በኢትዮጵያ በአንድ ጨቅላ ላይ የተገኘው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምንድን ነው? እንዴትስ ይተላለፋል?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ በዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) የተያዘ ጨቅላ ሕጻን መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቀዋል።
በሕመሙ ተይዘዋል ተብለው ከተጠረጠሩ ሰዎች በተወሰዱ ናሙናዎች ላይ በተደረገ ምርመራ ቫይረሱ የተገኘው የ21 ቀን ዕድሜ ባለው ጨቅላ ላይ ሲሆን እናቱም ለቫይረሱ መጋለጧ ተገልጿል።
የበሽታው ምንጭ ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ ሄዶ ነበር የተባለው የሕፃኑ አባት ሊሆን እንደሚችል ሲጠረጠር፤ በሄደባቸው አካባቢዎች እንዲሁም ከግለሰቡ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ግለሰቦችን በመለየት ክትትል እየተደረገ ነው ተብሏል።
ቫይረሱ የተገኘበት ጨቅላ ሕጻን እና እናቱ በለይቶ ማከሚያ ውስጥ አስፈላጊው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ እንዲሁም የከፋ የጤና እክል እንዳገጠማቸው የአገሪቱ የጤና ባለሥልጣናት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ቀብሪበያ ወረዳ የዚሁ በሽታ ምልክቶች የታዩበት እና በበሽታው የተጠረጠረ አንድ ግለሰብ ተገኝቶ በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲሆን መደረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ ማስታወቁ ይታወሳል።
ከዚህ ውጪ አሁን በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ ቫይረሱ ከተገኘበት ጨቅላ ውጪ በአገሪቱ በኤምፖክስ መያዙ የተረጋገጠ እና ይፋ የተደረገ ሰው የለም።
ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በምሥራቅ እና ማዕከላዊ አፍሪካ በፍጥነት የተስፋፋው የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) በሽታ በመላው አፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ መሆኑን የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) አስታውቆ ነበር።
በወቅቱ የተከሰተው የበሽታው ወረርሽኝ ቀደም ሲል ከተከሰቱት ወረርሽኞች ሁሉ የበለጠ አደገኛ መሆኑን ባለሙያዎች ተናግረዋል። ለዚህም ምክንያቱ የተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ አዲስ ዓይነት የበሽታው ዝርያ በመሆኑ ነው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox) በሽታ የሚከሰተው ሞንኪፖክስ በተባለ ቫይረስ አማካኝነት ሲሆን፣ ይህም ጉዳቱ ዝቅተኛ ከሆነው የፈንጣጣ ቫይረስ ቡድን ውስጥ የሚመደብ ነው።
የበሽታው ቫይረስ በመጀመሪያ ላይ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ የነበረ ሲሆን፣ ኋላ ላይ ግን ከሰው ወደ ሰው የሚሠራጭ ሆኗል።
በሽታው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን በመሳሰሉ በአፍሪካ ዝናባማ ጥቅጥቅ ደኖች ውስጥ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰት ነው።
በእነዚህ አካባቢዎች በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታው የሚያዙ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለህልፈት ይዳረጋሉ። ከ15 ዓመት ዕድሜ በታች የሚገኙ ልጆች በበሽታው በአስከፊ ሁኔታ ይጠቃሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምንድን ነው?
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በሁለት ዋነኛ የቫይረስ ዝርያዎች አማካይነት ሲሠራጭ ቆይቷል።
“ክሌድ 1” (Clade 1) የባለው የቫይረሱ ዓይነት በማዕከላዊ አፍሪካ በስፋት ይገኛል። “ክሌድ 1ቢ” የተባለው ደግሞ እየተስፋፋ ያለ አዲስ የቫይረሱ ዝርያ ከመሆኑ በተጨማሪ በጣም አደገኛ ነው።
የአፍሪካ ሲዲሲ እንዳለው ባለፈው ዓመት ከጥር እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ በነበሩት ሰባት ወራት ውስጥ ከ14,500 በላይ ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ ተይዘው ከ450 በላይ የሚሆኑት ሞተዋል።
ከበሽታው ክስተት 96 በመቶው በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የተመዘገበ ሲሆን፣ ከዚያም ጎረቤት ወደሆኑት እና የዝንጀሮ ፈንጣጣ እምብዛም ወደ ማይታወቅባቸው ቡሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ተስፋፍቷል።
በአውሮፓውያኑ 2022 ቀለል ያለው እና በምዕራብ አፍሪካ የሚገኘው “ክሌድ 2” (Clade II) የተባለው የበሽታው ዝርያ በዓለም ዙሪያ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ነበር።
በወቅቱ በሽታው ቫይረሱ ተከስቶባቸው የማያውቁት የአውሮፓ እና የእስያ አገራትን ጨምሮ 100 በሚጠጉ አገራት ውስጥ ተከስቶ ነበር። ነገር ግን ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በመከተብ ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ውሏል።
እስካሁን በየትኞቹ አገራት ተከሰተ?
በዲሞክራቲክ ኮንጎ ያለው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባት እና ሕክምና አቅርቦት ዝቅተኛ በመሆኑ የአገሪቱ የጤና ባለሥልጣናት የበሽታው ሥርጭት በየጊዜው በአሳሳቢ ሁኔታ ይከሰታል።
ባለፈው ዓመት የበሽታው ክስተት በምሥራቅ እና በመካከለኛው የአፍሪካ ክፍሎች በመስፋፋቱ ምክንያት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የጤና ባለሥልጣናት የዝንጀሮ ፈንጣጣ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት ነው ሲሉ አውጀው ነበር።
ከዲሞክራቲክ ኮንጎ በተጨማሪ በኡጋንዳ በኬንያ፣ በሩዋንዳ እና በቡሩንዲም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።

የበሽታው ምልክቶች
በቫይረስ አማካይነት በሚተላለፈው በዝንጀሮ ፈንጣጣ በተያዘ ሰው ላይ መጀመሪያ የሚታዩት ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ እብጠት፣ የጀርባ እና የጡንቻ ሕመምን ያካትታል።
ትኩሳት ከተከሰተ በኋላ ከፊት ጀምሮ ቀሪውን የሰውነት ክፍልን የሚያዳርስ ሽፍታ የሚከሰት ሲሆን፣ ሽፍታው በአብዛኛው በእጅ መዳፍ እና በእግር መረገጫ ላይ ይከሰታል።
በሰውነት ላይ የሚያጋጥመው ሽፍታ በጣም የሚያሳክክ እና የሚቆጠቁጥ ሲሆን፣ በተለያዩ የለውጥ ደረጃዎች ውስጥ አልፎ በመጨረሻም እብጠት በመፍጠር ኋላ ላይም ይከስማል። ቁስለቱም ጠባሳን ትቶ ሊያልፍ ይችላል።
በሽታው በአብዛኛው ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ በራሱ የሚጠፋ ይሆናል።
በበሽታው የተያዘው ሰው ክፉኛ የተጎዳ ከሆነ ቁስለቱ አጠቃላይ ሰውነቱን፣ በተለይ አፍ፣ ዓይን እና የመራቢያ አካላት ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።

የመተላላፊ መንገዶች
ኤምፖክስ ቫይረስ ቤተ ሙከራ ውስጥ በሚደረግ ምርመራ የሚለይ ሲሆን፣ በሰውነት ንክኪ ይተላለፋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወሲባዊ ግንኙነትን፣ የቆዳ ንክኪን እና በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ማውራትን ወይም መተንፈስን ጨምሮ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር በሚኖር የቀረበ ግንኙነት ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።
የበሽታው ቫይረስ ወደ ሰውነት በቆሰላ ቆዳ፣ በመተንፈሻ አካላት፣ በዓይን፣ በአፍንጫ ወይም በአፍ በኩል ሊገባ ይችላል።
በተጨማሪም በቫይረሱ የተበከሉ የመኝታ አልባሳት፣ በልብሶች እና በፎጣዎች አማካይነት በሚኖር ንክኪ በሽታው ሊተላለፍ ይችላል።
ሌላኛው የበሽታው መተላለፊያ መንገድ ደግሞ ቫይረሱ ካለባቸው ዝንጀሮ እና አይጦችን ከመሳሳሉ እንስሳት ጋር የሚኖር ንክኪም አንዱ ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት የዝንጀሮ ፈንጣጣ በዓለም ዙሪያ በበርካታ አገራት ውስጥ በተከሰተበት ጊዜ ቫይረሱ በዋናነት በወሲባዊ ግንኙነት ወቅት በሚፈጠር ንክኪ አማካኝነት ነበር የተሠራጨው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለበሽታው ተጋላጮች
አብዛኛው የበሽታው ክስተት የተመዘገበው ወሲባዊ ግንኙነት በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ እና የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት በሚፈጽሙ ወንዶች ላይ ነው። በተጨማሪም በርካታ የወሲብ አጋሮች ያሏቸው እና አዲስ የወሲብ አጋር የያዙ ሰዎች ለበሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ናቸው።
የበሽታው ምልክቶች ካለባቸው ሰዎች ጋር የቀረበ ንክኪ ያላቸው የጤና ባለሙያዎች እና በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቤተሰቦች በቫይረሱ ሊያዙ ይችላሉ።
ስለዚህም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ካለባቸው ሰዎች ጋር የሚኖር የቀረበ ንክኪን ማስወገድ እና በምንኖርበት አካባቢ በሽታው ከተከሰተ እጅን በሳሙና እና በውሃ በአግባቡ መታጠብ ይመከራል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው በበሽታው ተይዘው የዳኑ ሰዎች ለ12 ሳምንታት ያህል ወሲባዊ ግንኙነት ሲፈጽሙ ኮንዶም መጠቀም ይኖርባቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሕክምና
የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለማከም የተዘጋጀ ሕክምና የታመሙ ሰዎችን ለማዳን በጣም ጠቃሚ ቢሆንም፣ ነገር ግን ሕክምናው ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ የሚያሳይ ውስን ጥናት ነው ያለው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝን በሽታውን በመከላከል መቆጣጠር የሚቻል ሲሆን፣ ይህንንም ለማድረግ ተመራጩ መንገድ የመከላከያ ክትባት መስጠት ነው።
በአሁኑ ጊዜ ሦስት በሽታውን መከላከያ የክትባት ዓይነቶች አሉ፤ ነገር ግን ክትባቶቹ የሚሰጡት ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቀረበ ንክኪ ላላቸው ብቻ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም ሰው መከተብ አለበት ብሎ አይመክርም።
ያሉት የክትባት ዓይነቶች አዲስ ከተከሰተው የበሽታው ዝርያ አንጻር ምን ያህል የመከላከል አቅም አላቸው የሚለውን ለማወቅ ተጨማሪ ሙከራዎች እየተደረጉ ቆይተዋል።
ባለፈው ዓመት የዓለም የጤና ድርጅት መድኃኒት አምራቾች ያሏቸው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባቶች በሚፈለጉባቸው አገራት ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ ባያገኙ እንኳን ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ጠይቆ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የድንበር ላይ ቁጥጥር
መረጃው ለሕብረተሰቡ ማድረስ፣ ምርመራ ማድረግ፣ ሕክምና መስጠት እና በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን መለየት ቫይረሱን ለመከላከል ዋነኛ መንገዶች ናቸው።
በምሥራቅ እና በማዕከላዊ የአፍሪካ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ አገራት የድንበር አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ከአንድ አገር ወደ ሌላ ድንበር አቋርጠው የሚሻገሩ በመሆናቸው ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።
በኮንጎ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ጥናት አስተባባሪ ላንድሪ ሙራሁላ ማሲሪካ እንደሚሉት፣ ክፍት ድንበር መኖሩ በሽታውን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ያሰናክላል።
ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ለመሠራጨት እስከ 20 ቀናት የሚወስድበት ሲሆን፣ አንዳንዴ ምልክቱ የመራቢያ አካል አካባቢ ብቻ ሊታይ ስለሚችል በድንበር አካባቢ ቁጥጥር ለማድረግ አዳጋች ነው።
ስለዚህም በሽታው ያለበትን ሰው ምልክቱን ብቻ በማየት ለመለየት አስቸጋሪ ስለሚሆን ድንበር ላይ መደበኛ ምርመራ ማድረግ እንደሚያሻ ባለሙያው ይመክራሉ።
በተጨማሪም ከበሽታው ጋር ተያይዞ የሚከሰትን ማግለል ለማስቀረት ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ እንዲደረግም ያሳስባሉ።
ቫይረሱ በማኅበረሰቡ ውስጥ የመሠራጨት ደረጃ ላይ እንደደረሰ በዚህም ነፍሰ ጡር ሴቶች እና ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት እንደሚጎዱ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images















