በሰሜን ሸዋ ደራ ስለ ተከሰተው እና ስለ አሰቃቂው ቪዲዮ እስካሁን የምናውቀው

ከደራ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እና በአሰቃቂ ሁኔታ ልጃቸው የተገደለባቸው አቶ አመራ ተስፋ

የፎቶው ባለመብት, Daniel

የምስሉ መግለጫ, ከደራ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እና በአሰቃቂ ሁኔታ ልጃቸው የተገደለባቸው አቶ አማረ ተስፋ

በሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ አንድ ወጣት በታጣቂዎች ተይዞ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከታየ በኋላ በርካቶችን አስቆጥቷል።

በአካባቢው በተለያየ ጊዜ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የሚጋጩት የፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ይንቀሳቀሳሉ።

ጉዳዩን በሚመለከት ቢቢሲ ኦሮምኛ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ግድያው የተፈጸመው በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ “የፋኖ ታጣቂዎች” መሆኑን ይናገራሉ።

ነገር ግን ይህንን ክስ በተመለከተ ከፋኖ ቡድን የተሰጠ ምላሽ የለም፤ ቢቢሲም በአካባቢው ይንቀሳቀሳል ከተባለው ቡድን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።

ድርጊቱ የተፈጸመው ከሁለት ወራት በፊት ነው የሚለው ዳንኤል ገመዳ ወደ ሰሜን ሸዋ ደራ አካባቢ አምርቶ የሟችን ቤተሰቦች ማነጋገሩን ለቢቢሲ ገልጿል።

ግድያው የተፈጸመበት ወጣት ደረጀ አማረ ተስፋ እንደሚባል እና የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ቤተሰቦቹ የሄደ እንደነበር ዳንኤል ጨምሮ አስረድቷል።

በሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንዲሁም የፋኖ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ በተለያየ ጊዜ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ይጋጫሉ።

ቢቢሲ ከኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፣ የደራ ወረዳ አስተዳደር እና የፀጥታ ኃላፊዎች ግድያውን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ሐሙስ በሰጡት መግለጫ በሰሜን ሸዋ ደራ ከተፈጸመው ድርጊት ጋር “አሸባሪ እና ጽንፈኛ ቡድኖች በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙት” የጭካኔ ድርጊት ነው በማለት አውግዘዋተል።

ኃላፊው ጨምረውም ቡድኖቹ “የተለያየ ቋንቋ ይናገሩ እንጂ ድርጊታቸው ተመሳሳይ ነው” በማለት ድርጊቱ በሕዝቡ መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር የተፈጸመ ነው ብለዋል።

መንግሥት ሸኔ የሚለው ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች የሕዝብ ደኅንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ እና ልማት እንዲደናቀፍ እያደረገ ነው ያሉት አቶ ኃይ፤ኡ፤ ፋኖ ደግሞ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች በንጹሃን ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደሪ አቶ ከፋለው በበኩላቸው ይህ ድርጊት ወደ ተፈጸመበት ስፍራ በመሄድ ሁኔታውን አጣርተው እንደሚናገሩ ለቢቢሲ ኦሮምኛ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን እንደሰማ ገልጾ ማጣራት መጀመሩን እና የደረሰበትን ውጤት ወደፊት እንደሚያሳውቅም ገልጿል።

ቢቢሲ ቪዲዮው መቼ እና የት እንደተቀረፀ ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአሰቃቂው ቪዲዮ ላይ የሚታየው የ10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረ እና የዓመቱን ትምህርት አጠናቅቆ ለእረፍት ወደ ቤተሰቦቹ ያመራው ደረጀ እንዲሁም ጓደኛው ከማል ሁሴን በአንድ ቀን መገደላቸው ተነግሯል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ በከጀማ ተራራ ሸሽተው ነበር። ደረጀ እና ሌሎች ግን በቀያቸው የቆዩት በበረት ታስረው የሚገኙትን እንስሳትን ለመጠበቅ ነበር።

በአካባቢው የነበሩ የፋኖ ታጣቂዎች ደረጀ እና ከማል ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የደረጀ አባት የሆኑትን አቶ አማረ ተስፋ ቶላን አግኝቼ አነጋግሬያለሁ የሚለው ዳንኤል፣ “ያን ቀን አሳድደው እግሩን ተኩሰው መትተው ከያዙት በኋላ ሳርኩላ ወደ ሚባል ቦታ ወሰዱት። እዚያ ቦታ ነው የፋኖ ታጣቂዎች በብዛት የሚንቀሳቀሱት” ይላል።

ደረጀ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሎ አስከሬኑ ለአውሬ የተጣለው እዚያ ቦታ መሆኑን የተናገሩት አባትየው፣ የልጃቸውን መገደል ቢሰሙም አስከሬኑን አግኝተው መቅበር አለመቻላቸውን ጨምሮ ገልጿል።

የደረጀ እናት እና አባት በልጃቸው ሞት ምክንያት አእምሮ ጤናቸው መቃወሱን ዳንኤል ይናገራል።

“የደረጀ እናት አእምሮአቸው ተጎድቷል እና አትናገርም። ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም። ለማንም አይመልሱም።”

ደረጀ ለቤተሰቡ ታናሽ ልጅ ሲሆን ወንድሞቹ እና እህቶቹ አግብተው ከቤት በመውጣታቸው እናት አባቱን ለማገዝ በቤት ያለ ብቸኛ ትንሽ ልጅ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።

ቢቢሲ በደራ ወረዳ ቱሉ ጉዳ መንደር በሼህ ሁሴን መስጂድ አቅራቢያ ነዋሪ የሆኑና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ነዋሪ በርካታ የፋኖ ታጣቂዎች በሼህ ሁሴን መስጊድ አካባቢ እንደሚኖሩ ያስረዳሉ።

እኚህ ነዋሪ በተለያየ ጊዜ የፋኖ ታጣቂዎች ሰዎችን ገድለው ወደ ወንዝ እንደወረወሩ ይናገራሉ።

“ብዙ ጊዜ ለምነን ሬሳውን እንቀብራለን፤ ሳይቀበሩ የቀሩም አሉ።”

በአካባቢው ባለው ተደጋጋሚ ግጭት እና ጥቃት የተነሳ ያመረቱት ምርት መቃጠሉን የሚናጉት እኚህ ነዋሪ ከየቤታቸው ሸሽተው መሄጃ ያጡ ነዋሪዎች በመስኪዱ ዙሪያ ተሰብስበው ለመኖር መገደዳቸውን ገልጸዋል።

እኚህ ግለሰብ አክለውም ታጣቂዎች ደረጀን ለመግደል ሲዝቱ እንደነበር መስማታቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪ ታጣቂዎችን የመንግሥት ኃይሎች ከመጡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላትን ትመግባላችሁ በሚል ጥቃት ያደርሱብናል በማለት ፍርሃት እንዳለባቸው ይናገራሉ።

በተጨማሪም የፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ከመጡ ደግሞ ቤት ያቃጥላሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ይገድላሉ ሲሉ ነዋሪዎች መናገራቸውን ዳንኤል ይናገራል።

ለዚህም ማሳያ አንድ የአካባቢው ነዋሪ “ፋኖ ታጣቂዎች” ወደ ቤታቸው መጥተው አንደነበር ገልጸው “ባለቤቴ እና አማቴ ቤት ነበሩ። አማቴ ልጄን ደብቃ ከአባቷ ጋር ወጥታለች ብላ አሸሸቻት። እርሷን መትተዋት ባለቤቴን ይዘዋት ወጡ” ይላሉ።

ግለሰቡ ባለቤታቸውን ለማስለቀቅ 10 ሺህ ብር ቢከፍሉም ከቀናት በኋላ ግን ባለቤታቸው በታጣቂዎች መደፈራቸውን መስማታቸውን ለቢቢሲ ኦሮምኛ ተናግረዋል።

“መጀመሪያ አንደተደፈረች ደብቃ ነበር። ነገር ግን የአካባቢው ሰዎች ማውራት ሲጀምሩ ነው ለእኔ የነገረችኝ። እኔ እንዲለቋት ብዬ 10 ሺህ ብር ከፍዬ ነበር።”

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ከሚፈጽሙት የንብረት ውድመት እና ዘረፋ በተጨማሪም በተደጋጋሚ የመድፈር ጥቃቶች ይፈጽማሉ ሲሉ ነዋሪዎች ይከሳሉ።

በችግር ላይ የሚገኙት ነዋሪዎች

ሌላ በአካባቢው በሚገኝ መስኪድ ውስጥ ከሰኔ ወር ጀምሮ ተጠልለው የሚገኙ አንድ ነዋሪ “መውጫ መንገድ የለም። ለመንግሥት ይግባኝ ለማለት ምንም መንገድ የለም። መንገድ ዘግተው ያሉት እነርሱ [የፋኖ ታጣቂዎች] ናቸው” ይላሉ።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች አርሶ አደሮቹ ያመረቱትን ዘርፈው፣ የተረፈውን በማቃጠላቸው በአሁኑ ጊዜ የሚበላ ነገር በእጃቸው አለመኖሩን ይናገራል።

“በፊት በዘር እና በሃይማኖት ሳንከፋፈል አብረን እንኖር ነበር” የሚሉት እኚሁ ግለሰብ፣ “በጾም ወቅትም አብረን ጾምን ነበር። በኢሬቻ ጊዜ እንኳን ከአማራ ተወላጆችጋር አክብረናል” ሲሉ በአካባቢው የሚኖረው ማኅበረሰብ የነበረበትን ትስስር ይገልጻሉ።

“አሁን ግን እነዚህ ታጣቂዎች መጥተው አብረን የምንኖረውን ሰዎች በእኛ ላይ አነሳሱብን” በማለት የተለያዩ ሰቅጣጭ ጥቃቶች እና ግድያዎች መፈጸማቸውን ለቢቢሲ ኦሮምኛ በዝርዝር አስረድተዋል።

ሌላው የደራ ወረዳ ነዋሪ በበኩላቸው ከፍርሀት የተነሳ ማገዶ ለመልቀም እንኳ የምንሄደው በጋራ ነው ይላሉ።

ለዚህም ምክንያታቸውን ሲያስረዱ “ምናልባት አንዱ እንኳ ቢያዝ ጮኽን ለማስለቀቅ በሚል ነው በጋራ የምንሄደው።”

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በቀን አንድ ጊዜ እንኳ ለመመገብ እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ።

ባለፈው ዓመት መንግሥት የእርዳታ እህል ወደ ስፍራው ቢልክም በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እጅ መግባቱን ይናገራሉ።

መንግሥት ጉዳዩን በሚመለከት እስካሁን ድረስ ያለው የለም።

በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂዎች በሚደርሱ ጥቃቶች የተነሳ በርካቶች ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።

የፌደራል መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር የገባውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለሁለት ዙር በታንዛኒያ ያካሄደው ድርድር ያለውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።