“በእሳት እየተቃጠልን እያያችሁ ዝምታን መረጣችሁ” - እናት እና ልጆች በእሳት ቃጠሎ ያጣው ቤተሰብ

የፎቶው ባለመብት, al-Dalou family photograph
ማሳሳቢያ፡ ይህ ታሪክ አንባቢያንን የሚረብሽ ገለፃ ይዟል
ሰብዓዊነት የጠፋ ይመስላል። አቅም ያላቸው የሚባሉ መሪዎች እንኳ እያዩ ምንም እያደረጉ አይደለም።
አሕመድ አል-ዳሉ እንዲህ ነው እምነቱ። ቤተሰቡ በእሳት ሲቃጠል ተመልክቷል። ይህ ምሥል መቼም ከአእምሮው የሚጠፋ አይመስልም።
“ከአሁን በኋላ ሕይወት የለኝም” ይላል።
ሰኞ ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም. ወንዶች ልጆቹ እና ሚስቱ ጋዛ ውስጥ አል-አቅሳ በሚባል ስፍራ በእሳት ተቃጥለው ሞቱ። ከዚህ በኋላ በሕይወት ላይ ተስፋ ቆርጧል።
ከፊት ለፊቱ በጨርቅ የተጠቀለለ አስከሬን አለ። የ12 ዓመት ወንድ ልጁ አብዱልራህማን አስከሬን ነው። የመጨረሻ ልጁ።
በእስራኤል ጥቃት በተነሳ እሳት ምክንያት ነው ልጁ ተቃጥሎ የሞተው። በቃጠሎው ተጎድቶ አራት ቀናት ሆስፒታል ቆይቷል። ከመሞቱ አንድ ቀን ቀድሞ አሕመድ ሆስፒታል ተገኝቶ ልጁን አይቶት ነበር።
“አባዬ አታስብ፤ ደኅና ነኝ። ደኅና ነኝ አባዬ። አትፍራ” ለመጨረሻ ጊዜ ከልጁ የሰማው ድምፅ ነበር።
አሕመድ እንባ እየተናነቀው ነው የሚናገረው።
“ሦስት ጊዜ ከእሳት ውስጥ ላወጣው ሞከርኩ። ነገር ግን ሰውነቱ ወደ እሳቱ ወደቀ” ይላል።
ታላቅ ወንድሙ የ19 ዓመቱ ሻባን እና የ37 ዓመት እናቷ አላ በዚሁ ምሽት በተነሳው እሳት ሞተዋል።
ሻባን የጋዛ ስቃይ መለያ ምልክት ሆኗል። በሕይወት ሳለ በእሳት ሲቃጠል የሚያሳይ ዘግናኝ ምሥል በማኅበራዊ ሚድያ ላይ ተሠራጭቷል።
አሕመድ ፊቱ እና እጁ በእሣት ተቃጥሏል። ሚሳዔሉን የተኮሰው ፓይለት እና ትዕዛዙን የሰጡት መሪዎች “ልቤን ሰብረውታል፤ ቅስሜን ሰብረውታል. . . እሳቱ ቢበላኝ ይሻል ነበር” ይላል።

ጥቃቱ የተፈጸመው ሰኞ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ለሊት 7፡15 ሰዓት አካባቢ ነው።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) ዒላማ ያደረግነው የሐማስን “የዕዝ እና የቁጥጥር” ማዕከል ነው ይላል። ጥቃቱ የደረሰው ጋዛ ሰርጥ ውስጥ በአል-አቅሳ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ነው።
ሐማስ ሆስፒታሎች ውስጥ አልገኝም ሲል ወቀሳውን ያስተባብላል።
በጥቃቱ ምክንያት አራት ሰዎች ወዲያውኑ ሲገደሉ በርካቶች ከፍተኛ የተባለ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የእስራኤል መካለከያ ኃይል ሁኔታውን “እያጣራሁ ነው” ብሏል።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ የእሳት ቃጠሎው ምሥሎች “እጅግ የሚረብሹ ናቸው” ብለው እስራኤል ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ የበለጠ ጥንቃቄ እንድታደርግ አሳስበዋል።
“እስራኤል ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የመጠበቅ ግዴት አለባት። አሁን የተፈጠረው ነገር በጣም የሚረብሽ ነው። ሐማስ በሆስፒታሉ አካባቢ ሰላማዊ ዜጎች እንደ ምሽግ ቢጠቀም እንኳ የሆነው ነገር የሚረብሽ ነው።”
ዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታኒያ እና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት በጋዛ ጦርነት ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት አሳስቦናል ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጋዛው ጦርነት ሰዎች በእሳት እየተቃጠሉ ነው፤ በከባድ የጦር መሣሪያ እየተገደሉ ነው፤ በየቀኑ እየተተኮሰባቸው ነው።
ከፍርስራሶሽ ውስጥ የተረፉ ሰዎችን ለማውጣት የሚደረግ ጥረት፣ ሆስፒታሎች ውስጥ ያለው መረበሽ፣ መጨረሻ የሌለው ቀብር በካሜራ ዕይታ ውስጥ ገብተው ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ግን እነዚህ ግድያዎችን በካሜራ ስላልተቀረጹ ዓለም አላያቸውም።
የሻባን አል-ዳሉ አሟሟት ይለያል። እጆቹ ከእሳቱ ለመውጣት ሲሞክሩ ይታያሉ። በፍም እሳት የተከበበ ሰው ይታያል። የሚደርስለት ግን አጥቷል።
ከቃጠሎው በኋላ የሻባን ቪድዮዎች እና ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚድያ ላይ በስፋት መሰራጨት ጀምሯል። ሻባን ታዳጊ ነበር። የማኅበራዊ ሚድያን ኃይል ያውቀዋል። የየዕለት ተግባሩን በስልኩ ካሜራ ያስቀምጣል።
ስልኩ ውስጥ የተገኙት ቪድዮዎች እና ፎቶዎች ብዙ ነገር ያሳያሉ። ደም ሲለግስ ይታያል። ሌሎችም እንዲለግሱ ያበረታታል።
ቢቢሲ ከቃጠሎው የተረፉትን የሻባንን ቤተሰቦች አናግሯል። ቢቢሲ አካባቢው ባሉ ወኪሎች አማካይነት ነው ይህን ማድረግ የቻለው። ቢቢሲን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ወደ ጋዛ ሄደው እንዲዘግቡ ከእስራኤል ፈቃድ አልተሰጣቸውም።
ሻባን በጋዛው ጦርነት ምክንያት ከቤተሰቡ ጋር ሦስት ጊዜ ተፈናቅሏል። ሁለት እህቶች እና ሁለት ታናናሽ ወንድሞች አሉት።
“የምንኖርበት ሁኔታ አስከፊ ነው” ሲል በቀረጸው ቪድዮ ላይ ይታያል። “ቤት የለንም፣ ምግብ አጥሮናል፣ መድኃኒትም የለንም” ይላል።
ይህን ቪድዮ ሲቀርጽ ከኋላው የእስራኤል ድሮን ድምፅ ይሰማል። ድሮኗ አካባቢውን ትሰልላለች። ይህ የጋዛ ነዋሪዎች የዕለተ ዕለት እውነታ ነው።
የሻባን እና አብዱልራህማን ወንድም ሞሐመድ አል-ዳሉ ታላቅ ወንድሙን ለማዳን ወደ እሳቱ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ለቢቢሲ ይናገራል። ነገር ግን ሌሎች ሰዎች ይዘውት ነው የተረፈው። የዚያን ዕለት ውጪ ነው ያደረው። መንገድ ላይ ተኝቶ የወንድሞቹን ዕቃ እየጠበቀ።

ሞሐመድ ወንድሞቹ ከሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ አቅራቢያ አነስተኛ ጥላ ዘርግተው ምግብ ይሸጡ እንደነበር ያስታውሳል።
“ጠንክረን ሠርተን ያገኘውን ነገር በጥንቃቄ እንጠቀማለን። ያለን ነገር ሁሉ ሠርተን ያገኘነው ነበር። ሠርተን እንበላለን፤ ሠርተን እንጠጣለን። አሁን ግን ያለ ነገር ሁሉ ወድሟል።”
ሞሐመድ የቤተሰቡን የተቃጠለ አስከሬን ቢመለከትም ማወቅ የቻለው የእናቱን ብቻ ነው። ምንም እንኳ የእናቱ ሰውነት በእሳት ክፉኛ ቢጎዳም እጇ ላይ ባደረጉት አምባር ምክንያት ለይቷቸዋል።
“አምባሩን ባላየው ኖሮ እናቴ መሆኗን እንኳ መለየት አልችልም ነበር። እጇ ከሌላው የሰውነት ክፍሏ ተለያይቶ ነበር። ነገር ግን አምባሯ አለ። ከእጇ ላይ ወስድኩት።”
የእናቱ አንድ የቀረው ማስታወሻ ከእሳት ከተረፈው አስከሬኗ ላይ ያገኘው አምባር ነው።
የአል-ዳሉ ቤተሰብ ድንጋጤ ላይ ነው። የተረፉት ሐዘን ላይ ናቸው። “መግለፅ ይከብደኛል” ይላል ሞሐመድ።
“ለሰዎች ለማስረዳት እሞክራለሁ፤ ነገር ግን አይሆንልኝም። የገዛ ወንድሜ በእሳት ሲቃጠል አየሁት። እናቴም በእሳት ተቃጥላ ስትሞት አየኋት” ይላል።
“ምን እስኪሆን ነው የምትጠብቁት? ምን እስኪሆን ነው ዝም የምትሉት? በእሳት ስንቃጠል እያያችሁ ዝምታን መረጣችሁ?” ሲል የዓለም ማኅበረሰብን ይጠይቃል።















