ጋዛ ውስጥ አባት ለመንታ ልጆቹ የልደት ወረቀት እያወጣ ሳለ በእስራኤል የአየር ጥቃት ተገደሉበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጋዛ ውስጥ አንድ አባት የመንታ ልጆቹን የልደት ምስክር ወረቀት እያወጣ ሳለ እስራኤል ባደረሰችው የአየር ጥቃት ልጆቹ ተገደሉበት።
አሰር የተባለው ጨቅላ እና እሕቱ አይሰል ከተወለዱ ገና አራተኛ ቀናቸው ሲሆን አባታቸው ሞሐመድ አቡ አል-ቁምሳን የልደት ወረቀት ሊያወጣላቸው ሄዶ ነበር።
አባት ከቤት ውጭ ሳለ ነው ጎረቤቶች ደውለው ዳይር አል ባላህ የሚገኘው ቤታቸው በአየር ደብደባ መመታቱን የነገሩት።
በጥቃቱ የሞሐመድ ሚስት እና የመንታዎች እናት እንዲሁም ሴት አያታቸው መገደላቸው ተሰምቷል።
“ምን እንደተፈጠረ አላውቅም” ያለው ሞሐመድ “የነገሩኝ ነገር ቢኖር ቤቱ በአየር ጥቃት መደብደቡን ነው” ሲል ተናግሯል።
“የልጆቼን መወለድ ደስታ እንኳ በቅጡ አላጣጣምኩም” ሲል አክሏል።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር በጦርነቱ ምክንያት 115 ጨቅላ ሕፃናት ከተወለዱ ብዙም ሳይቆዩ ተገድለዋል ይላል።
ኤፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው ቤተሰቡ የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት የተጀመረ ሰሞን ከጋዛ ከተማ ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን ተከትሎ ነው ወደ መካከለኛው ሰርጥ የሚገኝ መሸሸጊያ የሰፈሩት።
ቢቢሲ ስለጥቃቱ አስተያየት እንዲሰጠው የእስራኤል መከላከያ ኃይልን ጠይቆ መልስ እየተጠባበቀ ነው።
እስራኤል ሐማስ ላይ በምታደርሰው ጥቃት ሰላማዊ ዜጎችን ላይ ጥቃት ላለማድረስ ሙከራ አደርጋለሁ ትላለች። ሐማስ በተለይ በርካታ ዜጎች በሚኖሩበት ሥፍራ ተሸሽጓል ስትልም ትከሳለች።
ነገር ግን የእስራኤል መንግሥት ባለሥልጣናት በተናጠል በሚደርሱ ጥቃቶች ላይ አስተያየት ከመስጠት ይቆጠባሉ።
ባለፉት ጥቂት ሳምንት በጋዛ የሚገኙ በርካታ መጠለያዎች ላይ ጥቃት ደርሷል።
ባለፈው ቅዳሜ ከቤታቸው የተፈናቀሉ ፍልስጤማዊያን የሚገኙበት ትምህርት ቤት ላይ እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት 70 ሰዎች መገደላቸውን የአንድ ሆስፒታል ዳይሬክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ትምህርት ቤቱ “የሐማስ እና የኢስላሚክ ጂሀድ ወታደራዊ ግምዠ ቤት ሆኖ እያገለገለ ነው” ቢሉም ሐማስ ግን ይህን አስተባብሏል።
እስራኤል የሟቾች ቁጥር ተጋኗል ብትልም ቢቢሲ ይህንን ቁጥር በግሉ ማጣራት አልቻለም።
በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7 የሐማስ ታጣቂዎች 1200 ሰዎችን ገድለው 251 ታጋቾችን አፍኖ ወደ ጋዛ መውሰዱ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቃት የከፈተች ሲሆን ከሐማስ ጋር የምታደርገው ጦርነት በርካታ ወራት አስቆጥሯል።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደሚለው በጦርነቱ ምክንያት 39 ሺህ 790 ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል።












