የግብፅ እና የሶማሊያ ፕሬዝዳንቶች ለሦስትዮሽ ጉባዔ አሥመራ ገቡ

የግብፅ፣ የሶማሊያ እና የኤርትራ ፕሬዝዳንቶች የጋራ የሦስትዮሽ ጉባዔ ለማድረግ በኤርትራ ዋና ከተማ አሥመራ ተገኝተዋል።
በሦስቱ አገራት መካከል በኤርትራ የሚደረገው የሦስትዮሽ የመሪዎች ጉባኤ የአገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም በቀጣናው ፀጥታ እና መረጋጋት ጉዳዮች ላይ የሚመክር መሆኑን የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
የሦስቱ አገራት መሪዎች እና ባለሥልጣናት ከዚህ በፊት በተናጠል ጉብኝት ሲያካሂዱ እና ሲነጋገሩ የቆዩ ሲሆን አሁን ደግሞ በመሪ ደረጃ በአንድ ላይ አሥመራ ተገኝተዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር በከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ የገቡት የሶማሊያው መሪ ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ትናንት ረቡዕ ማምሻውን እንዲሁም የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ለሥራ ጉብኝት ዛሬ ሐሙስ ረፋድ ላይ አሥመራ ገብተዋል።
ወደ አሥመራ ለሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ቀድመው የገቡት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ ነው ወደ ኤርትራ ያቀኑት።
የሁለቱ አገራት ፕሬዝዳንቶች አሥመራ የገቡት የኤርትራ መንግሥት ባደረገላቸው ግብዣ መሆኑን የማነ ገብረ መስቀል ገልጸዋል።
የግብፁ ፕሬዝዳንት እና የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር እንዲሁም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው የተካተቱባቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናትን የያዙ የአገራቱ ልዑክ አሥመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የአገራቱ መሪዎች በአገሮቻቸው መካከከል ያለውን ትብብር በማጠናከሩ ረገድ እንዲሁም ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ከማስታወቂያ ሚኒስትሩ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት እንደሻከረ የሚነገርላት ኤርትራ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ኢትዮጵያ በፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ውዝግብ ውስጥ ከምተገኘው የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት በተደጋጋሚ እያስተናገደች ትገኛለች።
የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዋና ከተማዋ አሥመራ የሚያደርገው በረራዎች ከመስከረም አጋማሽ በኋላ እንዲቋረጡ ሐምሌ ወር ላይ መወሰኑን ከገለጸ በኋላ፣ ጊዜው ከመድረሱ ቀደም ብሎ አየር መንገዱ ገጠሙኝ ባላቸው ችግሮች ምክንያት በረራውን መቋረጡ ይታወሳል።
የኢትዮ-ኤርትራ ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት ካበቃ በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የአውሮፕላን ጉዞ ሐምሌ 2010 ዓ.ም. መጀመሩ ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, @hawelti
በአሁኑ ወቅት ሁለቱን አገራት የሚያዋስኑ የድንበር በሮች በሙሉ ተዘግተው የሚገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ታድሶ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም የፕሪቶሪያ ስምምነት ተከትሎ መልሶ መሻከሩ ይገለጻል።
በአፍሪካ ቀንድ ያለው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋጋለ እየመጣ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ እንዲሁም በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረቶች ነግሰዋል።
በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት መሻከር እየተገለጸ በሚገኝበት ወቅት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከሶማሊያ እና ከግብፅ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያጠናከሩ ነው።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት መካከል እየተካሄደ ያለው የቃላት ጦርነት እየተባባሰ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ወደ ቀጥተኛ አሊያም የእጅ አዙር ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት ጭሯል።
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ስትወዛገብ የነበረችው ግብፅ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረሟ ኢትዮጵያን እንዲሁም የአፍሪካን ቀንድ ቀጣናን ስጋት ላይ ጥሏል።
ግብፅ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተገባው የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ለገባችው ሶማሊያ በሁለት ዙር በአውሮፓላን እና በመርከብ የተጫኑ የጦር መሳሪያዎች መላኳን ተከትሎ ውጥረቶቹ ተካረዋል።
የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ትብብር ስጋት ውስጥ የጣላት ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት አስታውቃለች።
የሶማሊያ መንግሥትንም “ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሠራ ይገኛል” ስትል ከሳለች።
የግብፅ የስለላ አገልግሎት ኃላፊ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአሥመራ ተገኝተው የፕሬዝዳንት አል ሲሲን መልዕክት ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ በማድረስ ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቧል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የግብፅ ጠቅላላ የስለላ አገልግሎት ኃላፊ አባስ ካሜል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባድር አብደልላቲ በቀጣናው ያለውን ወቅታዊ የደኅንነት እና የፖለቲካ ሁኔታ፣ እንዲሁም የአገራቱን ግንኙነት ማጠናከረን የሚመለከት መልዕክትን ለኤርትራው ፕሬዝዳንት ማድረሳቸው ተገልጿል።
የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የፕሬዝዳንት አል ሲሲን መልዕክት አሥመራ ተገኝተው ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባቀረቡበት እና በተወያዩበት ጊዜ ለሶማሊያ ያላቸውን ድጋፍ የገለጹ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ አንጻር ግን ስላነሱት ጉዳይ የተባለ ነገር የለም።












