ሳዑዲ አረቢያ ለዓለም ዋንጫ ከምድር 350 ሜትር ከፍታ ላይ ስታዲየም ልትገነባ ነው

ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ስታዲየም 200 ሜትር ከፍታ ባለው ተራራ ላይ ይገነባል።

የፎቶው ባለመብት, Saudi 2034

የምስሉ መግለጫ, ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ስታዲየም 200 ሜትር ከፍታ ባለው ተራራ ላይ ይገነባል።

የ2034 የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ ያቀረበችው ሳዑዲ አረቢያ 350 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገነባውን ጨምሮ 11 ስታዲየሞችን ለውድድሩ እንደምታዘጋጅ አስታወቀች።

ይህ ስታዲየም ሳዑዲ ልትመሠርተው ባሰበችው ኒዮም ከተማ የሚገነባ ነው።

በሰሜን ምዕራብ ሳዑዲ የሚገነባው ኒዮም ከተማ እጅግ ዘመናዊ ሲሆን፣ ወደ ከተማው መግባት የሚቻለው ሰው አልባ በሆኑ ፈጣን ባቡሮች አማካይነት ነው።

በነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆነውን የሳዑዲን ኢኮኖሚ ለማዘመን በተጀመረው ‘ዘ ላይን’ ፕሮጀክት እየተገነባ በሚገኘው ከተማ የ2034 የዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች የሚደረጉበት ስታዲየም ዝግጁ ይሆናል ተብሎ በዕቅድ ተይዟል።

እስካሁን ድረስ የ2034 የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ሳዑዲ አረቢያን እየተፎካከር የሚገኝ አገር የለም። አገሪቱ በቀጣይ ሳምንታት የዝግጅት ዕቅድ ዝርዝር ታስገባለች ተብሎ ይጠበቃል።

ፊፋ ታህሳስ 2017 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ የ2034 የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ አገርን ይፋ ያደርጋል።

ሳዑዲ ከምትገነባቸው 11 ስታዲየሞች መካከል ስምንቱ መገኛቸው በመዲናዋ ሪያድ ይሆናል።

ከእነዚህ መካከል አንዱ የመክፈቻ እና የፍጻሜ ጨዋታዎችን የሚያስተናግደው እና 92ሺህ 760 ታዳሚዎችን መያዝ የሚችለው ንጉሥ ሰልማን ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተጠቃሽ ነው።

ጅዳ፣ አል ካሆባር እና አብሃ የተባሉ የሳዑዲ ከተሞች እንዲሁ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ያስተናግዳሉ።

በ2034 የዓለም ዋንጫ የተሳታፊዎች ቁጥር ጨምሮ 48 ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድር።

ሳዑዲ ምን ዓይነት ግንባታዎችን ታካሂዳለች?

በልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ስም የተሰየመው ስታዲየም 200 ሜትር ከፍታ ባለው ተራራ ላይ ይገነባል።

የዓለም ዋንጫ ዝግጅት አካል የሆነው የኒዮም ከተማ ግንባታ እንዲሁ ሳዑዲ ብዙ ገንዘብ የምታወጣበት ፕሮጀክት ነው።

‘ዘ ላይን’ በተሰኘው ፕሮጀክት ከተሸከርካሪ ነጻ የሆነ 200 ሜትር ስፋት እና 170 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ከተማ ይገነባል።

በ2030፣ 2.4 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው የከተማው ክፍል ተገንብቶ ይጠናቀቃል ተብሏል።

የሳዑዲ የዓለም ዋንጫ አዘጋጆች እንደሚሉት አገሪቱ የአዘጋጅነት ዕድሉን የምታገኝ ከሆነ የኒዮም ስታዲም ሙሉ በሙሉ የኃይል ግብዓቱን ከንፋስ እና ከፀሐይ ኃይል በመሰብሰብ በታዳሽ ኃይል የሚንቀሳቀስ ሆኖ ይገነባል።

ከዚህ በተጨማሪም እአአ በ2034፣ 12 ሚሊዮን ተጓዦችን ማስተናገድ የሚችል አየር ማረፊያ ለመገንባት ታቅዷል።

ሳዑዲ እንዲሁ የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ በሆኑ ከተሞች ለሚገኙ አየር ማረፊያዎች የማስፋፊያ ስራዎችን ትሠራለች።

የኒዮም ስታዲየም ዕቀድ ገጽታ

የፎቶው ባለመብት, Saudi 2034

የምስሉ መግለጫ, የኒዮም ስታዲየም ዕቀድ ገጽታ

የሪያድ አየር ማረፊያ በ2034 በዓመት የማስተናገድ አቅሙን በ170 ፐርሰንት በመጨመር ወደ 100 ሚሊዮን ተጓዦች ከፍ እንዲል ይደረጋል።

የአባሃ አየር ማረፊያ እንዲሁ ከ1.5 ሚሊዮን ወደ 8 ሚሊዮን ተጓዦችን የማስተናገድ አቅሙ ከፍ እንዲል ይደረጋል።

ሳዑዲ ከአየር ማረፊያ መሠረተ ልማት በተጨማሪ የባበሩ እና የአውቶብስ መስመሮችን ከፋ የማድረግ ዕቅድ ተይዟል።

ሳዑዲ የ2034 የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ምን ያህል እንደሚያስወጣት ያለችው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ዕቅዱ በመቶዎች የሚቆጠር ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያስወጣ ነው።

ኳታር የ2022 የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት 220 ቢሊዮን ዶላር ማውጣት ይፋ ተደርጓል።

የዓለም ዋንጫው መቼ ሊካሄድ ይችላል?

የ2034 የዓለም ዋንጫ የዝግጅት ጊዜ ገና ቀን አልተቆረጠለትም።

ይሁን እንጂ ሳዑዲ ውድድሩን እንድታዘጋጅ የሚፈቀድላት ከሆነ የውድድሩ ጊዜ የሚወሰነው በአገሪቱ ባለው ወቅት ነው የሚሆነው።

ውድድሩን እንዲያዘጋጁ በሳዑዲ የተመረጡ ከተሞች ከጥቅምት እስከ ሚያዚያ አማካይ የሙቀት መጠናቸው ከ15 እስከ 30 ዲግሪ ሴሊሺየስ ነው።

ከግንቦት እስከ መስከረም ግን በከተማዎቹ ያለው ሙቀት በአማካይ እስከ 38 ዲግሪ ሴሊሺዬሽ ከፍ ሊል ይችላል።

የስታዲየሞች ዝርዝር

ሪያድ

  • ንጉሥ ሰልማን ዓለም አቀፍ ስታዲየም - የመያዝ አቅም 92ሺህ 760
  • ንጉሥ ፋሃድ ስፖርት ሲቲ ስታዲየም - የመያዝ አቅም 70ሺህ 200
  • ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ስታዲየም - የመያዝ አቅም 46ሺህ 979
  • ኒው ሙራባ ስታዲየም - የመያዝ አቅም 46ሺህ 010
  • ሮሻን ስታዲየም - የመያዝ አቅም 46ሺህ
  • ልዑል ፋይሰል ቢነ እፋሃድ ስፖርት ሲቲ ስታዲየም- የመያዝ አቅም 46ሺህ 865
  • ሳውዝ ሪያድ ስታዲየም- የመያዝ አቅም 47ሺህ 060
  • ንጉሥ ሳዑዳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም- የመያዝ አቅም 46ሺህ 319

ጅዳ

  • ንጉሥ አብደላህ ስፖርት ሲቲ ስታዲየም - የመያዝ አቅም 58ሺህ 432
  • ኪዲያ ኮስት ስታዲየም- የመያዝ አቅም 46ሺህ 096
  • ጂዳህ ሴንተራል ዴቨሎፕመንት ስታዲየም - የመያዝ አቅም 45ሺህ 794
  • ንጉሥ አብዱላህ ኢኮኖሚ ሲቲ ስታዲየም - የመያዝ አቅም 45ሺህ 700

አል ካሆባር

  • አርማኮ ስታዲየም- የመያዝ አቅም 46ሺህ 096

አባህ

  • ንጉሥ ካሃሊድ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም- የመያዝ አቅም 45ሺህ 428

ኒዮም

  • ኒዮም ስታዲየም- የመያዝ አቅም 46ሺህ 010
ንጉሥ ሰልማን ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመክፈቻ እና የዋንጫ ጨዋታ ያስተናግዳል ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Saudi 2034

የምስሉ መግለጫ, ንጉሥ ሰልማን ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመክፈቻ እና የዋንጫ ጨዋታ ያስተናግዳል ተብሏል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ስፖርት የኢኮኖሚ ስታራቴጂያቸው ውስጥ ካስገቡ በኋላ ሳዑዲ ከእአአ 2021 ጀምሮ በስፖርት ላይ ከ5 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ወጪ አድርጋለች።

ከእግር ኳስ በተጨማሪ ሳዑዲ የፎርሙላ 1፣ የጎልፍ እና የቦክስ ውድድሮችን አስተናግዳለች።

የአገሪቱ የኢንቨስትመንት ፈንድ የሳዑዲ ፕሮ ሊግን በበላይ ከመቆጣጠር አልፎ የእንግሊዙን ኒውካስል ዩናይትድን ገዝቷል።

ስመ ጠር የእግር ኳስ ተጫዋቾችም በከፍተኛ ገንዘብ የሳዑዲ ፕሮ ሊግን እንዲቀላቀሉ ሲደረግ ቆይቷል።

በርካቶች ታዲያ የሳዑዲ መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ የጎደፈ ስሙን በስፖርታዊ ውድድሮች ለመቀየር እየሞከረ ነው ይላሉ።

ሳዑዲ በሰብአዊ መብት አያያዟ ትችት ይቀርብባታል።

በሳዑዲ የሴቶች ነጻነት አይከበርም፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት አይፈቀድም፣ ሐሳብን በነጻነት የመናገር መብት የተገደበ ነው በሚሉ እና ሳዑዲ በየመን እየተካሄደ ባለ ጦርነት ባላት ተሳትፎ ስሟ በጥሩ አይነሳም።

ከዚህ በተጨማሪ እአአ 2018 ላይ የጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ የልዑል አልጋ ወራሹ ስም በእጅጉ ተበላሽቷል።

የሳዑዲ መንግሥት ግን በስፖርት ላይ እያደረገ ያለው ኢንቨስትምንት ኢኮኖሚውን እያነቃቃ እንደሆነና እና የቱሪዝም ፍሰት መጨመሩን ይገልጻል።

በፊፋ መርህ መሠረት የአንድ አገር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት ጥያቄ ተቀባይነት የሚኖረው በአገሪቱ የሰብአዊ መብት መከበሩ ሲረጋገጥ ነው።

ከወራት በፊት የሳዑዲ የስፖርት ሚኒስትር ልዑል አብዱላዚዝ ቢን ቱርኪ አል ፋይሳል አገራቸው ስፖርት ላይ ብዙ ገንዘብ የምታወጣው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስም ለማደስ ነው የሚባለው ስህተት ነው ብለዋል።

“የትኛውም አገር ማሻሻል የሚገባው ነገር ይኖረዋል። ማንም ሰው ፍጹም አይደለም። እኛም ይህን እንቀበላለን። ስፖርታዊ ሁነቶች ወደፊት እንድንሻሻል ያግዙናል” ብለዋል።