የግብጽ እና የሶማሊያ ወታደራዊ ትብብር ኢትዮጵያን ለምን ስጋት ላይ ጣላት?

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና የግብጹ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና የግብጹ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ስትወዛገብ የነበረችው ግብጽ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረሟ ኢትዮጵያን እንዲሁም የአፍሪካን ቀንድ ቀጣናን ስጋት ላይ ጥሏል።

ግብጽ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተገባው የባህር በር መግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ለገባችው ሶማሊያ በሁለት የጦር አውሮፕላኖች የጦር መሳሪያዎች መላኳን ተከትሎ ውጥረቶቹ ተካረዋል።

የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ትብብር ስጋት ውስጥ የጣላት ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት አስታውቃለች።

የሶማሊያ መንግሥትንም “ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ስትል ከሳለች።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ግብጽ እና ሶማሊያ የገቡትን የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ተከትሎ የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ሁለት ሲ-130 የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች ማክሰኞ ነሐሴ 21/ 2016 ዓ.ም በሞቃዲሾ አየር ማረፊያ መድረሳቸውን ተከትሎ በቀጣናው ያለው ውጥረት እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል።

በተጨማሪም በመጪው ዓመት ጥር ወር የሚጠናቀቀው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)ን የሚተካው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰማሩ 10 ሺህ ወታደሮችን ግብጽ ለማሰማራት ዕቅድ ይዛለች።

ኢትዮጵያ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወታደሮቿን እንድታስገባ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለውን አልሻባብን በመዋጋት ረገድ የሶማሊያ ቁልፍ አጋር ነበረች።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት በአባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ውዝግብ ውስጥ ከገባችው ግብጽ ጋር ሶማሊያ ያላቸው ወታደራዊ አጋርነት መጠናከሩን ተከትሎ “ ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም” ስትል አስጠንቅቃለች።

የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር ለኢትዮጵያ መግለጫ በሰጡት ምላሽ “ሁሉም የዘራውን ያጭዳል እና ኢትዮጵያ ዋይታዋን ማቆም አለባት” ሲሉ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በዚህም የአገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማሽቆልቆሉን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለምን ቅራኔ ውስጥ ገቡ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የባህር በር አልባዋ ኢትዮጵያ የንግድ መዳረሻ ወደብ ማጣቷ ብዙ አስከፍሏታል።ኤርትራ በአውሮፓውያኖቹ 1990ዎቹ መገንጠሏን ተከትሎ ኢትዮጵያ ለሶስት አስርት ዓመታት ባህር አልባ ሆና ቆይታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለ50 ዓመታት በሚቆይ ሊዝ ለመከራየት እና የባህር ኃይል ጣቢያ ለመገንባት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ፈርመዋል።

ኢትዮጵያ በምላሹ ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና በመስጠትም ከዓለም የመጀመሪያዋ አገር እንደምትሆንም የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ሶማሊላንድ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀች አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። ከሶማሊያ ከተገነጠለች ከ30 ዓመታት በላይ ቢሆንም ነጻ አገርነቷ በአፍሪካ ኅብረትም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና አልተሰጠውም።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለሶማሊላንድ ዕውቅና እንደሚሰጡም በይፋ አልገለጹም።ይልቁንም እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉ አትራፊ ተቋማት ድርሻ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

ይህም የመግባቢያ ስምምነት ሶማሊላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥረውን ሶማሊያን ያስቆጣ ሲሆን ስምምነቱን ወረራ ስትልም ገልጻዋለች።የሶማሊላንድ በዚህ መልኩ ዕውቅና የማግኘቷ ጉዳይ ሌሎች አገራትም ዕውቅና እንዲሰጧት መንገድ ሊከፍት ይችላል የሚል ፍራቻ ሶማሊያ እንደነገሰባት የፖለቲካ ተንታኙ ጆናታን ፌንተን ሃርቬይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለዓመታት የወጪ ንግዷን በጂቡቲ ከማድረጓ አንጻርም ጎርቤት አገር የሆነችው ጂቡቲም ምጣኔ ኃብቷን ሊጎዳው እንደሚችል ስጋት እንዳላትም ተንታኙ ተናግረዋል።

እንዲያውም በቀጣናው ያለውን ውጥረት ለማርገብ የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው ካሏት ወደቦች ውስጥ በአንደኛው ኢትዮጵያ መቶ በመቶ እንድትጠቀምበት ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ወደቡ ከኢትዮጵያ ድንበር 100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ታጆራ ወደብ ነው የሚሆነው” ሲሉ ማህሙድ አሊ የሱፍ ለቢቢሲ ፎከስ አፍሪካ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ከፍተኛ አማካሪ የቀይ ባህር መዳረሻን ለኢትዮጵያ ይሰጡ እንደሆን ተጠይቀው ፈቃደኝነት አለማሳየታቸው ጋር ተያይዞ የአሁኑ የጂቡቲ ምላሽ ለውጥ እንዳለ ማሳያ ነው ተብሏል።

የሁለቱን አገራት ውጥረት ለማርገብ በቱርክ አሸማጋይነት የተደረገው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ሶማሊያ ከሶማሊላንድ ጋር የተገባው የመግባቢያ ስምምነት ፈርሶ ሉዓላዊነቴ እስካልተከበረ ድረስ አልቀበለውም በማለቷ ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል።

የግብጽ እና የሶማሊያ ወታደራዊ ትብብር በኢትዮጵያ ላይ የፈጠረው ስጋት

ሶማሊያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት ቅራኔ ካላት ግብጽ ጋር ወታደራዊ ስምምነት መግባት ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮን (አትሚስ) በሚተካው አዲሱ የሰላም ተልዕኮ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንደማይሳተፉ አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ወታደሮቿን ያዋጣችበት የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በመጪው ዓመት ጥር ወር ተልዕኮውን አጠናቆ የጸጥታ ሁኔታውን የሶማሊያ መንግሥት እንዲረከብ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ሆኖም በሶማሊያ የጸጥታ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ከአስር ሺህ የማይበልጡ ወታደሮች ያሉበት የሰላም አስከባሪዎች ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባለበት እንደሚሰማራ ተጠቅሷል።

ራሷን በነጻ አገር ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተገባው የባህር በር መግባቢያ ስምምነት ምክንያት ሶማሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች የሰላም ተልዕኮው ጊዜው ሳይጠናቅቅ እንዲወጡ በመግለጫዎች ማስታወቋ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን የባህር መግባቢያ ስምምነት ካልሰረዘች በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ስር እንዲሁም በሁለትዮሽ ስምምነት የሰፈሩት ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከአገሪቱ እንደሚወጡ እንደሚደረግ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት አስጠንቅቀዋል።

ኢትዮጵያ በአትሚስ ስር 3 ሺህ ያህል ወታደሮችን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አሰማርታለች።

ለበርካታ ዓመታት ለሶማሊያ ደህንነት ወታደሮችን ለገበረችው ኢትዮጵያ የከፈለችውን መስዋዕትነት የሚያጣጥል እንደሆነ ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።

ኢትዮጵያ “ለሶማሊያና ለአካባቢው ሰላምና ፀጥታ መስፈን፣ ለጋራ ዕድገት እና በክልሉ ያሉ ህዝቦች መካከል ያለውን የጠበቀ የእርስ በርስ ትስስር ይበልጥ እንዲጎለብት ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን” መግለጫው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ መውጣታቸው አገሪቷን ለጂሃዲስቶች ጥቃት እንድትጋለጥ ያደርጋል ሲሉ የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ክርስቶፈር ሆክኒ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የግብጽ ወታደሮች በሶማሊያ ምስራቃዊ ድንበር ላይ እንዲሰማሩ መታቀዱ ለኢትዮጵያ ስጋት እንደሚያሳድርባትም አክለዋል።

ግብጽ የታላቁን ህዳሴ ግድብ እንደ ህልውና ስጋት እንደምትመለከተው በተደጋጋሚ የገለጸች ሲሆን ደህንነቷ ላይ አደጋ ከተጋረጠ “እርምጃዎችን” እንደምትወስድ ከዚህ ቀደም አስጠንቅቃለች።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለምን አወዛጋቢ ሆነ?

ግብጽ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የውሃ አቅርቦቷን ይቀንሰዋል በማለት በተደጋጋሚ ስጋት መሆኑን ገልጻለች።

86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረው ኢትዮጵያ የታላቁን ህዳሴ ግድብ መገንባት የጀመረችው በአውሮፓውያኑ 2011 ነበር።

የግድቡ ግንባታ ሲጠነሰስ ጀምሮ ስትቃወም የነበረችው ግብጽ፣ ኢትዮጵያ የታችኛውን ተፋሰስ አገራት ጥቅምና መብት እንዲሁም የውሃ ደህንነት ከግምት ውስጥ አላስገባችም ስትል ትከሳለች።

ከዚህ ቀደም ግብጽ ስታገኘው የነበረውን የውሃ መጠን 2 በመቶ በመቀነስ ወደ 81 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ የመስኖ መሬት ልታጣ እንደምትችል ስትናገር ቆይታለች።

85 በመቶ የሚሆነውን የናይልን ውሃ የምትገብረው ኢትዮጵያ በበኩሏ በአገር ውስጥ ያለውን የኤሌክትሪክ ፍጆታ እጥረት ለመሙላት እና 60 በመቶ ለሚሆነው ህዝቧ ሽፋን እንዲያገኝ ግድቡ እንደሚያስፈልጋት ስታስረዳ ቆይታለች።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌትና ዓመታዊ የውሃ አለቃቀቅ በተመለከተ ግብጽ፣ ሱዳንና እና ኢትዮጵያ ሲያደርጓቸው የነበሩ የሶስትዮሽ ድርድሮች ፍሬ ያላፈሩ ሲሆን የመጨረሻው ውይይት የተደረገው በዚህ ዓመት ታህሳስ ወር ነበር።

የአገራቱ ውጥረት ምን ያህል አሳሳቢ ነው?

ግብጽ ከሶማሊያ ጋር የገባችውን ወታደራዊ ስምምነት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ “ታሪካዊ” ሲሉ ጠርተውታል።ምናልባትም ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ ተደጋጋሚ ዛቻ ስታደርስ ለነበረችው ግብጽ ይህንን እንደ ዕድል ልትመለከተው ትችላለች።

በታላቁ ህዳሴ ግድብ የተነሳው የአገራቱ ውዝግብ አሁን ከሶማሊያ ጋር ግብጽ ባደረገችው ወታደራዊ ስምምነት ምክንያት ወደ ግጭት የሚያመራበት መንገድ ሊኖር እንደሚችል የሆርን ኢንተርናሽናል የስትራቴጂ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ሐሰን ካነንጄ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ እና የግብጽ ወታደሮች በሶማሊያ ድንበር ላይ ከተገናኙ “ግጭት ውስጥ” ሊገቡ እንደሚችሉም ይናገራሉ።

ሶማሊላንድ በበኩሏ የግብጽ ጦር በሶማሊያ ተሰማርቶ የቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ ሲወድቅ እጇን አጣጥፋ እንደማትመለከት አስታውቃለች።

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በቅርቡ የግብጽ ጦር በሶማሊያ እንዲሰማራ መደረጉ ለሶማሊያ እና ለአጠቃላዩ የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ደኅንነት አሳሳቢ ነው ብሏል።

ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት ከዘለቀው የደም አፋሳሽ ጦርነትን ጨምሮ ላለፉት ጥቂት ዓመታት እርስ በርስ እየታመሰች ትገኛለች።ሶማሊያም ለሶስት አስርት ዓመታት ከነበረው አውዳሚ የእርስ በርስ ጦርነት እያገገመች ቢሆንም አሁንም የማዕከላዊ መንግሥቱ ከአልሻባብ ጋር ግጭት ላይ ነው።

ተንታኞች እንደሚሉም ሁለቱም አገራት ተጨማሪ ጦርነትን ሊያደርጉ በሚችሉበት አቅም ላይ አይደሉም። በሁለቱ አገራት መካከል ግጭት የሚነሳ ከሆነ ሌሎች ተዋናዮችን በመሳብ የቀይ ባህር ቀጣናን የበለጠ ሊያወሳስበው እንዲሁም በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ዶክተር ካነንጄ ያስረዳሉ።

በየዓመቱ ቢያንስ 17 ሺህ መርከቦች በስዊዝ ካናል በኩል ያልፋሉ።ይህም ማለት አንድ ትሪሊየን ዶላር የሚያወጣ 12 በመቶ የሚሆነው የዓለም ንግድ መተላለፊያ ቀይ ባህር መሆኑን የባህር ንግዶችን የሚቆጣጠረው ሎይድ ሊስት መረጃ ያሳያል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ቱርክ ያሉ አገራት ቀይ ባህርን ከሚያዋስኑት እንደ ሶማሊያ ካሉ አገራት ጋር አጋርነት በመፍጠር የበላይነት ለመያዝ እየሞከሩ ይገኛሉ።

ቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሁለቱን አገራት ለማሸማገል እና ሊስማሙበት የሚችሉበትን መንገድ ለመቀየስ የተሻለ ስፍራ ላይ ተቀምጠዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬት በሶማሊላንዱ በርበራ ወደብ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰች ሲሆን በኢትዮጵያ ላይም ባላት ኢንቨስትመንት በሁለቱም አገራት ላይ ተጽእኖ ማሳረፍ ትችላለች።

ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላት ቱርክ ሁለት ጊዜ ያህል ቀጥተኛ ባልሆነ ድርድር ልታሸማግላቸው ሞክራለች።ሶስተኛው ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት በመጪው ዓመት መስከረም ላይ እንደሚካሄድ ተገልጿል።