይ ውሉ በተፈረመ ሰላሳ ቀናት ውስጥ “ውሉን አቅርበው እንዲረጋገጥ እና እንዲመዘገብ የማድረግ ግዴታ አለባቸው።”
በአዋጁ መሠረት “በዚህ አንቀጽ መሠረት ያልተረጋገጠ እና ያልተመዘገበ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል እንዳልተደረገ ይቆጠራል።” አዋጁን ተከትሎ የሚደረግ መኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ከሁለት ዓመት ሊያንስ እንደማይችል አዋጁ ያትታል።
የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ስለማቋረጥ
አዋጁ የደነገገው ሌላኛው ጉዳይ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ስለሚቋረጥበት ሂደት ነው።
ማንኛውም ቤት ኪራይ ውል የኪራይ ዘመኑ ሳይጠናቀቅ በአከራይ እና ተከራይ ስምምነት ተከራይ ቤቱን መልቀቅ ሲፈልግ የሁለት ወር ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠት ይኖርበታል።
አከራይ ያለማስጠንቀቂያ የቤት ኪራይ ውሉን ማቋረጥ የሚችለው በሰባት ምክንያቶች ብቻ መሆኑ በአዋጁ ላይ ተመላክቷል።
ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል አንደኛው፤ “[ተከራዩ] ቤቱን ያለአከራዩ ፈቃድ ከመኖሪያነት ውጪ ወይም ለንግድ ሥራ የሚጠቀምበት ከሆነ” ነው።
የቤት ኪራዩን በውሉ በተመለከተው የመክፈያ ጊዜ ለመጀመሪያ ከሆነ ከአስራ አምስት ቀን ካሳለፈ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ከሆነ 7 ቀን ካሳለፈ አከራዩ ውሉን ሊያቋርጥ እንደሚችል አዋጁ ላይ ተመልክቷል።
“[ተከራይ] በቤቱ ውስጥ የወንጀል ተግባር የሚፈጽም ወይም ቤቱን ለወንጀል መፈጸሚያ የሚጠቀምበት ከሆነ” አከራይ ውሉን ሊያቋርጥ ይችላል።












