በኔታኒያሁ፣ በመከላከያ ሚኒስትራቸው እና በሐማስ ጦር አዛዥ ላይ የእስር ማዘዣ ወጣ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ፣ የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ጋላንት እና የሐማስ ጦር አዛዥ ዴይፍ

የፎቶው ባለመብት, EPA / Reuters / Supplied

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ፣ የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ጋላንት እና የሐማስ ጦር አዛዥ ዴይፍ

የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ዳኞች የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር እንዲሁም የሐማስ ወታደራዊ አዛዥ ላይ የእስር ማዘዣ አወጡ።

የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የቅድመ ችሎት ጉዳዮችን የሚመለከተው ምክር ቤት እስራኤል በፍርድ ቤቱ ሥልጣን ላይ ያቀረበችውን ተቃውሞ ውድቅ ማድረጉን እና በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱን ገልጿል።

የእስር ማዘዣው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የእስራኤል ጦር ጋዛ ውስጥ በፈጸመው የአየር ጥቃት መግደሉን ያሳወቀው የሐማስ ወታደራዊ አዛዥ ሞሐመድ ዴይፍንም ጭምር ያካትታል።

ዳኞቹ፣ ሦስቱ ግለሰቦች በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ከአንድ ዓመት በላይ ጋዛ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ወቅት ለተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ ለተፈጸሙ ወንጀሎች “የወንጀል ተጠያቂ መሆናቸውን” የሚያሳዩ “አሳማኝ መሠረት” መኖሩን አመልክተዋል።

እስራኤልም ሆነች ሐማስ ክሱን ውድቅ አድርገውታል።

ከዚህ የእስር ማዘዣ መውጣት በኋላ እስራኤል እና አጋሯ አሜሪካ አባል ያልሆኑበት 124 አባል አገራት ያሉት የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ውሳኔው ተግባራዊ እንዲሆን ወይም እንዳይሆን የመወሰን ሥልጣን አላቸው።

ባለፈው ግንቦት የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ካሪም ካን በኔታኒያሁ ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣ ጠይቀው ነበር። በኔታንያሁ ላይ ብቻ ሳይሆን በተሰናበቱት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላን እና በሟቹ የሐማስ ወታደራዊ መሪ ሞሐመድ ዴይፍ እንዲሁም በሌሎች ሁለት የሐማስ መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ጥያቄው ቀርቦ ነበር።

ከሐማስ መሪዎች መካከል በእስራኤል ቴህራን ላይ የተገደሉት የቡድኑ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ እና ሌላው የሐማስ መሪ ሟቹ ያህያ ሲንዋር ይገኙበታል።

ዐቃቤ ሕግ በእነዚህ የሐማስ መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣባቸው የጠየቀው ከመስከረም 26/2016 ዓ.ም. መብረቃዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ ነው። በዚያ ዕለት ሐማስ 1200 ሰዎችን ገድሎ 251 የሚሆኑትን አግቶ ወደ ጋዛ መውሰዱ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ እስራኤል ከፍተኛ የተባለ ወታደራዊ ዘመቻ የከፈተች ሲሆን፣ እስከ ቅርብ ጊዜ 44 ሺህ ሰዎችን ጋዛ ውስጥ ገድላለች።አሃዙ በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስትር ነው።

የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ካን የሐማስ መሪዎችን በጦር ወንጀልና በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ሰዎችን በመሰወር፣ በማሰቃየት እና በሌሎችም ወንጀሎች ከሰዋቸዋል።

የእስራኤል መሪዎችን ደግሞ ንጹሐንን ሆን ብሎ በመግደል፣ ረሃብን እንደ መሣሪያ በመጠቀም እና በመግደል ነው ክስ የቀረበባቸው።